Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ በ2015 በጀት ዓመት ስምንት ሺሕ ለሚጠጉ ጀማሪ ቢዝነስ ተቋማት ብድር መስጠቱን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአነስተኛ፣ ጥቃቅንና መካከኛ የቢዝነስ ተቋማቶች የሚሰጠውን ብድር ለማሳደግ የእየሠራ መሆኑን የገለጸው አዋሽ ባንክ፣ በ2015 በጀት ብቻ ከ7,800 በላይ ለሚሆኑ ተበዳሪዎችም ብድር መስጠቱን አስታውቋል፡፡

አዋሽ ባንክ ‹‹ታታሪዎቹ›› እና ‹‹ቀጠሌዋን›› በሚል የሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ከወለድ ነፃ ብድር ለመስጠት የሚያስችለውን ሁለተኛውን ውድድር መጀመሩን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ወቅት በተለያዩ መንገዶች ለአነስተኛ፣ መካከለኛና የቢዝነስ ዘርፎች የሚሰጠውን ብድር ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ በፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹትም፣ ‹‹በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ብድር ማግኘት የሚችሉ ዋስትና ያላቸው በብዛት በከተማ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ አዋሽ ባንክ ይህንን ክፍተት ከግምት በማስገባት ለአነስተኛ ቢዝነሶች የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት ከከተማ ወጣ ባሉ የክልል ከተሞች ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ በአብዛኛው ብድር እየቀረበ ያለው ለብድር ዋስትና ማቅረብ በሚችሉ ከተማ አካባቢዎች በመሆኑ፣ ዋስትና ካላቸውና ከከተማ አካባቢ ወጥቶ ወደ ገጠሩ ክፍል፣ በተለይም ጥቃቅን የቢዝነስ ዘርፎችን ለመድረስ አቋም በመያዝ ወደ ትግበራ ገብተናልም ብለዋል፡፡ 

ይህንን የባንኩን ዓላማ ለማሳካት አንዱና ዋነኛው ታታሪዎቹና ቀጠሌዋን በሚል ለሥራ ፈጣሪዎች ባለፈው ዓመት የጀመረው የሽልማት ፕሮግራም ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ ለአሸናፊዎቹ ሽልማትና ብድር መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ቢዝነሶች ላይ በሰፊው ባንኮች ገብተው መሥራት ያለባቸው ጭምር መሆኑን ለማሳየት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡    

‹‹አዋሽ ባንክ በጥቃቅንና አነስተኛ ቢዝነሶች አካባቢ በሰፊው ለመድረስ በተለያየ መልኩ እየሠራ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ፀሐይ፣ ከዚህ መካከል ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በጥምረት በመሥራት እስከ አምስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር በማመቻቸት እየተሠራበት መሆኑ አንድ ማሳያ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ ወደ አምስት ለሚሆኑ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋሞች ብድር በመልቀቅ እነርሱ ደግሞ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላሉ ጥቃቅንና አነስተኛ የቢዝነስ ዘርፎች ብድር ማቅረብ እንዲችሉ እየተደረገም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ባንኩ ጥቃቅን፣ አነስተኛ መካከለኛ የቢዝነስ ዘርፎች ከመድረስ አኳያ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ለአነስተኛና ጥቃቅን የቢዝነስ ዘርፎች እየሰጠ ያለው ብድር የተበዳሪዎችን ቁጥር እያሳደገ እንዲመጣ አስችሏል፡፡ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በጥምረት እየተሠራ ባለው ሥራም ባለፈው 2015 በጀት ዓመት ብቻ ከ7,800 ጥቃቅንና አነስተኛ ቢዝነሶች ከአዋሽ ባንክ ብድር ማግኘታቸውን ከአቶ ፀሐይ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

ባንኩ ለአነስተኛና ለጥቃቅን ቢዝነሶች እየሰጠ ያለው አገልግሎት እየሰፋ በመምጣቱና ውጤታማ መሆን በመቻሉም በቅርቡ በህንድ ኒው ደይሊ ዋና ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ቢዝነሶች ጉባዔ ላይ ለአነስተኛ የቢዝነስ ተቋማትን በመደገፍ በማቅረብ በአፍሪካ ደረጃ  ተሸላሚ ከሆኑ ባንኮች መካከል አንዱ ሊሆን እንደቻለም ገልጸዋል፡፡

የታታሪዎቹና ቀጠሌዋን የሥራ ፈጠራ ውድድር ራስን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻልም፣ ፈርስት ኮንሰልታንት የተባለ አማካሪ በመቅጠር እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ፀሐይ፣ ፕሮግራሙም በየዓመቱ በቋሚነት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ 

በመጀመርያው ዙር አሸናፊ ለሆኑት የፈጠራ ሥራዎች ቢዝነሶች ባንኩ በገባው ቃል መሠረት ሽልማትና ከወለድ ነፃ ብድር በማቅረብ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ባንኩ አሸናፊ ለሆኑት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ውጤት ከ100 ሺሕ ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት ሰጥቷል፡፡ ይህም በሁለቱም ዘርፎች ለየብቻ የተሰጠ ነው፡፡ ለአሸናፊ ፕሮጀክቶቻቸውም እስከ 5 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ብድር እንዲመቻችላቸው ተደርጓል፡፡  

እንዲህ ያሉ እውነቶች አነስተኛ ቢዝነሶች ከባንክ ብድር ማግኘት እንደሚቻል መንገድ ማሳያ የሚሆንም እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሁሉም ተባብሮ ጥቃቅን ሥራዎች ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በማገዝ፣ ወደ ባንክ እንዲመጡና ብድር ብናመቻች ለአገርም ሆነ ለባንኮቹ ዕድገት ያመጣል የሚል እምነት ያላቸው መሆኑንም አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡ ለባንኮች ተደራሽነትም ቢሆን ከአነስተኛ ቢዝነሶች ጋር መሥራት ጠቃሚ ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በ2015 የታታሪዎቹ የሽልማት ፕሮግራሞችን በተመለከተ የፈርስት ኮንሰልታንቲንግ ተወካይ አቶ ሚካኤል አዲሱ፣ ይህ ፕሮጀክት በአገር ደረጃ ያለውንም ጥቅም በማየት፣ ሌሎች ተቋማትም እንደ ቤስት ፕራክቲስ እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ጭምር እየተተገበረ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

በ2015 በተጀመረው የመጀመርያው ዙር ውድድር ለአሸናፊዎች በተገባው ቃል መሠረት ያለ ዋስትና ብድር እንዲመቻችላቸው የተደረገ ሲሆን፣ ከመጀመርያው ዙር የተገኘውን ተሞክሮ በመያዝ ሁለተኛው ዙር በተሻለ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ 

የቢዝነስ ሐሳብ ኖሯቸው ግን ፋይናንስ ማግኘት ያልቻሉ ገበያ ዕድል ያጡትን በተለይ በአብዛኛው የፈጠራ ሥራ አመንጪዎች በመሆን የሚጠቀሱ ወጣቶችን የሚያግዝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የ35 ዓመት በታች ዕድሜ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ከ80 በመቶ በላይ በመሆኑ፣ ይህንን ግሩፕ መድረስ እንዲህ ዓይነቱ ፕሮጀክት መንገድ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ በአብዛኛው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት፣ ሙያው ኖሯቸው  የቢዝነስና ፋይናንስ ዕውቀት የላቸውና የገበያ ኔትዎርክ የሌላቸው ስለነበሩ፣ በውድድሩ ሦስትና አራት ዙር እያለፉ ሲሄዱ፣ እነዚህ ችግሮቻቸውን በሚሰጣቸው ሽልማት ለመቅረፍ ማስቻሉንም አቶ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

በመጀመርያው ዙር ውድድር ለመወዳደር የቀረቡ ተሳታፊዎች ቁጥር ከ7,300 በላይ ነበሩ፡፡ ከዚህ ውስጥ 52 በመቶ ከአዲስ አበባ ያመለከቱ ሲሆን፣ ይህን ቁጥር ለማስተባበር የሚሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

በዘንድሮ ውድድርም ከዚህ በላይ የሚጠበቅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ሁለተኛው ዙር የሥራ ፈጠራ ተወዳዳሪዎች ከጥቅምት 12 እስከ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ማመልከቻቸውን ማስገባት ይኖባቸዋል፡፡ አዋሽ ባንክ በተለያዩ አፈጻጸሞቹ በኢትዮጵያ በቀዳሚት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም ከ11 ቢሊዮን ብር ባላይ ማትረፉ መጠቀሱ ይታወሳል፡፡ 

ባንኩ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አጠቃላይ ቅርንጫፎችን ቁጥር ከ850 በላይ አደርሷል፡፡ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ደግሞ ከ10 ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች