የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፋቸው ትልልቅ ተፅዕኖዎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በተለይ በምርትና ሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያስከትል መሆኑም በግልጽ ይታወቃል፡፡ ችግሩ ግን በአገራችን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተንተርሰው የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች በዘፈቀደ የሚካሄዱ መሆናቸው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተፅዕኖ ያከብዱታል፡፡
ከዚህ ቀደም የነዳጅ ዋጋ ጨመረ በተባለ ቁጥር ሲታዩ የነበሩ ዋጋ ጭማሪዎች በነዳጅ ላይ የተጨመረውን ዋጋ ያገናዘቡ ያለመሆናቸውና በተዋረድ ሁሉም የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች የመሰላቸውን ዋጋ ስለሚያወጡ የዋጋ ጭማሪው ተደራርቦ ሸማቹንና ተገልጋዩን በእጅጉ ሲጫን ቆይቷል፣ አሁንም እየተጫነ ነው፡፡
በአንድ ሌትር ናፍጣ ላይ አንድ ብር ጨመረ ሲባል ይቺህን አጋጣሚ ያገኘ ሰበብ ፈላጊ ነጋዴዎች በተለያዩ ምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ዋጋ ለመጨመር ይፈጥናሉ፡፡ የዋጋ አጨማመሩ በሥሌትና ትክክለኛውን ጭማሪ በመደመርና በማባዛት ሳይሆን፣ በዘፈቀደ የሚካሄደው የዋጋ ጭማሪ ደግሞ የዋጋ ንረቱን በማባባስ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡
ብዙ ጊዜ የሸቀጥ ምርቶች ዋጋ ባለተጠበቀ ሁኔታ ሲጨምሩ የነበረውም ነዳጅ ጭማሪ ተደረገ በተባለበት ወቅት ነው፡፡ ነዳጅ ላይ አንድ ብርም ጨመረ አምስት ብር ጭማሪውን ሰበብ በማድረግ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ የነዳጅ ዋጋ በጨመረበት ልክ ታሳቢ የሚደረግ አይደለም፡፡ በትክክለኛ የነዳጅ ጭማሪ ሊያስከትል የሚችለውን የዋጋ ጭማሪውን ብናሠላ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ፈጽሞ ኢኮኖሚያዊ ያለመሆኑንም በቀላሉ መገንዘብ ይችላል፡፡
ለምሳሌ በአንድ ሌትር ናፍጣ ላይ አምስት ብር ጭማሪ ተደረገ ቢባል፣ አንድ ኩንታል ስንዴ ወይም ጤፍ ለማምጣት በኩንታል 100 ብር ይጠየቅ ከነበረ፣ በአንዴ 20 እና 30 ብር ይጨመራል፡፡ ይህ ጭማሪ ከተደረገው የነዳጅ ጭማሪ ጋር ሲመሳከር ፈፅሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ የትራንስፖርት ዋጋው ላይ 20 እና 30 ብር ጨመረብኝ ያለ ነጋዴ ደግሞ እንደገና በሚሸጠው ምርት ላይ የሚያደርገው ጭማሪ የተጋነነ ስለሚሆን በአምስት ብር የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአንድ ኩንታል ጤፍም ሆነ ስንዴ ዋጋ ላይ መቶና ሁለት መቶ ብር ጭማሪ ይደረጋል፡፡
ከዚያም በላይ የሚሆንበትን አጋጣሚንም ታዝበናል፡፡ ትክክል የነዳጅ ጭማሪው በማጓጓዣ ዋጋው ላይ ሊያስከት የሚችለው የዋጋ ልዩነት ከላይ እስከ ታች ያሉ በግብዓት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ከሚጨምሩት ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡ ይህ የዕውር ድንበር አሠራር ነዳጅ በጨመረ ቁጥር ብዙዎች ያልተገባ ዋጋ እንዲተከሉ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸው አሁንም ድረስ እየሠሩበት ነው፡፡
ይህ በዘፈቀደ የሚደረግ ጭማሪ ተቆጣጣሪ የሌለው በመሆኑና ለዓመታት በዚሁ መንገድ እየቀጠለ መምጣት፣ በትክክልም ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የመጣ ስለመሆኑ ያሳየናል፡፡
በተለይ የግብርና ምርታችንን ለማጓጓዝ በኪሎ ሜትርና በኩንታል እየተሠላ የሚጠየቀው ዋጋና ነዳጅ በጨመረ ቁጥር የሚከተለው የዋጋ ጭማሪ በመርህ ላይ የተመሠረተና ኢኮኖሚያዊ በሆነ መንገድ የማይሠራ በመሆኑ ገበያውን በእጅጉ እየጎዳው ነው፡፡
ዛሬ ዜጎችን በእጅጉ እየፈተነ ያለው የዋጋ ንረት ብዙ ሰበቦች ያሉት ቢሆንም፣ እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ የዋጋ ጭማሪዎችም የነበራቸው አስተዋጽኦ ከሚገመተው በላይ ስለመሆኑ በቅጡ ያልተፈተሸ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ የሚያስችል አሠራር ባለመዘርጋቱ ችግሩን ይዘን እየተጓዝን ነው፡፡
መንግሥት ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ እንደሚያወጣ በማሳወቅ የነዳጅ ገበያ የዓለም ዋጋን መሠረት በማድረግ የሚሸጥ በመሆኑ በተደጋጋሚ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ስለሚደረግ፣ ይህንን በማሳሰብ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ አደጋ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሻቀበ ያለው የነዳጅ ዋጋ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ጉዳዮች በእጅጉ የሚያሳስብ ይሆናል፡፡
ስለዚህ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር በኢትዮጵያ የችርቻሮ ዋጋው ላይ ጭማሪ ሲደረግ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን የተገናዘበ የዋጋ ጭማሪዎች እንደ እስካሁኑ በዘፈቀደ መካሄድ እንደሌለባቸው አምኖ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መፍትሔ ሊሆን የሚያስችል አሠራር የመዘርጋትና ቁጥጥር ማድረግ ግድ ይሆናል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሚያስፈልገው ተፅዕኖ ግልጽ ቢሆንም፣ ተፅዕኖ የከፋ እንዳይሆን አስቻይ የሆነ ሥራዎች ጎን ለጎን ሊሠሩ ይገባል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም ዋጋ ጭማሪውን ሲያደርግ ቅንነት የተሞላው ቢሆን ግን፣ ነገሮችን ቀላል ሊያደርግ እንደሚችልም ማመን መልካም ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መንግሥትም ቢሆን እጁን በማስገባት በነፃ ገበያ ስም እየተደረገ ያለውን አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አደብ ሊያስገዛ ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ከሰሞኑ በራሳቸው በመንገድ እያደረጉ ያለው የዋጋ ጭማሪ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌትር 5 ብር ነዳጅ ስለጨመረ በአንዳንድ መስመሮች ላይ 20 ብር ሲያስከፍሉ የነበረውን ዋጋ 25 ብር፣ 25 ብር ሲያስከፍሉ የነበረውን ደግሞ 30 ብር አድርገዋል፡፡
ለዚህም ከኃይሌ ጋርመንት መገናኛና ከኃይሌ ጋርመንት ቦሌ ባለው የጉዞ መስመርን በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወትሮም ቢሆን ከኃይሌ ጋርመንት መገናኛ ድረስ ትክክለኛ ታሪፍ ተብሎ የወጣው ዋጋ 17 ብር ነው፡፡ ነገር ግን 25 ብር እየተከፈለበት ነበር፡፡ አሁን ደግም በሰሞኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተሳብቦ በአንድ ጊዜ 5 ብር ጨምሮ 30 ብር ደርሷል፡፡ ይህም የዋጋ ጭማሪ በትክክል ዋጋ ጭማሪውን ያገናዘበ አይደለም፡፡
በአንድ ሌትር ላይ አምስት ብር ጭማሪ ተደረገ ማለት በአንድ የጉዞ መስመር ላይ በአንድ ሌትር የሚደርስ ከሆነ ጭማሪውን በተሳፋሪ ልክ ካሰብን ሊደረግ ይገባ የነበው ጭማሪ በሳንቲሞች ደረጃ መሆን እንደነበረበት እንረዳለን፡፡ እያንዳንዱ ተሳፋሪ የሚከፍለው ተጨማሪ ገንዘብ እጅግ የተጋነነ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ ላልተገባና የታክስ ዋጋ ጭማሪ መባባስ ደግሞ በትክክል ቢተገበርም ባይተገበርም የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል ታሪፍ ማውጣት ያለበት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ወዲያው ታሪፍ እያወጣ ያለመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በትራንስፖርት ዘርፉም ይህንን በግብይት ሥርዓት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን በማሳበብ የሚደረጉ ዋጋ ጭማሪዎች ሕግና ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በተለይ የዕቃ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ በጨመረ ቁጥር የሚያወጡ ታሪፍ ምን ያህል አግባብ መሆን አለመሆኑን በሚገባ መፈተሽ የችግሩን ግዝፈት ያሳያል፣ ለመፍትሔም ያግዛል፡፡