Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአንድ ወር ውስጥ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይስተጓጎል ተሠግቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለተከታታይ ዓመታት ሳይካሄድ የቆየውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲያከናውን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ዝግጅቱን ቢያጠናቅቅም፣ የጠቅላላ ጉባዔው አባል የሆኑት የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የሚጠበቅባቸውን አስፈላጊ ፎርማሊቲ እስካሁን አለማሟላታቸው ተገለጸ። 

በዚህም ምክንያት አገር አቀፍ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን በተቆረጠው ቀን ለማካሄድ መቻሉ አጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል።

የአገሪቱን የንግድ ኅብረተሰብ የሚወክለውና የሁሉም ክልሎች ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያካሂድ ባሳሰበው መሠረት ጉባዔውን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ ቆርጦ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት የሁሉም ክልሎች አባል ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን በማካሄድ፣ የኦዲት ሪፖርታቸውንና የአባላት ቁጥራቸውን አያይዘው ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጊዜ ገደብ በማስቀመጥ ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን በጠቅላላ ጉባዔው ለመሳተፍ እንደሚችሉ ያስታወቁት አምስት ብቻ መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ከአምስት ዓመታት በላይ ጠቅላላ ጉባዔውን ሳያካሂድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከአንድ ወር በኋላ ለማከናወን ያቀደው ጠቅላላ ጉባዔ እንዳያካሂድ እንቅፋት እንደገጠመው አመላካች ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድና ምርጫ ለማድረግ የተያዘው ፕሮግራም እስካሁን ድረስ እንደተጠበቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔውን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም በጠቅላላ ጉባዔው የሚቀርበውን የኦዲት ሪፖርት ማሰናዳታቸውንና ሌሎች ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቃቸውንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በአባልነት የያዛቸው 18 የሚሆኑ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በሕጉ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አካሂደው በአገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባዔ ለመወከል ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ጥቅምት 29 ቀን ለሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ለመሳተፍ እንዲችሉ በአባል ንግድ ምክር ቤቶች ወደ አራት ተከታታይ ደብዳቤዎች መጻፋቸውን አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡ 

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመወከል እንዲችሉ የኦዲት ሪፖርታቸውን የአባላቶቻቸውን ቁጥርና ሌሎች ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርት አሟልተው እስከ መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ እንዲያሳውቁ በተደረገው ጥሪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን እስካሁን ለተደረገላቸው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት አምስት አባል ምክር ቤቶች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

እስካሁን አስፈላጊውን መረጃ በማያያዝ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሪፖርት ያደረጉት የአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሲሆኑ፣ ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላላ ጉባዔው አንድ አንድ ድምፅ ያላቸው ሁለት የዘርፍ ምክር ቤቶችም በተመሳሳይ አስፈላጊውን መረጃ አያይዘው ማቅረባቸውን ከአቶ አሰፋ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቀሪዎቹ 13 አባል ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ንግድና ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ እንደሚችሉ እስካሁን ያሉት ነገር እንደሌለ ለመረዳት ተችሏል።

አባል ንግድ ምክር ቤቶቹ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት አዎንታዊ ምላሽ ያልሰጡበት ምክንያት የተለያየ መሆኑም ታውቋል፡፡ እንደ አቶ አሰፋ ገለጻም አንዳንዶቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልተው በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሊሳተፉ የማይችሉበትን ምክንያት አሳውቀዋል፡፡ 

አንዳንዶቹ ደግሞ የጉባዔ ማካሄጃ ጊዜ ይራዘምልን ያሉ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግን ምንም ምላሽ ሊሰጡ እንዳልቻሉም አቶ አሰፋ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ከአብዛኛዎቹ አባል ምክር ቤቶች የተጠበቀውን ያህል አዎንታዊ ምላሽ ባያገኝም ለአባል ምክር ቤቶቹ በጠቅላላው ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ በተከታታይ በጻፈላቸው ደብዳቤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ፎርማሊቲውን አሟልተው ሪፖርት የሚያደርጉ ከሆነ ሪፖርት ባደረጉት አባል ምክር ቤቶችን ብቻ በማሳተፍ ጠቅላላ ጉባዔው እንደሚያካሂድ የተገለጸላቸው በመሆኑ በዚሁ አግባብ ጠቅላላ ጉባዔው በተያዘለት ፕሮግራም እንደሚካሄድ አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ሪፖርት ባደረጉት ጥቂት አባል ምክር ቤቶች ብቻ ማካሄዱ በሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ግን ከዚህ በላይ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ መቆየት የለበትም የሚል አቋም ምክር ቤቱ መያዙን አስረድተዋል። 

