Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለአገረ መንግሥት መፅናት የሚበጀው ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት ነው

ለአገረ መንግሥት መፅናት የሚበጀው ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት ነው

ቀን:

 በገለታ ገብረ ወልድ        

       የአነጋገር ወግ ሆነና በእያንዳንዱ አገር ያለፈውን ነገር ሁሉ መዘን “ደጉ ዘመን” (The Good Old Days) የማለት ሰብዓዊ ትዝታ አለ፡፡ እኛ ግን ያለፈው ሁሉ ደግና ጥሩ ብለን ልንነሳ አይዳዳንም፡፡ ጦርነትንና ግጭትን ደግሞ አክሳሪና አውዳሚ ከማለትም አንቦዝንም፡፡ በተለይ እኛን ለመሰሉ ደሃ አገሮች የአገረ መንግሥትን አቅም እንደ ጥንጣን በልተው የሚጨርሱ የውስጥ አለመግባባትና ግጭቶች ናቸው ማለትም ግነት የለውም፡፡

በእርግጥ በሌሎች አገሮችም ቢሆን በጊዜያት ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች ዋነኛው የሰው ልጅ የሚያካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ነው፡፡ አገሮች በተናጠል ወይም በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል በእርስ በርስ አለመግባባትና ጥላቻ የሚቀሰቀሰው ጦርነት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን አስተላልቋል፡፡ ከዚያም በላይ የዓለም አገሮች ጎራ ለይተው የተጠዛጠዙባቸው እንደ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ያሉ ክስተቶች በአውዳሚነታቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለእነዚህ ጦርነቶች መቀስቀስ በርካታ ምክንያቶች በየታሪክ ድርሳናቱ ቢጠቀሱም በአብዛኛው ከመሪዎች አምባገነናዊነት፣ ዘረኛና ዘራፊ አስተሳሰብ የሚመነጨው የተሳሳተ አመለካከት ከፍ ያለውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገፋን፣ ጥቅማችን ተነካ፣ ተገለልን፣ ተጨቆንን ባይነትም ጦርነት ይነሳል፡፡

በተለይ ፖለቲከኞች ሕዝቦችን ባልተገባ የጥላቻና የቂም መንገድ በመንዳት በትንንሽ ምክንያቶች (በዘረኝነት፣ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ፣ እንዲሁም በድንበርና በወሰን፣ በጋራ ሀብት፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ሽሚያ…) ሰበብ የሚለኮስ እሳት በቀላሉ ሳይበርድ፣ እስከ ትውልድ የሚደርስ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፣ የአፍሪካ እውነታ ይኸው ነው፡፡

   ይህ ችግር በሠለጠነው ዓለም ጉዳት ካደረሰ በኋላ በይቅርታና ወቅቱ በሚጠይቀው የጠንካራ አገረ መንግሥት ግንባታ ዕሳቤ እየተሻረ መጥቷል፡፡ በሦስተኛው ዓለም በተለይ በአፍሪካ ግን ቅኝ ገዥዎችና የተዛባ አስተሳሰብ አራማጆች በቀደዱት ቦይ በመፍሰስ፣ እስካሁንም ድረስ ጥላቻ፣ ቂመኝነት፣ ግጭትና መለያየት ተባብሶ የቀጠለባቸው አገሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ የፖለቲካ ጥገኞችም የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማረም መለያየትን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

የአገራችን ሁኔታም ከዚህ እውነታ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ እንደ ብዙ ሰፋፊ አገሮች ኢትዮጵያም ብዝኃነት የሞላባት፣ የተፈጥሮ ባለፀጋና የታሪክ ምሰሶ ብትሆንም በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይል የግጭትና የጦርነት ሰለባ ሆና ነው የቆየችው፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ የእነዚያ ዘመናት ቅሪት አስተሳሰቦች በአሁኑ ትውልድ አዕምሮ ውስጥም እንዲመላለሱ እየተደረጉ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና መነጣጠል እያንዣበበ መሄዱ ነው፡፡ ከሐሳብ ትግልና መነጋገር ይልቅ ጉልበትና መተላለቅ ከባድ ዋጋ በማስከፈልም ላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አገረ መንግሥቱም ሊፀና አይችልም፡፡

አገራችን ምንም እንኳን በሕዝቦቿ ጥንካሬና በፈጣሪም ረዳትነት ሳትጠፋ እዚህ ብትደርስም፣ በየዘመናቱ በውጭ ጦርነትና በውስጥ ግጭት ያለቀባት ሕዝብ፣ ምሁርና አምራች ኃይል ግን ለኋላ ቀርነትና ድህነት መባባስ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ይኼ ትውልድ መገንዘብና መገመት አለበት፡፡ ያ አልበቃ ብሎን ባለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን አካባቢ (በትግራይ፣ በአማራና በአፋር) ብቻ ሳይሆን፣ በምዕራብ ኦሮሚያ የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው ልዩ ልዩ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር በማፋለማቸው ቀውስ እየተባባሰ ይገኛል፡፡

አስገራሚው ነገር ግን ሁሉንም አማፅያንና ተዋጊዎች በኃይል ለመስበር ተሞከረ እንጂ፣ ሰብሰብ አድርጎ ለመነጋገርና የሚስተዋሉ ነበርና አዲስ ችግሮችን ለመፍታት በቂ ጥረት አለመደረጉ ነው፡፡ የውጭው ዓለምም ቢሆን ችግሮችን በእጅ አዙር ያባብሳል እንጂ፣ አገረ መንግሥት እንዲፀናና አገር እንድትገነባ መደላድል የሚፈጥር አልሆነም፡፡

ካለፉት የታሪክ ዝንፈቶችና የተሳሳቱ የጥላቻ መንገዶች ዓለም እየወጣ ወደ ሥልጣኔና ትብብር ቢመጣም፣ በእኛ አገር በዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ለምን የመራራቅና የመገፋፋት ዕሳቤ አረበበ ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው፡፡ የተቃርኖ አስተሳሰብስ እስከ የት ድረስ ሊወስደን ይችላል ብሎ ማውጠንጠንም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች የዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻ የጎሳ ፌዴራሊዝም መከተላችን ነው ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች በጫኑብን ኢፍትሐዊነት ምክንያት የተገፉ ወገኖች በመብታቸው ነው ይላሉ፡፡ ይህ ነው/አይደለም ለማለት ግን እንደ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ያሉ ገለልተኛ ተቋማትን በጋራ ወደ ሥራ አስገብቶ የሕዝቡን ውሳኔ ማዳመጥ አስፈላጊ ነበር፡፡

በእርግጥ ባለፉት ዘመናት ከአገራዊ አንድነት ይልቅ የብሔርና የማንነት መብትና ጥቅምን ለማስከበር ከሚዛኑ ያለፈ ትኩረት መስጠት እንደነበር አይካድም፡፡ ከሁሉ በላይ ይህን አስተሳሰብ በአዲሱ ትውልድ ላይ ለማስረፅ ሐሰተኛና የተጋነነ ትርክትን በተራ የፖለቲካ ቀለም እየቀቡ ጥላቻን መዝራት ዛሬ ለደረስንበት አብሮነት መዳከምና የቂም በቀል ፖለቲካ ዳርጎን መገኘቱም አይሸሸግም፡፡ ይህን ዝንፈት ለመቀየር የሚችለው ደግሞ ፖለቲከኞችና መላ ልሂቃን በረጋ መንፈስ ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበት መድረክ ሲከፈትና ሲዳብር ነው፡፡ ጉዳዩ ለምን ችላ ይባላል ነው ጥያቄው፡፡

እንግዲህ ይህ ለምንና እንዴት ሆነ ከማለት ይልቅ ከጥላቻና ከዘረኛ አስተሳሰብ፣ የጎሳና የዘር ፖለቲካ ቅኝት እየወጣን ወደ አገራዊ አንድነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች አንድነት ልንመለስ እንችላለን ብሎ ማብሰልሰል ተገቢና አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ፋሽሽታዊ ባህሪ የነበራቸውና በዘረኝነት ብቻ ለከፋ ግጭትና መለያየት የተዳረጉ የዓለም አገሮች አካሄድም ተሞክሮ ሊሆነን ይችላል፡፡ ተው ጎብዝ ሰከን ብለን አገረ መንግሥቱን ከመናጋትና መፍረስ እናድነው ማለታችንም ለዚሁ ነው፡፡

ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ጀርመንን በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የናዚ ፓርቲው አምባገነን መሪ አዶልፍ ሂትለር ጀርመኖችን ከዓለም የሚነጥል ፋሽስት ብቻ ሳይሆን፣ የውስጥ አንድነታቸውንም የሚሸረሽር ዘረኛና ከፋፋይ አዘቅት ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ የዚያ አስተሳሰብ ጥንስስ በርዕዮተ ዓለምና በፖለቲካ አስተሳሰብም ታግዞ በርሊንን ከሁለት የከፈለ ግንብ እስከ መገንባት ያደረሰ ነበር፡፡ ጀርመናዊያንም ምሥራቅና ምዕራብ በሚል ተከፋፍለው ለዓመታት ቆይተዋል፡፡

