Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአኞ ትርክቶችን ስለሚያንጎላጭ የቤታችን ድህነት

አኞ ትርክቶችን ስለሚያንጎላጭ የቤታችን ድህነት

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ዘመናችን ነገሮች ፈርጅና ዘርፍ እያበጁ በሠለጠኑ ሙያተኞች የሚጠኑበትና የሚመረመሩበት ነው፡፡ ጥቅሎቹን የጥናት ዘርፎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማኅበራዊ ሳይንስ መስኮች ልንላቸው እንችላለን፣ በእነዚያ ውስጥ ያሉ የዘርፍ ዘርፎች ብዙ ናቸው፡፡ ከጊዜ ጊዜም አዳዲስ ጉጦች ሲያበቅሉ ይታያሉ፡፡ ከየሙያዎቹ ውጪ የሆንን ሰዎች አስተማማኝና በጠበብቱ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መረጃ ስንፈልግ ሙያተኞቹን ወደ መጠየቅ መሄድ የተለመደ ነው፡፡ የሙያተኞች ሥምሪት ከንግድ ጋር እየተቀላቀለና የንግድ ጥቅምን የማገልገልም ፈርጆች እያበጀ (ለምሳሌ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የምርቶቻቸውን ተፈላጊነት በማሳደግ ዓላማ የተቃኙ ሳይንስ ነክ ጥናቶች፣ ሙከራዎችና ቅመማዎች ስለሚያካሂዱ) የባለሙያዎች መረጃና ምክር ስንፈልግ የት መሄድ እንዳለብን ማወቅ ተቀዳሚ ነው፡፡

በዕውቀት ዓለም ውስጥ አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ፣ በተለይም ከዚህ ቀደም የነበረን አመለካከትና አካሄድ የሚቀይሩ የምርምር ውጤቶች ብቅ ሲሉ ወዲያው ተቀባይና ተከታይ አያገኙም፡፡ በሊቃውንት የሚገመገሙበትና ዕርባናቸው የሚፈተሽበት ሥርዓት አለ፡፡ የዚህ ዓይነት ሥርዓት በየአገሩም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታላላቅ አካዴሚዎችና ዩኒቨርሲቲዎች መስተጋብራዊ በሆነ መልክ ይካሄዳል፡፡ አዲስ መጡ የጥናት/የምርምር ውጤት ተገምግሞ እንደ አዲስ ዕውቀት ሊቃውንቱ ከሞላ ጎደል ሲቀበሉት በዩኒቨርሲቲዎችና በአካዴሚዎች ጆርናሎች፣ በጥቅሉ ለንግድ ትርፍ ባልገበሩ ኅትመቶች እየተፍታቱ ይወጣሉ፡፡ ይህንን ሒደት ቀድመውም ሆነ ተከትለው የንግድ መገናኛ ብዙኃን ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እናም ውሎ ስላደረም ሆነ ስለትኩስ የጥናትና የምርምር ጉዳይ መረጃ ስንፈልግም ወደ ዋነኞቹ የሙያው ምንጮች ነው መሄድ ያለብን፡፡ በየሙያው ያሉ አንቱ የተባሉ ሊቃውንቶች በጽሑፍም ሆነ በቃለ መጠይቅ የሚሰጡትን መረጃ ከሙያው ውጪ ያለን ሰዎች ለመቀበል አዕምሯችን አነሰም በዛ ፈቃደኛ ነው፡፡ ምክንያቱም በየመስኩ ያሉ ጉዳዮችን የመመርመርና የመፈታታቱን ተግባር በሥራ ክፍፍል ዘይቤ ለእነዚህ ሙያተኞች ሰጥተናልና፡፡ እናም እነሱ በጥቅሉ የተስማሙበትንና ይበጃል ያሉትን እንቀበላለን፡፡ በጤና ዘርፍ አድርጉ ያሉንን ለመፈጸም አናቅማማም፡፡ ‹‹ውዝግብ አለበት… ገና በእርግጠኝነት የለየለት ነገር የለም፣ ግን-›› የሚሉንንም ከ‹‹ግን›› ጋር ለመገንዘብ እንጥራለን፡፡ ተገንዝበንም የተጣራና የተሻለ የምርምር ውጤት ባለሙያዎቹ አስኪያመጡልን እንጠብቃለን፡፡ የሊቃውንቱ መንበር የተጣራ ወይም ይበልጥ ውጤታማ የምርምር ግኝት መጣ ሲለን ደግሞ፣ በተባልነው መሠረት ዕውቀታችንን፣ አስተሳሰባችንንና አኗኗራችንን እናድሳለን፡፡

በተፈጥሮ ሳይንስም ሆና በማኅበራዊ ሳይንስ መስክ መርሁ ያው ነው፡፡ በተለመደው የቤተ ዕውቀቶች የሥራ ክፍፍል መሠረት የማኅበራዊ ጉዳዮቻችንም ጥናት ለሙያተኞች ተደልድለዋል፡፡ በዚያ ሙያ ያሉ ሊቃውንት የተከናወኑና አጠቃላይ ተቀባይነት በሙያተኞቹ ያገኙ ሥራዎችን ዕውቀት ብለን እንቀበላለን፡፡ ‹‹ክፍተቶች ያሉባቸው/አከራካሪ›› የተባሉትንም በዚያው ልክ ለማጤን እንሞክራለን፣ መሞከርም ይጠበቅብናል፡፡

እንደዚያም ሆኖ፣ በተፈጥሮ ሳይንስና በማኅበራዊ ሳይንስ መስኮች ውስጥ በጥናት ትልምና ሥነ ዘዴ በጥቅልም ሆነ ከዘርፍ ዘርፍ ጉልህ ልዩነቶች አሉ፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ምልከታዊ መረጃ ለቅሞና አደራጀቶ ከሚተረጉም ጥናት አንስቶ እስከ ቤተ ሙከራዊ ፍተሻና ፍልሰፋ ሊሄድ የሚችል ምርምር አለ፡፡ በማኅበራዊ ሳይንስ ውስጥ በተፈጥሮ ሳይንስ እንደሚታወቅ ያለ ቤተ ሙከራዊ ፍተሻና ፍልሰፋ የለም፡፡ ሆኖም ማኅበራዊ ሳይንስ ከተፈጥሮ ሳይንስ ሥነ ዘዴ ብዙ ነገሮችን ይቀዳል፡፡ አንዳንዴም ቤተ ሙከራዊ መሰል አካሄዶችን ሲጠቀም ይታያል፡፡ ማኅበራዊ ሳይንስ ነባራዊ ለመሆን ቢጣጣርም ለስሜታዊነት፣ ለወገናዊነትና ለርዕዮተ ዓለም ፈተናዎች የተጋለጠ ነው፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ፀኑ የተባሉ ቲዎሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ሁሉ አሮጌ ቅራቅንቦ ሊያደርግ የሚችል አዲስ ግኝትና ፍልሰፍ ሲመጣ አመራረቶችና ሳይንሳዊ/ዘመናዊ ሲባሉ የቆዩ አሠራሮች ሁሉ መናወጥ ይደርስባቸዋል፡፡ አዕምሮዎች ጥያቄ በጥያቄ መሆን ውስጥ ይገባሉ፡፡ በሥነ ሕይወት፣ በፊዚክስ፣ በሥነ ምድር፣ በአርኪዮሎጂ፣ ወዘተ መስክ የሚመጡ አዳዲስ ግኝቶችና ፍልሰፋዎች ስለሰው ልጅ ምንነት ከቀደምት እስካሁን ያለንን ግንዛቤ ሊያናጉና እመርታ ውስጥ እስከ መክተት ተፅዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ፡፡ በማኅበራዊ ሳይንስ ረገድ ማኅበራዊ ‹‹ባህርያት››፣ ማኅበራዊ ቲዎሪዎች/‹‹ሕግጋት›› የሚባሉትን ሁሉ ጥያቄ ውስጥ በመክተት ንውጠት የሚፈጥሩት የሥርዓተ ኑሮና የሥርዓተ አመለካከት ለውጦች ናቸው ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡ ሊብራል ልውጠት በኢኮኖሚ፣ በፍልስፍና፣ በፖለቲካና በባህል ሕይወትነት ሥጋና ደም አበጅቶ በመጣበት ጊዜ ማኅበራዊ ግንዛቤዎች ምርምርና ጥናቶችም ሥር ነቀል ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ማርክሳዊ አስተሳሰብ ዓለማዊ ለውጥ ለማምጣት ባደረገው እንቅስቃሴም ብዙ ልክ ሲባሉ የነበሩ ነገሮች ጥያቄ ውስጥ ገብተዋል፣ ፉርሽ ተብለዋል፡፡

በ1966 አብዮትና ‹‹አብዮተኛነት›› ሒደት፤ ከዚህ ቀደም ልክ ናቸው ተብለው ሲነገሩንና ስንማራቸው የነበሩ ታሪክና ኅብረተሰብ ነክ፣ ሥነ ልቦናና አስተሳሰብ ነክ ግንዛቤዎች ተተችተዋል፡፡ ‹‹አድኃሪ፣  ፊውዳላዊ፣ ከበርቴያዊ፣ ኢምፔሪያሊስታዊ…›› እየተባሉ ተብጠልጥለዋል፡፡ ከእነዚያ በተቃራኒም ‹‹ተራማጅ/አብዮታዊ›› የተባሉ ጭራሽ ‹‹ሳይንሳዊ›› የተባሉም አስተሳሰቦች ነበሩ፡፡ በማኅበራዊ አብዮት ጊዜ ማኅበራዊ ሳይንሶችም መናወጣቸው ብዙ እስበቶቻቸው ጥያቄ ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከማኅበራዊ ሳይንስ ውስጥ በአዲስ አመለካከት አዲስ ትንታኔ የሚሰጡ ሊቃውንት ፈጥነው እስካልመጡ ድረስም አወቅን ያለ ጥራዝ ነጠቅ ሁሉ ተቺ ለመሆን ይደፍራል፡፡ በ1960ዎች አብዮታዊነት ጊዜ የኢትዮጵያን የታሪክ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሥዕልና የማኅበራዊ ኑሮ፣ ወዘተ ሥራዎችን በአድሃሪና ተራማጅ ዕይታ ለመሥፈር የደፈረው አብዮተኛ ነኝ ባይ ጥቂት አልነበረም፡፡ በሥራቸው ስም ያበጁ ሰዎችን (እንደ አፈወርቅ ተክሌና ፀጋዬ ገብረ መድኅን ያሉትን) ለማጣጣል ያላፈረ ጮርቃነትም ተከስቷል፡፡ ጮርቃዎች/ጥራዝ ነጠቆች (ከአፍ ቃራሚዎች ጭምር) አዋቂ መስለን ይህን ያህል የምንዳፈረው የነባር ሊቃውንቶቻችንን ተሰሚነት የሚያናጋ ማኅበራዊ ቀውስ ሲመጣ፣ ከሙያው ቤት ውስጥ ክፍተት የሚደፍንና ሃይ ባይ ስናጣ፤ ከእኛ በላይ የለም ብለን ሁሉን ስንንቅ፣ ሊቆችና ሙያተኞች በተለያየ ምክንያት ዝም ሲሉና ከጊዜ ጋር ተራምደው ቁንፅልፅል አወቅን ባይነትን አልፈው ከፊት መሆን ሳይችሉ ሲቀሩ ነው፡፡ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ወደ እዚህ ከኅብረ ብሔራዊ ተራማጅነት ወደ ብሔርተኝነት መንሸራተት ከመደረጉ በቀር ክፍተቱ ዛሬም ድረስ እንዳለ ነው፡፡

ያለፈባቸውን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ የታሪክ ክስተቶችና የሚኖርባቸውን አሁናዊ እውነታዎች በትክክል ያልተረዳ ትውልድ በፖለቲካ ጉዞው መንገድ ከመሳትና ለውድቀት ከመዳረግ አደጋ ጋር ይገናኛል፡፡ የ1960ዎች ትውልድ አንዱ ሁነኛ ችግሩ ይህ ነበር፡፡ በጊዜው ወጣቱን በተራማጅ እንቅስቃሴ የነቀነቁት ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሥራዎች ብዙ ውስብስብ ነገሮችን የመረመሩና የበረበሩ ቢሆንም፣ የእኛ የአብዛኞቻችን ቃሪያ ተራማጅነት የወሰደው ብዙ ነገሮችን አቃሎና የማረኩትን ያህል ቦጭቆ ነበር፡፡ ‹‹እስከ ዛሬ ያለው የሰው ልጅ ታሪክ የመደቦች ታሪክ፣ የበዝባዥና የተበዝባዥ፣ የጨቋኝና የተጨቋኝ ታሪክ ነው›› የምትል የተቃለለች ግንዛቤ የብዙዎቻችን አዕምሮ የቃኘችና የጠረዘች ግንዛቤ ነበረች፡፡ ታሪካችንን/ኑሯችንን ስንመረምር አዕምሯችን የሚያነፈንፈው በጨቋኝና ተጨቋኝ የሚፈረጁ ነገሮችን በመልቀም ላይ ነበር፡፡ የጨቋኝ ተጨቋኝ/የበዝባዥ ተበዝባዥ አስተሳሰብ ከብሔርተኝነት ጋር ሲገናኝ ደግሞ በዳይነትና ተበዳይነት ለየብሔረሰቦች ታደላቸው፡፡

ኅብረ ብሔራዊ ፖለቲከኞች ሲሰባበሩ ብሔር/ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ የጭቆናና የተጨቋኝነት አስተሳሰብ ‹‹የትግል›› ሜዳውን ለብቻው መያዝም ቻለ፡፡ ብሔርተኞቹ ታሪክን ከመረዳት ይልቅ ታሪክን ብሔርተኛ አደረጉት፡፡ ታሪክ ቂም መቃረሚያና ማደራጂያ ማሳ ሆነ፡፡ ነፃነት ከመነጠል ጋር አንድ ተደርጎ ታሰበናም ‹‹ታሪክ›› ለመነጠል ተገቢ ማመካኛ እንዲወልድ እየተደረገ ተጠቃ፡፡ በፊት በፊት፣ ከብሔር ጋር የተያያዘው የበደል ትርክት ከበደል ጋር ስሙ በተነሳው ብሔረሰብ ውስጥ ያለ ገዥ መደብን የሚመለከትና ተራውን ሕዝብ የእኛው ብጤ ተጨቋኝ የሚል ነበር፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን ልዩነት ማድረጉ ማገጠና አሠላለፎች ድንግዝግዛቸው ወጣ፡፡ በተለይ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ድል በኋላ የመጣው ከአፍ በታች የነበር አተያይና አያያዝ ገዥንም ተራ ሕዝብንም ያሳከረ ነበር፡፡ አዲሱን ገዥ ቡድን የተቀናቀነ ተሬ ሁሉ ‹‹የብሔር ጠላት›› ያህል ይታይና በትር ይቀመስ ነበር፡፡ የሕወሓት ዋና ገዥነት ከተናጋ በኋላ ደግሞ ከጅምላ ፍረጃ አልፎ ጥላቻና ቂምን መዝራት፣ ብሔረሰባዊ ማንነት የሚያበሻቅጥ ስድብ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መለዋወጥና በጭካኔና በጥላቻ የተሞላ የደቦ ጥቃት በንፁኃን ላይ (በአዛውንትና ሕፃናት ላይ ሳይቀር) እስከ ማድረስ መዝቀጥ የሚኮራበት ፖለቲካና የትግል ሥልት ሆነ፡፡ ይኼውና እንዲህ ላለው ለታጋይ ነን ባዮች የዝቅጠት ተግባር ሕዝብ በመከራና በደሙ ዋጋ መክፈሉን ቀጥሏል እስካሁን፡፡

ይህንን ያህል ዓመታት ውሎ ካደረ መሪር ልምድ ተምሮ ለመታረም ፖለቲከኞቻችን የምር ፍላጎት አላቸው? ያጠራጥራል፡፡ በአፍ ሁሉም መፍትሔው በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው ይላል፡፡ ንግግር ስለመሞካከሩም ከጊዜ ጊዜ እንሰማለን፡፡ ግን፣ ጉዳዩ በተገናተሩ አቋሞች መሀል ውይይታዊ ልፊያ የማካሄድ ነገር አይደለም፡፡ የእንነጋገር ሁለመና እምብርት ከእንግዲህስ የሕዝቦቻችን አበሳና ሞት ይብቃ! ለሕዝብ ዕፎይታ ሲባል የማንጥለው ጠመንጃ፣ የማንጥለው የፍጥጫ አቋም፣ የማንታረቀው ሰው የለም የሚል ዝግጁነት መፈጠሩ ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ ቁርጠኛ ዕርምጃ ለመውሰድ የደረሰ አንድም ፖለቲከኛ አልታየም፡፡ ቁም ስቅል የሚያዩ ማኅበረሰቦቻችንም ‹‹ስለእናንተ ነው የምንታገለው›› የሚሏቸውን ቡድኖች ሀቀኝነት በዚህ መመዘኛ ገና መመዘን አልቻሉም፡፡

ዛሬም ብሔርተኛ ነን በሚሉና ብሔርተኛ አይደለንም በሚሉ ጎራዎች ዘንድ ታሪክ የፖለቲካ መፋጠጫ መሣሪያ እንደሆነ ነው፡፡ የታሪክ አረዳዳችን ተቸግሮ የቆየው በፖለቲካ ፍጥጫ ምክንያት ብቻ ግን አይደለም፡፡ ‹‹ማን ሊታዘበኝ! ማን ሊያሳጣኝ!›› ባይነትን ያደፋፈረ ክፍተትም ችግሩን እያገዘ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ ፖለቲካችን ሲያኝካቸው ከቆዩት የቦተለኩና የጦዙ ትርክቶች ባሻገር አዳዲስም እየመጡ ነው፡፡ የ1960ዎች ትውልዶች ‹በ‹‹ሸ›› እና በ‹‹ቸ›› የተጣሉ፣ እግዜርን በመካድ ራሳቸውንም፣ መጪውንም ትውልድ ለሰማይ ቁጣ የዳረጉ› የሚል መሳዩ ፍርድ ገና ያበቃላቸው አይመስልም፡፡ በዓድዋ ድል ያሸነፍናቸውን አውሮፓውያን በማርክሲዝም ሌኒንዝም በኩል እንደማቀፍ አድርጎ የቀድሞውን ርዕዮተ ዓለማዊ መጥለቅለቅ መግለጽ የባሰበት ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ የሚጎዳውም ያለፈውን ትውልድ ሳይሆን አሁን ያለውን የአገራችንን አዕምሮ ዕውናዊ የመሆን አቅም ነው፡፡ የ19ኛውን ሁለተኛ አጋማሽ ቀዳማዊ መትቢያውና ማኮብኮቢያው አድርጎ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሌላ የአብርሆት እንቅስቃሴ በመፍጠር ደረጃ ዓለምን ነቅንቆ ከነበረው ማክርሳዊ ሌኒናዊ የአስተሳሰብና የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማምለጥ እጅግ በጣም ከባድ ይሆንባቸው እንደነበር ለማስተዋል መቻል፣ ሌሎች ዓለማዊና አገራዊ ጉዳዮችን በትክክል የማጤን አቅም የማጎልበት ልምድ አካል ነው፡፡ በዘመናችን የዓለም ታሪክ ውስጥ የማርክሲዝም ሌኒንዝም እንቅስቃሴ የፈጠረው አብዮት የዓለማችን ሕይወትና አስተሳሰብ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡

ማርክሲዝም ምዕራብ በቀል መሆኑን ተመርኩዞ ማርክሲዝምን መቀበልንና በአገራዊ ለውጥ መመርያነት ለመያዝ መሞከርን ለአውሮፓውያን የበላይነት እጅ ከመስጠት ጋር ማገናኘት፣ ማርክሲዝምን አማኒ ባለመሆኑ ሙላውን ቅርጫት ውስጥ ከመወረወር አላዋቂነት እጅግም አይለይም፡፡ ቅድሚያ ነገር የዚያ ዓይነት አንድምታዊ አተረጓጎም የሰው ልጆች የጥበብና የዕውቀት ሀብቶች በድንበሮች በማይገደብ መቀዳዳት የተሞላ ከመሆኑ ጋር ይጋጫል፡፡ ክርስትናና እስልምናን ከመካከለኛው ምሥራቅ መቀበል የመካከለኛው ምሥራቆች ተቀጥላ ለመሆን ግድ እንደማይዳርግ ሁሉ፣ በማርክሲዝም የተመራ የሥርዓተ ማኅበር ለውጥ ለማድረግ መሞከር የአውሮፓውያንን አቅኝነት ወዶ መቀበል ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ ከዚያም በላይ፣ ማርክሲዝም የሰው ልጆች ከማንኛውም በደል እንደምን ይገላገላሉ የሚል ጥያቄን ለመመለስ ሲል፣ የሰው አኗኗር ሥርዓቶችን፣ በተለይም ካፒታሊዝምን የጥናቱ መሠረት አድርጎ የማኅበራዊ ለውጥ ፈሮችን ለመረዳትና ለማስረዳት የሞከረ አስተሳሰብ መሆኑም የአቅኝዎች ርዕዮተ ዓለም ለመሆን የማይመች ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ማርክሳዊ ሌኒናዊነትና ሶሻሊስታዊ ትብብር የምጥመጣ ግንኙነት መሠወሪያ አልተደረገም ማለት አይደለም፡፡ ወደ መዝባሪነት የዘቀጠው የሶቪየት ኅብረት ኃያልነት የዚሁ ምሳሌ ነበር፡፡

በእኛም አገር የደርግ ‹‹ማርክሲስትነትና ሶሻሊስትነት›› የዚሁ አብነት ነበር፡፡ እኩልነት፣ ፀረ ጭቆናነትና ፀረ ምዝበራነት የምጥመጣና የክርን ሥራ ‹‹መሰወሪያ››› ለምድ ሲሆኑ፣ እንደ ዘይትና ውኃ አልላላስ የሚል ተራክቧቸው የሚፈጥረው የመሸዋወድ ቴአትር ቧልታይ አስቂኝነት ያለው ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚታየው ‹‹ቀኝ ግራ›› የተባለ ቧልታይ ስላቅ በግነት ዘይቤ እያጎላ የሚያንፀባርቀው የደርግን ዘመነ ‹‹አብዮተኛነት›› ብቻ ሳይሆን፣ በእነ ሶቪየት ኅብረት የነበረውንም ቅጥ አምባር አልባ እውነታ ነው፡፡ የስላቅ በትሩ የሚያርፈውም ማርክሲዝም ላይ አይደለም፡፡ በኦና ማርክሳዊነት/አብዮተኛነትና በአሮጌነት መሀል፣ አፋዊ አንጋሬው በሚንኳኳ ሶሻሊስትነትና ከአፋዊው አንጋሬ ሥር በሚስለከለከው ራስ ወዳድነት መሀል፣ በአፋዊ ነፃነትና በአምባገነናዊ አዝረጥርጥነት መሀል፣ በአፋዊ ኢዓማኒነትና በአማኒ ነፍስ መሀል ያሉ ልፊያዎች የሚፈጥሯቸው ጅልና ጮካ መሙለጭለጮች ላይ ነው፡፡ በ‹‹ቀኝ ግራ/ግራ ቀኝ›› ላይ የምናገኛቸው ባለ ታሪኮች (ከአንቀጥቃጩ ዳኛ አንስቶ እስከ ዓቃቤ ሕግ፣ የተከላካይ ጠበቃና ተከሳሽ ድረስ) የፍርኃትና የአምባገነንነት መጫወቻ የሆኑ ነፍሶች ናቸው፡፡ የተፋለሰ ሰብዕናቸውን (አድራጎታቸውን) እየታዘብን ስንንከተከት የምንታዘበው የትናንቶቹን ሰዎችና ኑሯቸውን ብቻ አይደለም፡፡ የምንታዘበው የራሳችንንም በመጀነን/በዜንጦነት፣ ወዘተ የተለበጠ የዛሬ እበላ ባይነትን፣ ሙልጭልጭነትንና ቶስቷሳነት ጭምር ነው፡፡

ፈጠራዊው ሥራ፣ በትናንትናና በዛሬ ገመናችን እየሳቅን እንድናፍርና ከዚያ ዓይነት የተዋረደ ሰብዕና ለመውጣት እንድንደፍር ይቆነጥጠናል፣ የጌታ ፊት እያየን ምላሳችንንና ግብራችንን ለመቀያየር የማንገደድበት (ሰብዓዊ ክብርን፣ መብትን፣ በራስ መተማመንን፣ በሀቀኛ ሥራ መተማመንን የሚንከባከብ፣ በደልና ጥቃትን የሚከላከል፣ በደልና ጥቃት የፈጽሙም ከግለሰብ እስከ ቡድንና መንግሥት ድረስ ተከሳሽና ተጠያቂ የሚሆኑበት) ሥርዓት እንድንገነባ ይጎተጉተናል፡፡ በዚህ አቅጣጫ መፍጨርጨርም ማርክሳዊ ተራማጅነት ለሰው ልጅ ሃርነት (ኢማንሲፔሽን) ካደረገው ትግል ጋር አይጋጭም፡፡ የከሸፈው ሌኒናዊው የተግባር ሙከራና የዛሬ ዓለማዊ እውነታ የሚነግረን የያኔው ሙከራ ብዙ የነባራዊና የህሊናዊ ተስማሚ ሰበዞች (ቴክኖሎጂን ጨምሮ) ባልለሙበት አፈር ላይ የተደረገ እንደነበር እንጂ፣ በዚህ ዓለም ላይ በዳይና ተበዳይ/ሀብታምና ድሃ ሁሌም እንደማይጠፉ አይደለም፡፡

ማርክሳዊ አስተሳሰብና እንቅስቃሴው የተረሳ ነገር ይምሰል እንጂ፣ ማርክሳዊ ሌኒናዊነት ካነሳሳው ፍትሐዊ ሥርዓት የመፍጠር ዓለማዊ ማዕበል ወዲያ የእሱን ግዝፈት የሚወዳደርም ሆነ የሚያደበዝዝ ሌላ እንቅስቃሴ አልመጣም፡፡ ዓለም የደነበዘ በሚመስል ደረጃ ባዶ ሆኖ የቆየውን ሥፍራ የሞላ ሌላ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ታመነም ተካደም ማርክሳዊ ዲያሌክቲካዊ አስተሳሰብና አተናተን በፍልስፍና በሎጂክ፣ በኅብረተሰብ ሳይንሶች ያደረጋቸው አስተዋፅኦዎች እንዳልነበር የሚታለፉም አይደሉም፡፡ ዛሬ በስካንድኔቪያን አገሮች አካባቢ የምናየው ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ካፒታሊስታዊነት በሶሻሊስታዊ ፍትሐዊነት የተከተበበት ነው፡፡ ከዚህ አካባቢ የተወሰነ ትምህርት ወስደን፣ ‹‹ለሶሻል ዴሞክራሲ/ለማኅበራዊ ፍትሕ እንሠራለን›› ስንልም በተዘዋዋሪ ከማርክሳዊ/ሶሻሊስታዊ ትሩፋት መቋደሳችን ነው፡፡ በ1960ዎች አብዮታዊ ትግል ጊዜ ማርክሲዝምን ቀማምሰን የነበርንም ከማርክሲዝም ስንለያይ ዱሮ የነበርንበት ህሊና ውስጥ ተመልሶ ሳፊ በሳፊ መግባት አልተቻለንም፡፡ አወቅነውም አላወቅነው የተወሰነ የማርክሲዝም እንጥፍጣፊ በውስጣችን መቅረቱ አልቀረም፡፡ ዛሬ የእነ ማርክስን የእነ አነቶኒዮ ግራምሺን የመሳሰሉ ሥራዎችን ያልበረበሩ የፍልስፍና፣ የኢኮኖሚ፣ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ አምባዎችና ሊቆች ብዙ ነገር ይቀርባቸዋል፡፡

የምድራችንና የሰው ልጅ የዛሬ ደኅንነት፣ የመላውን ዓለም ለዓለም አቀፋዊ የታረመ አኗኗር መታገልን እየጠየቀ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ አብዮቱ ዓለምን የመለወጥ ዕምቅ አቅሙ እነማርክስ ከተነበዩት ‹ኦቶሜሽን› የትናየት የመጠቀ ከመሆኑ በላይ፣ እነሱ እንደ ገመቱት ወደፊት የሰው ልጆች የኑሮ ሃርነት የማይቀር መሆኑን እያመላከተ ይገኛል፡፡ አመላካችነቱም መጪው የሰው ሃርነት፣ በጉልበትና በአዕምሮ ሥራዎች መካከል ያለውን የሥራ ክፍፍል እስከ ማክሰም የሚሄድ መሆኑን በዝምታ እስከ መናገር የረዘመ ነው፡፡ የሰው ልጅ ማድረግ የሚገባውን ሳያደርግ ራሱንና ምድርን ካላጠፋ በስተቀር፣ በሁሉም የሥራ መስኮች ውስጥ እየተሰማራ ያለው ሮቦታዊ ‹‹አሳቢነት‹‹ ሰዎችን ሥራ አጥነት ውስጥ የሚከት ሳይሆን፣ በውድም ሆነ በግድ የሰው ልጆችን ምርምር — ማሻሻል — ፍልሰፋ ወዳለበት ነፃነት የሚወስድ ነው፡፡

ከላይ ያልኩት ከማርክሳዊው/ሶሻሊስታዊው ታላቅ እንቅስቃሴ በኋላ ሌላ ዓለም አቀፋዊ ንጠት የፈጠረ እንቅስቃሴ አለመኖሩ እውነት ቢሆንም፣ ከትናንትናው በላይ እጅግ ዓለምን ያጥለቀለቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ጅምር ግን እየተንተከተከ ነው፡፡ እንትክትኩ ኃይል እያከማቸ ነው፡፡ እንትክትኩ የተሳለጠ (ፍትሐዊና ጤናማ) ዓለምን የሚጠይቅ ነው፡፡ እንደ በፊቱ በአንድ አገር ወይም በተወሰኑ አገሮች ውስጥ የተሳለጠ ህልውናን ጀምሬ ማስፋፋት እችላለሁ ለሚል ቅዠት መንገድ የሚሰጥም አይደለም፡፡ ለውጡ ዓለም አቀፋዊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሊፈጥር የሚችለውም የማትመም አቅም ከበፊቱ እጅግ፣ እጅግ ብርቱና ፈጣን ሊሆን የሚችል ነው፡፡

ይህ ዕምቅ ኃያልነቱም ከሁለት ቅንብሮች የሚመጣ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሥርዓት ለውጡ በታጠቀ ኃይል መጨፋጨፍ/ማፈንዳት፣ ማውደም ያለበት ትግል የማይሻ ነው፤ እከሌ የሚባል ርዕዮተ ዓለምም የማይሻ ነው፣ (ሁሉንም ርዕዮተ ዓለሞች አንድ ላይ ደልዞ በሰው ልጅ የሞትና የሽረት ጥያቄ የዓለም ሕዝቦችን/አያሌ መደቦችን የሚያስተባብር ነው)፡፡ ይህ ጥያቄ ‹‹የሰው ልጆችንና ምድራችንን ከመጥፋት እናድን›› የሚል የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ጥያቄ ውስጥ ትናንት የተከሰቱ የፍትሕ ማዕበሎች ያነሷቸው ጥያቄዎች የህልውና ጥያቄ ሆነው ታዝለዋል፡፡ የለውጡ ሞገድ ኃያልነት የሚያገኝበት ሌላው ምንጭ፣ እንቅስቃሴው ሰዎች ምድርንና ሰውን ለማትረፍ የሚታገሉ ሰዎችን ለማበራከት ከሚያካሂዱት ቅስቀሳ የበለጠ የትናየት ጉልበት ያለው ነባራዊ የቅስቀሳ አቅም እየጎለበተ መምጣቱ ነው፡፡ ይህ ቅስቀሳ የሚካሄደው የሰው ልጅ በጥፋት ሥራዎቹ ከሚያስከትለው የሥነ ምኅዳር መቃወስ በሚመነጩ ቅጣቶች አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ ቅጣቶች በጎርፍ በድርቅ/በሐሩርነት መስፋፋት፣ ወዘተ፣ ወዘተ እየመረሩና እየከፉ ገና ይመጣሉ፡፡ መራራ የህልውና ቅጣታቸው የሚፈጥረው ዓለማዊ የቀቢፀ ተስፋ መርበድበድና ቁጣ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡

ይህንን ያህል ትናንትናችንን፣ ዛሬያችንንና ነጋችንችን አያይዘን ያለ ጠባብ አድሎኛነት ለመረዳት መሞከር መልሶ የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፤ አመለካከታችንን ዕውናዊ፣ ሚዛናዊና ስል ስናደርግ የምንጠቅመው ለተሻለ ሕይወት የምናካሂደውን ትግል ነው፡፡ በዚህ የአስተሳሰብ ፈር ውስጥ ለመቆየት የሚጣጣር አዕምሮ፣ የ1960ዎችን ወጣቶች ተራማጅ እንቅስቃሴ የፈለገውን ያህል በድክመትና በጥፋቶች ቢወቅስም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ለአዲስ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት መሠረታዊና አስፈላጊ የነበረውን የመሬት ሥሪት ለውጥ በማዋለድ ረገድ ትውልዱ ያለውን ታሪካዊ ሥፍራ ቁልጭ አድርጎ ለማሳየት አይሰስትም፡፡ የዚህ ዓይነት ሰፊ አስተዋይነት መበርከት፣ በፋሽስት ጣሊያን ጊዜ የውስጥ አርበኝነት ሚና ያልነበረውን የጣሊያን ደጋፊ የነበረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ‹‹ባንዳ›› ብሎ በጥቅል ከመደምደም ለመራቅ ያግዘናል፡፡ በጣሊያን ገዥነት በኩል የኢትዮጵያን መልማት የጓጉ ሰዎች እንደነበሩ/ሳይኖሩ እንዳልቀሩ ለማየት ክፍት የሆኑ አዕምሮች በውስጣችን መበርከት፣ ወደ 20ኛ ክፍለ ዘመን መባቻ ጊዜ ፈቀቅ ብሎ በጃፓን መንገድ ለውጥን የፈለጉትን የዝመና ናፋቂዎችን በአግባቡ ለመረዳትም አቅም ይሆነናል፡፡ እናም ከግለሰብ ግለሰብ በዘመኑ የነበረውን የለውጥ ፍላጎቶች መዝጎርጎር ትተን፣ በጥቅሉ ተይዞ የነበረው የጃፓን መንገድ በጊዜው ከነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ አኳያ የመገኘት ዕድል የነበረውን ያህል ለውጥን ለመፈልቀቅ የሞከረ የዕውናዊ ለውጠኝነት አብነት እንደነበር ማስተዋል ቃር አይሆንብንም፡፡ ይህንን ያህል ዕውናዊ ለመሆን የሚጠነቀቁ አዕምሮዎች መበርከት፣ ከዚያ ራቅ ያሉ ዘመኖችንና የታሪክ ጉዳዮቻችንን በአግባቡ ለመረዳትና ለማስረዳት የሚያስችሉ የአዕምሮ ስንቆችን ማፍራትም ማለት ነው፡፡

የቅርብ ጊዜውን የሃምሳ ዓመታት ታሪካችንን በተመለከተ፣ እስካሁን በሰነዘርናቸው የታሪክና የፖለቲካ ግምገማዎቻችን ውስጥ ምን ያህል ስህተት እንደሠራን ማስተዋል ከቻልን፣ መቶና ከዚያ በላይ ዓመታት ወዳለፋቸው የታሪክ ዘመናት ውስጥ ገብተን የምንሰጠው ግምገማ ምን ያህል ለስህተቶች የተጋለጠ እንደሚሆን ለማጤን አቅም ይኖረናል፡፡ እንደዚህ ያለ አቅም ካገኘን ገንተራነትን ለማለዘብ እንችላለን፣ በነካ ነካ ጥናት ፈራጅ ከመሆን መጠንቀቅ እንጀምራለን፡፡ የታሪክ ግምገማን ከተሟላና ከሚዛናዊ የጥናት ሥራ ለማግኘት የሚሹ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ዘመን በራቀ መጠን ልናገኘው የምንችለውም የመረጃ ብቃትና ጥራት ይሳሳል፣ የትንታኔያችንም ትክክለኛነት እየሰለለ ይሄዳል፡፡ እዚህ ድፍን እውነት ላይ ተማምኖ እኔ ብቻ ልክ ከሚል ንቁሪያ መላቀቅ ባልቻልንበትና ወደ ሰላም የመምጣትን አገራዊ ጉጉት ጠመንጃ ተኳሾች አናዳምጥ ባሉበት የአሁን እንቆቅልሻዊ ሁኔታ፣ የእነ ተካልኝ ወልደ ማሪያም (ዶ/ር) ዓይነት የታሪክ ምሁራን ወደፊት መምጣትና በአዲስ ዕይታ የኢትዮጵያን ታሪክና የታሪክ አረዳድ ለመዳሰስ መቻላቸው በጣም ይበጃል፡፡ ከዚሁ ጋር በአሁናዊ ዓለማችን የሕዝቦችና የአገሮች ህልውና በዓለም ደረጃ ተያይዞ ለመፍትሔ መሥራትን የጠየቀ መሆኑን፣ ይህንን ጥያቄ ዓለም ለመመለስ እስካልፈጠነ ድረስም ለውኃ፣ ለመሬትና ለምግብ ዋስትና መባላት የቅርብ ነጋችን የሚወድቀበት ጉድጓድ እንደሚሆን በደንብ ተንትኖ ማስረዳት የሚችሉም ምሁራን ብቅ ማለታቸው ወቅታዊ ነው፡፡

የደረደርኳቸው ነጥቦች ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ እያልኩ ያለሁት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብን ሥቃይና መከራ በቁርጠኝነት በቃ የሚል ተግባራዊ ውሳኔ ላይ ወደ መድረስ የሚወስዱት መንገዶች ብዙ ናቸው ነው፡፡ ዛሬ ህልውናችን እንኳን በአገር ደረጃ በአኅጉርና በዓለም ደረጃ መያያዝን የጠየቀ መሆኑ ልባችንን ከረታ፣ በየሠፈር ጉዳይ መታኮሳችን፣ የሠፈር ዓላማን 50 ዓመት ሙሉ የፖለቲካ ግብ ብሎ መሸከም፣ ጭራሽ ሕዝባዊ ነኝ ከማለት ተሰነባብተን ንፁኃንን የመረሸን አዘቅት ውስጥ መግባታችን በፖለቲካ የመሞት ያህል ቅሌት መሆኑ ሊታየን ይችላል፡፡ ሚዛናዊ የሆነና የሁሉም ተራክቦ የተሰደረበት አዲስ የታሪክ ትንታኔ ብቅ ማለቱም ከሌሎቹ ሰበዞች ጋር ተጋግዞ የእስከ ዛሬ የታሪክ አረዳዳችንን ጥበትና ግንታሬ ለማጤን ሊረዳን ይችላል፡፡ የቤተ ዕውቀቶችን የሥራ ክፍፍል አክብሮ ከታሪክ ቤት የተሻለ ውጤት ለመጠበቅም የመነሻ ተስፋ ለመጨበጥ ዕድል እናገኛለን፡፡ ያ ሲሆን ጥራዝ ነጠቅ ደፋሮችም ልካቸውን ማወቅ ይጀምራሉ፡፡ በታሪክ አረዳድ የነበረንን ችግርና የፖለቲካችንን ለውጥ የለሽ አዙሪት ከተረዳን፣ ሃምሳ ዓመታት ለረዘመ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቁም ስቅል ኑሮ ምን ያህል ተጠያቂነት እንዳለብን ማየት ይቀለናል፡፡ ይህንን ያህል ራሳችንን ለመውቀስ ከደፈርን ደግሞ ተፀፅቶ ሕዝብ ማረን እንካስህ ማለት ሞት ሆኖ አየታየንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...