አራት የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጉባዔው እንዲራዘምላቸው መጠየቃቸውን ያስታወሱት አቶ አሰፋ፣ አስገዳጅ ነገር ከሌለ የጉባዔውን ቀን ሊቀየር እንደማይችል ገልጸዋል።

የይራዘምልን ጥያቄ አቅርበዋል ከተባሉት መካከል በጠቅላላ ጉባዔው ሁለት ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው አባል ምክር ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ ትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ ሊሆን እንደማይችል ታውቋል፡፡

አቶ አሰፋ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ሌላ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆናቸው የትግራይ ንግድ ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊ ሊሆን የማይችልበትን ምክንያት እንዳሳወቁ አመልክተዋል፡፡ 

‹‹በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የከተማና የወረዳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ማካሄድ አልቻሉም፤›› ያሉት አቶ አሰፋ ይህም ባለመሆኑ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ጉዳዩን በማስመልከትም የክልሉ ንግድ ምክር ቤት ባደረግነው ጥናት የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አካሂደው ለማጠናቀቅ ስድስት ወራት የሚፈጅባቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ 

ስለዚህ አሁን ባለው በክልሉ ሁኔታ ከ42ቱ የወረዳና የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ያካሄዱት ሁለቱ ብቻ በመሆናቸው በክልል ደረጃ ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ ባለመቻሉ ይህንኑ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ያቀረቡ ሲሆን፣ የራሱን ውሳኔ የሚወስንበት ጉዳይ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

‹‹በትግራይ በኩል በክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር ያሉ አባል ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያችንን አካሂደን ማሳወቅ እንድንችል የስድስት ወራት ጊዜ እንዲሰጣቸው መጠየቁንም አመልክተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የዚህን ያህል ጊዜ መጠበቅ አልቻልም የሚል ከሆነ ውሳኔውን እንደማይቃሙም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር ለማካሄድ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ አሰፋ፣ ተለዋጭ ነገር ካለ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሚያሳውቅ እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ይካሄዳል ለተባለው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለሚካሄደው ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች መታወቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ አባል ምክር ቤቶች በጉባዔው የማይገኙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ዕጩ ማቅረብ አልተቻለም፡፡

ሆኖም ጠቅላላ ጉባዔው የሚካሄድ ከሆነ ከአምስቱ ተሳታፊ አባል ምክር ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ የአባላት ቁጥር ያለው የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ምክር ቤቱ በሚኖረው አብላጫ ድምፅ አዲስ የቦርድ አባላትን ለማስመረጥ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ 

ምንጮች እንደገለጹትም የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ለፕሬዚዳንትነትና ለቦርድ አባላት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ለማቅረብ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ አወካከል በአባላት ቁጥር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እስካሁን በነበረው አወካከል የኦሮሚያና የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በጋራ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ በመያዝ ይታወቃሉ፡፡ ቀሪዎቹ ወንበሮች የ16ቱ አባል ምክር ቤቶች ሆኖ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የሚመራው ቦርድ የሥልጣን ዕድሜውን ከጨረሰና ኃላፊነቱን ማስረከብ ከነበረበት ከአራት ዓመታት በላይ የዘገየ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ የነበረበትም ቢሆን ይህንን ሳያደርግ ቆይቷል፡፡ በየሁለት ዓመት ምርጫ ማካሄድ ሳይችል እስካሁን መቆየቱ ብዙ ሲያነጋግር ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በሕገ ደንቡ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ሲያካሂድ ለመቆየቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታን በምክንያትነት ሲያቀርብ ነበር፡፡ 

ከሁሉም በላይ ደግሞ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ስለሚሻሻል ጉባዔውንም በአዲሱ አዋጅ መሠረት ለማካሄድም ጊዜ ሲጠብቅ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ሆኖም በዚህ መሀል ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጉባዔያቸውን እንዳያካሂዱ በማሳሰቡ የጥቅምት 29ኙ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካሄድ ሊወሰን ችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች