አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ማኅበሩ በአዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀጽ 57 ድንጋጌ መሠረት የተቋቋመና ሥራ ከመረጀ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘ የሙያ ማኅበር ነው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ካገኙ በኋላ፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በፌዴራል ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ቀደም ብሎ ልደታ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ተብሎ በተቋቋመው ልዩ የዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ የከባድ ችሎት ማለትም ከ15 ዓመታት ፅኑ እስራት እስከ ሞት ሊያስቀጡ የሚችሉ የወንጀል ክሶችን በዓቃቤ ሕግነት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በተቋሙ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሲሠሩ ቆይተው በ2006 ዓ.ም. የዓቃቤ ሕግ ሥራቸውን በማቆም ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የጥብቅና ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ከጥብቅና ሥራቸው በተጨማሪ ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሕግ አማካሪነት ይሠራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ውስጥም በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው፣ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ሁሉንም የፌዴራል ጠበቆች በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ከተመሠረተ በኋላ በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ በከፍተኛ ድምፅ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ተጣባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. በደቡብ ዛምቢያ ሊቪንግስተን ከተማ በተደረገ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባዔ ላይ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በአጠቃላይ ለ16 ዓመታት በዓቃቤ ሕግነትና በጥብቅና አገልግለዋል፡፡ ሰሞኑን ማኅበራቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣሪያና የግድግዳ ግብርን አስመልክቶ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ጥናት በማድረግ፣ የሕግ ክፍተት አለበት ባለው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ በመሆኑም አስተዳደሩ ስላደረገው ጥናትና ማኅበሩም ስላገኘው ክፍተት፣ እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ታምሩ ጽጌ ከአቶ ቴዎድሮስ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የአፍሪካ የጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ከ21 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) ሲመሠረት፣ አቶ ጌታቸው ቅጣው ጸሐፊ ሆነው ተመርጠው ለአራት ዓመታት መሥራታቸው ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ላለፉት 18 ዓመታት ኢትዮጵያ አባል ከመሆን ባለፈ በአመራር ደረጃ መሳተፍ ሳትችል ቆይታለች፡፡ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ውስጥ በምዕራብ ዛምቢያ ሊቪንግስተን ከተማ በተካሄደ ጉባዔ ላይ እርስዎ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆን ተመርጠዋል፡፡ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት እንዴት እንደተቋቋመና የተቋቋመበትን ዓላማ ቢያብራሩልኝ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ላለፉት 21 ዓመታት ራሱን እያሳደገ ያለ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ በአኅጉሩ መሪ የሕግ ተቋምም ነው፡፡ 56ቱንም የአፍሪካ አገሮች ጠበቆች ማኅበራትን በአባልነት የያዘ ተቋም ነው፡፡ ከአገሮቹም በተጨማሪ ስምንት የሪጅን ተቋማት ማለትም ‹‹East Africa Law Society›› (ከ28,000 በላይ አባላት ያሉትና ሰባት አገሮችን በአባልነት ያቀፈና በምሥራቅ አፍሪካ መሪ ተቋም ነው)፣ ‹‹Southern African Development Community (SADC)) እና ሌሎቹም አባል የሆኑበት ማኅበር ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ1,100 በላይ የክብርና መደበኛ አባላት ያሉት ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ማኅበሩ በአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ያለውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) አጀንዳዎች ጭምር ምክክር የሚደረግበት ተቋምም ነው፡፡ ወደ ውጭ አገሮች የሸሹ ንብረቶችን ለማስመለስ (Asset Recovery) የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ማኅበሩ በሚያካሂዳቸው ጉባዔዎች ላይ አገሮች በተወካዮቻቸው አማካይነት አጀንዳዎቻቸውን በመላክ ስሜታቸውና ፍላጎታቸው እንዲሰማ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ፍልስጤምን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የማኅበሩ ምሥረታ አዲስ አበባ የተደረገው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ተሰሚነት አንፃር ማለትም በዓድዋ ያገኘችው ድል፣ በቅኝ ገዥዎች አለመገዛቷ፣ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት በመሆኗና የአፍሪካ ኅብረትንም የመሠረተች አባል አገር በመሆኗ፣ ማኅበሩ አዲስ አበባ ላይ እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ዋና መሥሪያ ቤቱን ማቆየት ባለመቻላችን ወደ ታንዛኒያ ሊሄድ ችሏል፡፡ ማኅበሩን ከመሠረቱ ጉምቱ የሕግ ባለሙያዎች መካከል ታዋቂዎቹ ጠበቆች አቶ ጌታቸው ቅጣውና አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁ ይገኙበታል፡፡ እንደገለጽከው ምንም እንኳን መሥራች ብንሆንም፣ ለ18 ዓመታት በየትኛውም የአመራርነት ቦታ ላይ ውክልና ሊኖረን ቀርቶ፣ በተሳትፎ ደረጃ እንኳን ምንም ነገር አልነበረንም፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደው ጉባዔ ላይ እንድንሳተፍ የጋበዘን ‹‹East Africa Law Society›› ነው፡፡ በምርጫው ሒደት ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለ18 ዓመታት ምንም ተሳትፎ አልነበረንም፡፡ አዘጋጇ ዛምቢያ አጀንዳ እንዲያድር አድርጋና ሌሎች አገሮችም አግዘውን ወደ ከፍተኛ አመራርነት ልንመጣ ችለናል፡፡ ነገር ግን ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከመካከለኛው አፍሪካና ከዌስት አፍሪካ (ከእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ) ከፍተኛ ድምፅ አግኝተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው? በተለየ የሚጠቅማት ነገር አለ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- የመጀመርያው ጥቅም የአገር መወከል (Symbolic) ነው፡፡ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረትን ከሚመሩት ጥቂት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አንዱ መሆኑ፣ ምንም እንኳን አዲስ ቢሆንም ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ አገርን ለማስተዋወቅና የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን በተለያዩ ሁኔታዎች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ማኅበራት ከለላ እንዲያገኙ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በአምባገነን መንግሥታት የሚጠቁ አባላት ካሉ የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ በተወሰነ መልኩ የአገር ውስጥ ሕግ በማይነካ ሁኔታ ባለሙያዎች በአኅጉሩ እንዲሠሩ ሁኔታዎችንም ያመቻቻል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በአዋጅ ቁጥር 1249/2013 በአንቀጽ 57 ድንጋጌ መሠረት ተመሥርቷል፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተው በ2010 ዓ.ም. በተደረገ አገራዊ አመራር ለውጥን ተከትሎ በተደረገው የሕግ ማሻሻል (Legal Reform) በመደረጉ ነው፡፡ በሕግ ማሻሻያ ሒደት ነባር ሕጎች ሙሉ በሙሉ ተቀይረው እንደ አዲስ የተደነገጉና የተሻሻሉ ሕጎችም አሉ፡፡ ሕግ ማሻሻያው ቀደም ብሎ የነበሩ የሕግ ጥሰቶችንና የፍትሕ መዛባቶችን አስተካክሏል ብለው ያምናሉ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ማኅበራችን ከተቋቋመ ገና የአንድ ዓመት ተኩል ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ እኛ ወደ ኃላፊነት ስንመጣ የተረከብነው ወረቀት ነው፡፡ በሌጋል ሪፎርሙ የተሻሻሉና እንደ አዲስ የወጡ ሕጎች እጅግ በጣም ጥሩ ሕጎች ቢሆኑም፣ ወደ መሬት ለማውረድ ተቋም መፍጠር ያስፈልግ ነበር፡፡ በመሆኑም የተቋም ግንባታው ላይ ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ነበር፡፡ ይህም ማለት አንድ ተቋም ሊሠራባቸው የሚያስፈልጉ ደንቦችና መመርያዎች እንዲረቀቁ ተደርጓል፡፡ ወደ ሥራ የገቡና በሒደት ላይ ያሉም አሉ፡፡ ሌለው ማኅበሩ ሲሠራ የቆየው በጠበቆች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠበቆች እነማን ናቸው? ስንት ጠበቆች አሉ? የሚለውን ጥያቄ ምላሽ መስጠት ግድ ይል ነበር፡፡ ማኅበሩ ሥራውን ለመጀመር አባላቱን ቀድሞ ማወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም በመላው አገሪቱ ያሉትንና የፌዴራል የጥብቅና ፈቃድ ያላቸውን ጠበቆች የመመዝገብ ሒደት አከናውነናል፡፡ መረጃዎችን በዘመናዊ መልክ የማደራጀት ሥራ ሠርተናል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙን ሙሉና ብቃት ያለው አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሰው ኃይል ምልመላና ቅጥርም ሌላው ሥራ ነበር፡፡ ማኅበሩ ነፃ ሆኖ በራሱ እንዲንቀሳቀስ፣ የራሱን በጀት ማዘጋጀት አለበት፡፡ ይህንንም በጀት የመፍጠር ግዴታ ስለነበረብን ይህንንም ስንሠራ ነበር፡፡ ዋና ገቢያችንን መሰብሰብ ሳንጀምር ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችል የፋይናንስ አቅም መፍጠር እየቻልን ነው፡፡ አባላቱን በማስተዳደር ረገድ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን እየገነባን ነው፡፡ ሜምበርስ ማኔጅመንት ሲስተም (ኤምኤምኤስ) እየገነባን ነው፡፡ ለአንድ ተቋም የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች በሙሉ ከዜሮ ጀምረን እያጠናቀቅን እንገኛለን፡፡ ጎን ለጎን ግን ማኅበሩ የሚጠበቅበትን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በሳምንት፣ አንዳንድ ጊዜም በቀን 40 እና 50 አቤቱታ ይቀርባል፣ ለዚህ ምላሽ መስጠት አለብን፡፡ የአገልግሎት ጥያቄው በጣም ብዙ ነው፡፡ ማኅበሩ ከ5,000 በላይ አባላት ስላሉት፣ በጠበቆቻችን ላይ የሚደርሱ የመብት ጥያቄዎች አሉ፡፡ መከታተልና መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሰው መብት ሊያስከብሩ ሄደው የታሰሩ ጠበቆች ነበሩ፡፡ እነሱን ማስፈታትና በሕዝቡ የሚቀርበውን በርካታ አቤቱታና ቅሬታ ምላሽ መስጠትም የማኅበሩ የዕለት ከዕለት ሥራ ነው፡፡ ተቋሙ አንደ አዲስ ሳይሆን አቤቱታ ተቀብሎ ምላሽ የመስጠት ብቃቱ ከፍ ያለ ተቋም ነው፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በርካታ ግንኙነትም እያደረግን ነው፡፡ የአሠራር ግንኙታችንን እያጠናከርን ነው፡፡ አባሎቻችንን ለምርጫ ቦርድ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ድረስ በመላክ ዕገዛ አድርገናል፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑንም እየረዳን ነው፡፡ ከፓርላማው የሕግ ክለሳዎችን በሚመለከት የሚመጡ ጥያቄዎችም ላይ የሙያ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ውስጥ ማኅበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የጣሪያና ግድግዳ ግብር እንዲከፍሉ በአፈ ቀላጤ (በደብዳቤ) የውሳኔ ሐሳብ ማስተላለፉን አስመልክቶ በውሳኔው ላይ ጥናት አጥንታችሁ ማብራሪያ እንዲሰጣችሁ ጠይቃችኋል፡፡ እስኪ ስለዝርዝር ጉዳዩ ያብራሩልን?
አቶ ቴዎድሮስ፡- እኛ እንደ ማኅበር ከተማ አስተዳደሩ ባስተላለፈው የጣሪያና የግድግዳ ታክስ ክፍያ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ጥናት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይህኛው ብዙ የሕዝብ ጥያቄ ስላለበት ገኖ ወጣ እንጂ፣ ሌሎችም ብዙ ጉዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉና የማስረጃ ሕጉ ጥናት በጣም ሰፊና በርካታ አባላቶቻችን የተሳተፉበት ጥናት ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ፣ ባለበት መፅደቅ እንደሌለበት በመግለጽ ተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብና ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ፣ ትኩረት እንዲደረግበት በማድረግ ከ490 በላይ አንቀጾችን የያዘና የዜጎችን መብት ሊያስጠብቅ የሚችል ሕግ እንዲሆን በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ የሙያ ማኅበራት ዋናውና አንዱ ተግባራቸው በሕጎች ላይ ጥናት መሥራትና የተሻለ ሕግ እንዲወጣ መርዳት ነው፡፡ ጥራት ያለው ሕግ ኖሮ የተሻለና ዜጎች የሚረኩበት አፈጻጸም እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ማኅበሩ የሠራው ትልቁ ጉዳይ ጠበቆችን የሚመለከተው የታክስ ጉዳይ ነው፡፡ ለ20 ዓመታት ሲንከባለል የቆየን የታክስ ጉዳይ አዲስ ነን ብለን ወደኋላ ሳንል በድፍረት ገብተንበት፣ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ማኅበራችን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር በጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ለስድስት ወራት ጥናት በማድረግ፣ በታክስ ሥርዓት ላይ ያለውን ችግር፣ ከስምንት የውጭ አገሮች ልምድን መውሰድን ጥናቱን አቅርበናል፡፡ ለቀጣይም እየሠራን ነው፡፡ አተገባበሩን እየተከታተልን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ ባስተላለፈው ሰርኩላር ጠበቆች ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ክፍያ እንዲጀምሩ ያለው ከጥናታችሁ ውጪ ነው ማለት ነው?
አቶ ቴዎድሮስ፡- በተጻፈው ደብዳቤ ወይም ሠርኩላር ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል የሚል እምነት የለንም፣ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ ቋሚ የሆነና ወጥ የሆነ መመርያ የማይወጣ ከሆነ፣ የታክስ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ስለታክስ ሥርዓት በተደረገው ጥናት የተገኙ ግኝቶች በጣም መሠረታዊ ናቸው፡፡ የታክስ ሥርዓት መዘመን አለበት፡፡ ተዓማኒና ዘላቂ መሆንም አለበት፡፡ አዲስ ነገር ሲመጣ የሚደነግጥ መሆን የለበትም፡፡ ሕጉን በማሻሻል መመለስ የሚችሉ አሉ፡፡ በመመርያም የሚያስተካከሉ አሉ፡፡ ይህንንም የአጭርና የረዥም ጊዜ በሚል ከፋፍለን እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የጥብቅና ሥራ የሙያ ሥራ እንጂ የንግድ ሥራ ባለመሆኑ፣ ታክስ ክፈሉ ልንባል አይገባም የሚሉ የሕግ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ማኅበሩ ይህንን አይቀበለውም፡፡ ጠበቆች እንደ ማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት አለባቸው፡፡ እንኳን ጠበቆች የተማሩት ቀርቶ ማንኛውም ዜጋ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ታክስ መክፈል አለበት፡፡ ሁሉም ማለት ባይቻልም፣ አብዛኛዎቹ ጠበቆች ይህንን የሚረዱ ይመስለኛል፡፡ እኛ አገር ወደ ሲስተም የገባውንና ሥርዓት የተከተለውን መቀጥቀጥ ይበዛል፡፡ እንዲያውም ወደ ሥርዓት እንዲገባ ማበረታታት አለባቸው፡፡ እንደ ሙያ ማኅበረሰብም ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ማድረግ የሚገባውን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ጥያቄው የሕጎች የመስተካከል ጥያቄ ነው፡፡፡ እውነት ነው ጠበቆች ነጋዴዎች አይደሉም፡፡ ጠበቆች ለሕዝብ የማይታዩ የሚሠሯቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በዓመት እስከ ሦስት ጉዳዮች ያለ ክፍያ በነፃ እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን የትኛውም ነጋዴ ነው ‹‹ከምትሸጠው ሸቀጥ ወይም ሌላ ንግድ ላይ 30 በመቶውን በነፃ ሽጥ›› የምንለው? የጥብቅና የሙያ ዘርፍ ግን ጥብቅ ክትትል የሚደረግበት ነው፡፡ ሌላው በጥብቅና የሚገኝ ገንዘብ ጣሪያው የተወሰነ ነው፡፡ ማንም ነጋዴ ገዥ እስካገኘ ድረስ በፈለገው ዋጋ እንዳይሸጥ የሚያስገድደው የለም፡፡ ከቫትም ሆነ ከቲኦቲ ጋር በተያያዘ በርካታ አማራጮችን አቅርበናል፡፡ ወደ ፊት በሕግ የበላይነት ላይ ተፅዕኖ እንዳያመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል ያሉ ተከራካሪ አካላት ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና የስለላ ተቋማት ከፍተኛ ጡንቻ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ ነው አንድ ተከሳሽ የሚከላከለው፡፡ በጠበቃ የማይወከል ከሆነ ክርክሩ ተመጣጣኝነት ያጣል፡፡ የመብት ጉዳይ፣ የቀለብ ጉዳይ፣ የቤተሰብ ጉዳይ፣ በጠበቃ ካልታገዘ ፍትሕ ይጓደላል፡፡
ሪፖርተር፡- ከላይ ያብራሩልን የማኅበሩ የሥራ ክንውኖች ሰፊና ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት መሆናቸውን ነው፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ላይ (በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ) ከፍተኛ ቁጣን፣ ብሶትንና መማረርን ስላስከተለው የጣሪያና ግድግዳ የግብር ክፍያ ጉዳይ ስላጠናችሁት ጥናትና ለከተማ አስተዳደሩ ስላቀረባችሁት የማብራሪያ ጥያቄ ቢያስረዱን?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ከተማ አስተዳደሩ አስተላልፌያለሁ ያለው ውሳኔ የግብር ማሻሻያ ውሳኔ ነው፡፡ ይህንን የግብር ማሻሻያ ውሳኔ እንደ ማንኛውም ሕዝብ የሰማነው ከመገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ በኋላ ስለጉዳዩ ለማወቅ ክትትል አድርገናል፡፡ መረጃዎችን አሰባስበን ስንመረምር አስተዳደሩ ለውሳኔ መነሻ ያደረገው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ወጥቶ እስካሁን ያልተሻረውን አዋጅ ቁጥር 80/1968 ድንጋጌዎችን ነው፡፡ እኛም ውሳኔውን ከአራት ዋና ዋና ነጥቦች አንፃር ስናጠናው ቆይተናል፡፡ የመጀመርያው ነጥብ የቤት ግብርን ለማሻሻል፣ ለመደንገግና ለመወሰን ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት አካል ማነው? የሚል ነው፡፡ ይህንን ያነሳነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ግብር የሚወሰነው በአግባቡና ከምንጩ ጋር ተጠንቶ መሆን እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ (100) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ አግባብ የቤት ግብር የሚወሰነው ‹‹ቤቱ ቢከራይ ምን ያህል ይሆናል?›› የሚለውን ግምት በመውሰድ ነው፡፡ ከመሬት ተነስቶ ግብር አይወሰንም፡፡ ይህንን ደግሞ የያዘው የከተማ ቦታ ኪራይና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የግብር ውሳኔ የሰጠው የአዋጅ ቁጥር 80/1968 ድንጋጌን መነሻ አድርጎ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለዚህ አዋጅ ቁጥር 80/1968 ስላልተሻረ በሥራ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ተፈጻሚነቱም ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 6(2) ድንጋጌን ብንመለከት፣ የቤት ግብር መጠን፣ በቤቱ ኪራይ ግምት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለዚህ በአዋጁ አንቀጽ 6 (3) እና (4) ድንጋጌ መሠረት የቤት ኪራይን ለመወሰን ሥልጣን ያለው አካል በወቅቱ የሥራና የቤት ሚኒስትር የሚባለው ነው፡፡ በኋላ በተደረጉ ማሻሻያዎች ደግሞ የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስትር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 80/1968 አንቀጽ 19 (1) መሠረት የተሻሻለው በደርግ አገዛዝ ወቅት በአዋጅ ቁጥር 161/71 ሲሆን፣ አዳዲስ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ሲታይ ግን የከተማ ቤትን ኪራይ መጠንና ግብርን ለመወሰን ሥልጣን የተሰጠው የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አስተዳደሩ በቀላጤ ውሳኔ ያስተላለፈው አዋጅ ቁጥር 80/68 ባልተሻረበት በሕገወጥ መንገድ ነው ማለት ነው?
አቶ ቴዎድሮስ፡- አሁን የጠየቅነው ማብራሪያ ነው፡፡ አቋም አልያዝንም፡፡ በጥናታችን ያገኘነውን ክፍተት አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጠን ነው፡፡ ግብር የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ፣ የከተማ አስተዳደሩ የተሻሻለውን ግብር ወስኛለሁ ብሎ ያስታወቀው፣ በፋይናንስ ቢሮ ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ንብረትና ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በኩል ነው፡፡ ይህ ለአንድ የፌዴራል ተቋም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተሰጠን ሥልጣን በምን ሁኔታ እንደወሰደ ማብረሪያ ጠይቀናል፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር ተቋማት ሊተኩ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በሕግ አግባብ እንጂ በዘፈቀደ ሊሆን አይገባም፡፡ ሌላው አስተዳደሩ የፈጠረው ክፍተት ደንብ ከማውጣት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ተስተካክሎ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 161/1971 አንቀጽ 2 (2) ድንጋጌን ብንመለከት፣ አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ነው፡፡ ደንቡን ማውጣትም ግዴታም ነው፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠው ለሕገ መንግሥቱ ሆኖ፣ ቀጥሎ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው መውጣት አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ አስተዳደሩ ሕጋዊ ወራሽ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ደንብ አላወጣም፡፡ ይህንን ባላደረገበት ሁኔታ በቀላጤ (ደብዳቤ) ነው ውሳኔ መወሰኑን ያስታወቀው፡፡ ይህ ትልቅ ክፍተት ነው፣ ያሳስባልም፡፡ ሥልጣን አለኝ የሚል ከሆነ (አስተዳደሩ) ቅድሚያ ማውጣት ያለበት በከተማው ሕግ አውጪ አካል በኩል ተመክሮበት ደንብ መውጣት ነበረበት፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጊቱ ከአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ድንጋጌ አንፃር እንዴት ይታያል? አዋጁን የጣሰ አይደለም?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ትክክል ነህ፡፡ አዋጁንም በጣም የጣሰ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በቀጥታ አባሎቻችን ከተሳተፉበትና እንዲፀድቅ ከፍተኛ ጫና ካደረግንባቸው አዋጆች አንዱ ነው፡፡ በሪፎሙ ከወጡ ከ11 በላይ አዋጆች ውስጥ አብዛኛው ላይ የማኅበሩ አባላት በቀጥታ ተሳትፈዋል፡፡ የዚህ አገር የሕግ ሥርዓት ያሻሽላሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው አዋጆችም አንዱ የጠቀስከው የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ነው፡፡ አዋጁ ለአስፈጻሚ የመንግሥት አካላት ልጓም የሚሆን ወሳኝ አዋጅም ነው፡፡ አገር ወደ ዴሞክራሲ፣ ወደ ተሟላ የሕግ የበላይነት እንድትሄድ ከተፈለገ ይህ አዋጅ ዋናውና ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አዋጅ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት መመርያ የሚወጣበት መንገድ አለው፡፡ ማን ያረቀዋል? ከተረቀቀ በኋላ እንዴት ለውይይት ይቀርባል? ለአስተያየት ክፍት የሚሆነው መቼ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችን የሚመልስ አዋጁ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ነው አስተዳደሩ ያስተላለፈው ውሳኔ ይህንን የተከተለ አካሄድ መሆን አለመሆኑን ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ የመጨረሻው ነጥባችን፣ አስተደደሩ ያስተላለፈው ውሳኔ የቤት ግብር ከአዋጅ ቁጥር 80/68፣ እንዲሁም አዋጁን ተከትሎ የወጣውን ደንብ የማሻሻል ይዘት ያለው ይመስላል ያልነው፡፡ መታወቅ ያለበት ከሕገ መንግሥት ጀምሮ ሕግ ሲወጣ የሚከተላቸው ሒደቶች አሉ፡፡ አዋጅ ከወጣ በኋላ ደንብ ይወጣል፡፡ ቀጥሎም መመርያ ይወጣል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ በፋይናንስ ቢሮ በኩል በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ያስተላለፈው የውሳኔ ደብዳቤ ነው፡፡ በደብዳቤ አዋጅን ለማሻሻል የተደረገ ውሳኔ ይመስላል፡፡ ለማሳያ ያህል እኛ ደንብ ብለን በጥቄያችን ላይ የጠቀስነው የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 36/68ን ነው፡፡ በ1968 ዓ.ም. የወጣውን ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 80/68ን ለማስፈጸም ስለተደነገገው ስለዚህ ደንብ አስተዳደሩ የጠቀሰው ምንም ነገር የለም፡፡ በዝምታ ነው ያለፈው፡፡ ቀደም ብዬ በጠቀስኩ የሕግ ማስታወቂያ ቁጥር 36/68 አንቀጽ 6(2) መሠረት ማንኛውም ሰው በባለቤነት ለያዘው ቤት ግብሩን በየዓመቱ በሰንጠረዘዥ (3) መሠረት ይከፍላል ነው የሚለው፡፡ ሰንጠርዥ 3 የያዘውን ዝርዝር ስንመለከት ደግሞ፣ የዓመት የቤት ግብር ግምትን በብር የሚዘረዝርና የግብሩን መጠን በመቶኛ ያመለክታል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ግብር የኪራይ መጠንን ያመለክታል፡፡ ሰንጠረዥ 3ም ከዚህን ያህል ኪራይ በመቶኛ ይህንን ያህል ይከፍላል ይላል፡፡ ነገር ግን በቀላጤ (በደብዳቤ) የተላለፈው የአስተዳደሩ ውሳኔ፣ ከኪራይ በተጨማሪ ሌላ መሥፈርቶችን አምጥቷል፡፡ የቁጥር ለውጥም አምጥቷል፡፡ ለምሳሌ 50 ብር ወይም 18 ብር የሚከፍል ሰው 50,000 ብር ወይም 18,000 ብር ተጠይቋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ ያልተደረጉ መሥፈርቶችን ስላመጣ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሥነ ሥርዓት ሕጉ ውጪ አዋጁን በደብዳቤ እየሻረ ነው ማለት ነው፡፡ ሕጎች ከሚከተሉት የገዥነት ተዋረድ ያፈነገጠ አሠራር ነው፡፡ የበታች ሕግ በምንም ሁኔታ የበላይን ሕግ መሻር አይችልም፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይም ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀናል፡፡ በእናት ሕጉ የተሰጠውን አሠራር የጣሰ ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ባደረግነው ጥናት ከላይ በጠቀስኩት ሁኔታ ክፍተት ስላገኘንባቸው ነጥቦች ማብራሪያ ጠይቀናል፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም፣ የአስፈጻሚ አካል፣ የከተማ አስተዳደር ይሁን የፌዴራል አስተዳደር አካል የሚሠራውን የዕለት ከዕለት ሥራውን በሕግ አግባብ ስለመሥራቱ ማረጋገጥ ይኖበታል፡፡ የዴሞክራሲ ሐሳቦች መተግበር የሚችሉት በሕግ መመራት ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ላቀረብናቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አስተዳደሩ የጣሪያና ግድግዳ ግብር እንዲከፈል ያስተላለፈው ውሳኔ በርካታ ነዋሪዎችን ያስጨነቀ፣ አንዳንዱም በሥጋት ያላግባብ ቤቱን እስከመሸጥ የደረሰና ገሚሱ ደግሞ በብድር ለመክፈል ሲሯሯጥ አምስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ አንፃር ጥናታችሁ አልዘገየም?
አቶ ቴዎድሮስ፡- እንደ ተቋም የሚጠና ጥናት በተወሰነ መልኩ ጊዜዎችን መውሰዱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ኃላፊነት የሚወሰድበት በመሆኑ እያንዳንዱን ቀዳዳ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ማኅበሩ በሌሎችም በርካታ ሥራዎች ተወጥሮ ያለ በመሆኑ ጥናቱ ጊዜ ወስዷል፡፡ ይፋ ለማድረግም ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ፡፡ በእርግጥ አንተ እንደጠቀስከው የከፈሉ፣ የተጨነቁና ለመክፈል የሚሯሯጡ አሉ፡፡ አሁንም እስከ የካቲት ይቀጥላል፡፡ በየዓመቱ የሚቀጥል እንጂ የሚቆም አይደለም፡፡ በመሆኑም ጥናቱ ከወሰደው ጊዜና ይፋ ለማድረግም መከናወን ከነበረባቸው ድርጊቶች አንፃር ዘገየ የሚባል አይደለም፡፡ ገና መጀመሩ ከመሆኑ አንፃር አግባብ ነው ብለን ባሰብንበትና ጥናቱ በደረሰልን ጊዜ ጥያቄያችንን አቅርበናል፡፡
ሪፖርተር፡- አስተዳደሩ ያስተላለፈው የግድግዳና ጣሪያ ግብር ክፍያ ወቅታዊ ጉዳዮችን ያላገናዘበ፣ ሕዝቡ ያለበትን የኑሮ ጫናና የመክፈል አቅም ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ እጅግ የተጋነነ ነው የሚል ሮሮ ከሕዝቡ እየተሰማ ነው፡፡ የክፍያ ግምቱ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ለእኛየሚያሳስበን ጉዳይ የክፍያ ግምቱ መጋነን ወይም ማነስ ሳይሆን የሕጋዊነቱ ጉዳይ ነው፡፡ አንተ እንዳልከው በክፍያ መጠኑ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ቀርበዋል፣ እየቀረቡም ነው፡፡ ለምሳሌ ጡረተኞች ሆነው በዓመት 100 ብርና 118 ብር ይከፍሉ የነበሩ ሰዎች፣ በድንገት 30 ሺሕ እና 40 ሺሕ ብር ክፈሉ ቢባሉ፣ ምናልባትም ዓመቱን ሙሉ ከጡረታ የሚያገኙትን ቢያጠራቅሙ ያንን ማሟላት አይችሉም፡፡ ነገር ግን መጠኑ አንድም ብር ሆነ አንድ ሚሊዮን ብር የሕጋዊነት ጥያቄ ግን መሠረታዊ ነው፡፡ ምክንያቱም አገር የምትቆመው በሕግ መመራት ስትችል ብቻ ነው፡፡ እኛም እየመረመርን ያለነው አግባብነቱን ነው፡፡ ውሳኔው አግባብነት አለው ወይ የለውም ለማለት ሕግን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ እኛም ጥያቄ ያነሳነው ከዚያ አንፃር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከግብር ክፍያው መጋነን በተጨማሪ ቤቱን ለሚለካው መሐንዲስም ክፍያ የሚፈጽሙት ባለንብረቶቹ መሆናቸውን በውሳኔው መጠቀሱ ተቀባይነት የሌለውና ሕገወጥ አሠራር ነው የሚሉ አሉ፡፡ የእናንተ ምልከታ ምንድነው?
አቶ ቴዎድሮስ፡- በመሠረቱ በመርህ ደረጃ ግብር መሰብሰብ ያለበት በግብር ሰብሳቢው ወጪ እንጂ በግብር ከፋዩ ወጪ አይደለም፡፡ መንግሥት ግብር የሚሰበስበው፣ መንግሥታዊ ወጪዎችን ለመሸፈን ነው፡፡ በመሆኑም የመሐንዲስም ክፍያ የመንግሥት ወጪ እንጂ የከፋዩ የሚሆንበት አሠራር የለም፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ትክክል ያልሆነና አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ነዋሪው ግብር ይከፍላል እንጂ የመሐንዲስን ደመወዝ ወይም አበል መክፈል የለበትም፡፡ ይህ እንዲያውም ሌሎች ያልተገቡ ተግባራትን ሊያጋልጥ የሚችልም ነው፡፡ እኛም በጥናታችን ያገኘነውና ምላሽ እንዲሰጥበት ያቀረብነው ጥያቄም ጭምር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የመሬት (አፈር) ግብር ለዘመናት እንደ አግባቡ ሲከፈል የኖረ ነው፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ ‹‹የጣሪያና የግድግዳ›› ግብር ክፈሉ የማለቱ አግባብነቱ እንዴት ይታያል?
አቶ ቴዎድሮስ፡- የእኛም የጥያቄያችን አንዱ ነጥብ ይህ ነው፡፡ ተጨማሪ መሥፈርቶች ያልናቸውም እነዚህ ናቸው፡፡ አዋጁ ወይም የበላይ ሕጉ ያላስቀመጣቸውን በተግባር አዋጁን ማሻሻያ የሚመስል ውሳኔ ነው የተላለፈው፡፡ በመሆኑም አስተዳደሩ ከምን መነሻ ይህንን ውሳኔ እንደሰጠ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠይቀናል፡፡ በሕግ ላይ የሌሉ ነገር ግን በውሳኔው ተካተው የቀረቡ አግባብነት የሌላቸውና ከየትኛው የሕግ አግባብነት እንደተወሰዱ የማያሳዩ መሥፈርቶች ናቸው፡፡ አንዳንዱን ነገር ስናየው ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ይመስለናል፡፡ ሕግ ሳይሻሻል ደንብ ወይም መመርያ ሊወጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት የምትከተል አገር በመሆኗ የሥልጣን ክፍፍል ተደርጓል፡፡ መሠራት ያለበት ይህንን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ሕጎች በአግባቡ እስካልተሻሻሉና እስካልተሻሩ ድረስ መከተል ያለብን ነባሩን ሕግ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሥልጣን ክፍፍል ቢኖርና አስተዳደሩም ሥልጣኑ የእሱ እንደሆነ ቢታሰብም፣ ውሳኔውን ያስተላለፈው አዋጅ ቁጥር 80/68 ድንጋጌን መሠረት አድርጎ በመሆኑ አካሄዱ ትክክል አይደለም፡፡ ሥልጣን አለኝ የሚል ከሆነ፣ መሆን ያለበት በሕግ አውጪው ክፍል ሕግ ሆኖ መውጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ያስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ እናጠጋጋው ብንል እንኳን ሊሆን የሚችለው መመርያ ነው፡፡ አዋጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎና ውይይት ተደርጎበት ሕግ ሆኖ ሊፀድቅ ይገባል እንጂ በደብዳቤ ብቻ መወሰን ያለበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ባለሥልጣናት በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ የሚያበረታታ በመሆኑ ሥጋታችን ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ስህተት ከሆነ እንዲስተካከልና እንዳይደገም ነው ጥያቄያችን፡፡ እናት ሕጉ መከበር አለበት፡፡ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ይህንን የሚያስተካክል መሠረታዊ ሕግ ቢሆንም እየተፈጸመ አይደለም፡፡ ሕግን ተከትሎ ግብር መጨመርም ሆነ ሌላ ነገር ማድረግ ሲቻል በዘፈቀደ ብድግ ብሎ የፈለጉትን ማድረግ ውጤቱ መልካም አይሆንም፡፡
ሪፖርተር፡- ባጠናችሁት መሠረት የአስተዳደሩ ውሳኔ ክፍተት አለበት ያላችሁት ላይ ማብሪሪያ እንዲሰጣችሁ ያቀረባችሁት ጥያቄ ምላሽ ቢነፈገው፣ ቀጣይ ዕርምጃችሁ የሚሆነው ምንድነው?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ማኅበሩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የተለያዩ ጫናዎችን ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ ምን ዓይነት ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚቻል ወቅቱ ሲደርስ የምናየው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ክስ ትሄዳላችሁ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- አሁን ላይ ሆነን ምንም ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን ወደ ሕግ መሄድም ሌላው አማራጭ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት የአስተዳደር ለውጥ አድርጎ እየሠራቸው ካሉ ተግባራት አንዱ የሕግ ማሻሻያዎችን (Legal Reform) ማድረግ ቅድሚያ ከሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ የመጀመርያው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕጎች እንደ አዲስ እንዲወጡና የሚሻሻሉትም እንዲሻሻሉ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ሕግ ባለሙያና የሕግ ተቋም እንደሚመራ ኃላፊ በወጡት ሕጎችና በተሻሻሉት ሕጎች የተገኙ ለውጦች አሉ ማለት ይቻላል?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ይህ በጣም ሰፊ ጥያቄ ነው፡፡ በየዘርፉ መታየትና መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ጥቅል ዕይታና መደምደሚያ የሚወስዱ በመሆናቸው ጥያቄውን ለመመለስ ከባድ ነው፡፡ በእኛ በኩል አሁንም ከፍ ባለ ሁኔታ ሕግን የማስከበርና የማስፈጸም ክፍተቶች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸው ቢታወቅም፣ አፈጻጸም ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ከአሥር በላይ በሚሆኑና በተሻሻሉ ሕጎች ላይ የእኛ አባላት ከ80 በመቶ በላይ በሚሆን ደረጃ ተሳትፈዋል፡፡ እጅግ በጣም ጥሩ ሕጎችም ወጥተዋል፣ ተሻሽለዋል፡፡ በተለይ በለውጡ ሁለት ዓመታት ውስጥ በጣም ጥሩ ሕጎች ወጥተዋል፡፡ በፍጥነት የይድረስ ይድረስ እንዳይፀድቁም የተቃወምናቸው ሕጎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም እስካሁንም ገና በሒደት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በደንብ ተከልሶ እንዲስተካከል አድርገናል፡፡ ቋሚ ሕጎች ናቸው፡፡ የፖለቲካ አመራሩ ቢቀያየርም ጠንካራ ሕግና ተቋም ያስፈልጋል፡፡ አገር መቆም ያለበት በሕግ እንጂ በፖለቲካ መሆን የለበትም፡፡ ጥሩ ጥሩ ሕጎች ቢኖሩም አፈጻጸም ላይ ግን በርካታ ክፍተቶች አሉ፡፡ ሕጉን ያወጣው አካል ሕጉን ሲጥስ ይታያል፡፡ ሁሉንም ይፋ ማውጣት ባይቻልም ከተለያዩ አካላት ጋር ትክክል ስላለመሆኑ እንነጋገራለን፣ ዝም አንልም፡፡ በተለይ የሕግ ተቋሞቻችን የማስፈጸም አቋም በጣም ያሳስበናል፡፡ በተለይ የፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና የማረሚያ ቤቶች አፈጻጸም ብቃትና አቅም በጣም ያሳስበናል፡፡ ሕጎች በሚጣሱበትና የዜጎች መብት በግልጽ በሚጣስበት ወቅት ሥልጣን ተሰጥቷቸው ምላሽ የሚሰጡ ተቋማት ማነስ ያሳስበናል፡፡ በዚህች ግዙፍ አገር በሕግ መመራት ካልተቻለ አደጋው ከፍተኛ ነው፡፡ ሁሉንም በሕግ መምራት ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ጥሩ ሕጎች የወጡ ቢሆንም አፈጻጸሙ መስተካከል አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት የማስፈጸም አቅም የሚያጡት ከአመራሩ ብቃትና ቁርጠኝነት ማነስ የተነሳ ነው? ወይስ የፖለቲካ ወገንተኝነት በመኖሩ?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ይህ የብዙ ነገር ድምር ውጤት ይመስለኛል፡፡ አንድ ነገር ማስገንዘብ የምፈልገው ጥሩ ጥሩ ሕጎች ወጥተዋል ቢባልም፣ በሕግ አረቃቀቅ መሠረቶችና መርሆዎች (Legislative Principles) ይመዘኑ ቢባል የጥራት ጉድለት ሊኖር እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ወደ አፈጻጸም ስንመጣ የፈጻሚው ብቻ ሳይሆን ሲስተሙ (ሥርዓቱ) እንዴት ይሠራል? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ተቋማት መታየት አለባቸው፣ ቀጥሎ የፈጻሚው ብቃት ለቦታው የሚመጥንና ክህሎት ያለው መሆኑ መታየት አለበት፡፡ የተሾመበትን ዓላማ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ ሰውን ለማስደሰትና ወገንተኝነት ያለበት ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ የአቅም ግንባታ የሚያስፈልግ ከሆነም የፈረሰውን የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ በግልጽ የሚታዩ ሕጎችን የሚያስፈጽምና አተገባበሮችን የማወቅ ችግር ይታያል፣ መፈታትም አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥትን ከሚያቋቁሙ ሦስት አካላት አንዱ ሕግ ተርጓሚው (Judiciary) ፍርድ ቤት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን ካላቸው የመንግሥትነት ኃላፊነት አንፃር እየሠሩ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ፍርድ ቤት እውነት ነው ከመንግሥት ሦስት ክንፎች አንዱ ነው፣ ግዙፍም ነው፡፡ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ከመሆኑ አንፃር መጀመርያ ማስከበር ያለበት ራሱን ነው፡፡ በተቋሙ የሚሠሩ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችና ዳኞች ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ ከሥራቸው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጠያቂነቶች ካሉም ያንን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ይኼ ካልሆነ ትርጉም የለውም፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜ እየታዩ ያሉ አሠራሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ የፍርድ ቤትን ውሳኔ አናስፈጽምም የሚሉ አስፈጻሚ አካላት (የፖሊስ ተቋማት) አሉ፡፡ ዋስትና የተፈቀደላቸውን ዜጎች ‹‹አንለቅም›› በማለት ታስረው እንዲቆዩ ያደርጋሉ፡፡ ይግባኝ ማለት የሚችለው ተከሳሽ ወይም ተጠርጣሪ ቢሆንም፣ ፖሊስም ‹‹ይግባኝ እጠይቃለሁ›› ይላል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት እዚህ ላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፈቀደውን ዋስትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማገድ የለበትም፡፡ ይኼ ማለት ከፈቀደ የፖሊስን ያልተገባ ሥራ እያገዘ ነው ማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ በአሠራር ይከፋፈሉ እንጂ መዋቅራቸው ወጥና ተመሳሳይ ነው፡፡ መዋቅራቸውም ተመሳሳይ ነው፡፡ የበላይ ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ፖሊስ እንዲፈጽም ማስገደድ አለበት፡፡ የፈታበትን ማስረጃ ተቀብሎ መዝገብ መክፈት ካለበትም (በሕጉ የተፈቀደ ነገር የለም)፣ ፖሊስ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝን መፈጸሙን አረጋግጦ መሆን አለበት፡፡ ያንን ተግባራዊ ካላደረገ ይኼ ሌላ ጉዳይ ስለሚሆን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ የፍርድ ቤት ነፃነትም በዚያ ልክ መሆን አለበት፡፡ የእኛ ማኅበርም ለፍርድ ቤት፣ ለዓቃቤ ሕግና ተቋማት ነፃነት ይታገላል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፈቀደውን ዋስትና ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያፀድቁት፣ እዚያም የክልል የፀጥታ ተቋማት ይፈለጋል ተብሎ ወደ ክልል የሚወሰድበት ሁኔታ ተፈጥሮ ዓይተናል፡፡ ይህን አካሄድ እንዴት መቅረፍ ይቻላል?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ይህ ግልጽ ነው፡፡ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ማሽሞንሞን ወይም ማለዘብ አያስፈልግም፡፡ የመረረ ነገር ቢሆንም መዋጥ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊስ የሚሠራውን ስህተት ዓቃቤ ሕግ ማረምና ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ምርመራውን መቆጣጠር አለበት፣ መከታተል አለበት፡፡ የምርመራውን ሕጋዊነት የማረጋገጥ ሕጋዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ያ ከሆነ እየተስተካከለ ይመጣል፡፡ ፍርድ ቤትም በተመሳሳይ ከሠራ ማለትም በይግባኝ የሚጠየቅን ዋስትና ከመፍቀዱ በፊት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መፈጸሙን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የፌዴራል ተቋማት በማለት ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ ኮሚሽንና ማረሚያ ቤቶች በጥምረት ኮሚቴ አቋቁመው የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ አካሄድ አሠራሮች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር (Check and Balance) ሒደትን አያደናቅፍም?
አቶ ቴዎድሮስ፡- አንድ ላይ በጥምረት መሥራታቸው ክፋት የለውም፣ ጥቅም አለው፡፡ የሚፈጸመው ስህተትና ጥፋት በግንባር የሚነገርበትና ወዲያውኑ ዕርምት የሚወሰድበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ እኛም አባል በመሆናችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ያሉ ችግሮችን በማንሳት የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ እንሠራለን፡፡ ነፃ ማኅበራት መካተታቸው ጥሩ ነው፡፡ በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚቻለው በዚህ ዓይነት አደረጃጀት ውስጥ በመግባት በመሆኑ፣ የእኛም ማኅበር አባል ሆኖ አብሮ እየሠራ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ በምርመራ ወቅት አብረው መሥራታቸው በተለይ ለተጠርጣሪው ወይም ተከሳሽ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የሚደርሰውን አላግባብ የሆነ የምርመራ ሒደት ያስቀራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሁሉም ተቋማት የራሳቸው የአሠራር ነፃነት አላቸው፡፡ አንዱ በአንዱ አሠራር ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡ በጋራ ሊያሠሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው አብረው የሚሠሩት፡፡ ሰው እነዚህን የፍትሕ አካላት የሚያያቸው እንደ አንድ ነው፡፡ ፖሊስ ጥሩ ሠርቶ ዓቃቤ ሕግ ቢያበላሸው ወይም ፍርድ ቤት ቢያበላሸው ‹‹እዚህ አገር ምን ፍትሕ አለ?›› ነው የሚለው፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ በቅብብል የሚሠሩ በመሆናቸው ነፃነታቸውን ጠብቀው በጋራ ቢሠሩ ክፋት የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ፡፡ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ከፍ ባለ ሁኔታ ግጭቱ ወደ ጦርነት እያደገ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን በገለጸው አማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ነገር ግን በአዋጁ ውስጥ እንደየሁኔታው አዋጁ በመላው የአገሪቱ ክፍል ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚደነግግ አንቀጽ ተካቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያስከትላል የሚሉ አሉ፡፡ ተገቢነቱም ላይ ጥያቄ እየተነሳ ከመሆኑ አንፃር የእናተ ማኅበር አቋም ምንድነው?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በቅርቡ እያየናቸው ካሉ ጉዳዮችና ጥናት እያደረግን ካለንባቸውም ጉዳዮች አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው፡፡ የጥናታችን ውጤት ሲደርስ ይፋ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ግን መርሁን (Principles) ላስቀምጥ፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ፡፡ ‹‹UDHR፣ ICCPR፣ ICESCR›› ወዘተ ኢትዮጵያ የፈረመችባቸውና የምትገደድባቸው ናቸው፡፡ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚናገሩትም አለ፡፡ በሕገ መንግሥቱም የተደነገጉ አሉ፡፡ መርሁ ምንድነው? አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ ከሕጉ አጻጻፍ እስከ አተገባበሩ ድረስ ልዩ (Specific) መሆን አለበት፡፡ ለጉዳዩ ብቻ የተወሰነ መሆን አለበት፡፡ ለሃይላንድ የጀሪካን ክዳን እንደማይሆነው ሁሉ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ለጉዳዩ ብቻ መዋል አለበት፡፡ በጠባቡ መተርጎም (Exceptions) አለበት፡፡ ለአደጋው ብቻ የሚሆንና የሚመጥን መሆን አለበት፡፡ ማኅበራችን ጥናት እያደረገበት በመሆኑ እንዳለቀ ይፋ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች እያደጉ መጥተው ከፋ ወዳለ ጦርነት እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ዜጎች እየተገደሉ፣ ንብረት እየወደመና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ግጭቱ በፈጠረው ተፅዕኖ ማምረት ባለመቻሉ ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ ማኅበራችሁ የሕግ ማኅበር እንደመሆኑና መፍትሔ የመፈለግ ግዴታ ያለበት ከመሆኑ አንፃር ምን እየሠራ ነው? ብዙ ባለሙያዎች (ምሁራን) ስብስብ ከመሆኑ አንፃር በሰላም ዙሪያ እየሠራ ያለው ነገር ካለ ቢገልጹልን?
አቶ ቴዎድሮስ፡- ማኅበሩ ነፃ ተቋም ነው፡፡ በነፃነቱ ላይ አይደራደርም፡፡ ማኅበሩ አዲስ በመሆኑ ልምድም የለውም፡፡ ነገር ግን ከዴሞክራሲ ተቋማት እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር አብረን እየሠራን እየረዳን ነው፡፡ ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ባለሙያዎችን በመመደብ ዕገዛ እያደረግን ነው፡፡ የእኛ አገር ሥርዓት ከዳኝነት ወደ ጥብቅና በመሆኑ፣ ብዙ ልምድ ያላቸው ምሁራን አባሎቻችን ስለሆኑ እንደ ማኅበርም እንደ ዜጋም የተቻለንን እያደረግን ነው፡፡ በአገሪቱ ላይ ያለው ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ የኃይል አማራጭ እንኳን እርስ በርስ ከሌላ አገርም ጋር ቢሆን አስገዳጅ ነገር ከሌለ በስተቀር አይመረጥም፡፡ ልዩነቶችን በንግግር ማጥበብና አገር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መደረግ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ተቋምና ኃላፊ ቆም ብሎ ማሰብና መሥራት አለበት፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው ጦርነት (የሕወሓትና ፌዴራል መንግሥት)ም ያሳጣን ብዙ ነገር ነው፡፡ አሁንም ቆም ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ማኅበር ማድረግ ያለብንን ሁሉ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ የምናወጣቸው መግለጫዎችና ምክር አዘል ሒደቶች ፖለቲካዊ አድርጎ መመልከት መቅረት አለበት፡፡ ከተጻፈው ውጭ የራስን ትርጉም ሰጥቶ ማንበብ መቆም አለበት፡፡ ችግሩ የአገር በሕግ አለመመራት ውጤት በመሆኑ ሁሉም ለሕግ ተገዥ መሆን አለበት፡፡