በኋላ ግን የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ አብዛኛው ምሁርና የፖለቲካ ኃይል ግልጽ ምክክርና ኅብረት ፈጥረው ሕዝቡንም በማንቃት ዘመን ተሻጋሪ ጠንካራ አገራዊ አንድነት አረጋግጠዋል፡፡ ዛሬ በቆዳ ስፋቷ ከእኛዋ ኦሮሚያ ክልል ያነሰችው ጀርመን በሥልጣኔም ሆነ በዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋ ግንባር ቀደም የምድራችን ተጠቃሽ አገር የሆነችው፣ ከአገራዊና ከኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚመነጭ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞዋ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ማጠናከሪያ በሁለተኛነት ሩሲያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያቺ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችና በሶሻሊዝም ርዕዮት ቀዳሚ መሞከሪያነት የምትታወቅ ምድር፣ በታሪኳ በተመሳሳይ በጠባብነትና ዘረኝነት ከፍተኛ ፈተና አስተናግዳለች፡፡ ከሩሲያ አብዮት በኋላ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግራ ዘመም (Center Left) በመሆኑና በኒዮሊብራሊዝም ኃይሉ የቀዝቃዛው ጦርነት ተፅዕኖ የተባበሩት ሩሲያ ወደ 15 ብጥስጥስ አገሮች ልትበተን ችላለች፡፡ ዛሬም ድረስ የእነ ስታሊን ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፈለግ የኪሳራ ምልክት ሆኖ እየተጠቀሰ ነው፡፡

ይሁንና አሁንም የተባበሩት ሩሲያ ፓርቲ ሀልዮትን በማግኘቱ (በተለይ ከቭላድሚር ፑቲን መምጣት በኋላ) በአንድ በኩል በዕድገትና በሥልጣኔ ቀዳሚ የምትባል አገር፣ በሌላ በኩል ያለውን ሕዝብ የሚያስተሳስርና የተበተነውንም የሚመልስ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ለመሆን በቅተዋል፡፡ እዚህም ላይ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አገራዊ አንድነት ማቆጥቆጡ ድርሻው ከፍተኛ ሆኖ ይገኛል (ያም ሆኖ አሁን ላይ አብራት ከኖረችው ዩክሬን ጋር በእጅ አዙር ምዕራባዊያን በገጠሟት ጦርነት ሩሲያን ውድ ዋጋ ማስከፈል ብቻ ሳይሆን ሰንኮፉ የሚመነጨው ከቀደመው የመለያየት ኡሪት መሆኑን መረዳት አያዳግትም)፡፡

የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት አገሮች አንዷ የሆነችው ቻይናንም ብንመለከት (ፀረ ዴሞክራሲያዊነቱም ቢኖር በሁሉም ሕዝቦች ላይ እንጂ ነጣጥሎ የሚፈጸም አይደለምና)፣ በሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ረገድ የማይናወጥ ሐውልት በመገንባት ከትውልድ ትውልድ የምትሸጋገር ምድር ነች፡፡ ይህም በተባበረና በሚደማመጥ የሕዝብ አቅም ምድርን ጉድ ያሰኘ ዕድገትና ሥልጣኔ እንድታረጋግጥ አስችሏታል፡፡ በዓለም የአገረ መንግሥት ጥንካሬ ቻይናን የሚቀድም አገር አለ ማለትም አይቻልም፡፡

በመሠረቱ ፌዴራላዊ አስተዳደርን ባትከተልም 1.5 ቢሊዮን ከሚደርሰው የቻይና ሕዝብ 93 በመቶ የሚሆነው “ሀን“ በሚባለው ብሔር የሚታቀፍ ነው፡፡ ቀሪው ስድስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብም የ56 አናሳ ብሔሮች አባል እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ግን በኮሙዩኒስት ፓርቲውም ሆነ በአገረ መንግሥቱ እንደ መጠናቸው የሚወከሉበት አግባብ ስላለና በአገረ ቻይና በእኩልነት መንፈስ የሚጠቀሙበት ዕርምጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ስለመጣ፣ ምንም ቢሆን እንደ ሕዝብ በአንድነታቸውና በቻይና ሉዓላዊነት  ሊደራደሩ አይችሉም፡፡ መነጣጠልና የቂም በቀል ፖለቲካም በዞረበት አይታዩም፡፡

     ከላይ ከጠቃቀስናቸው አገሮች ሌላ በተለይ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚያራምዱ እንደ ህንድ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና መሰል አገሮችንም ስንመለከት በቀለም (አልፎ አልፎ የሚታይ ችግር ቢኖርም)፣ በዘርና በጎሳ ተሰባስቦ ከመታገልም ሆነ አንዱ ሌላውን ከማሳደድ ልክፍት ከተላቀቁ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አረረም፣ መረርም በአገራቸው አንድነትና በሉዓላዊ ሰንደቃቸው ላይ መደናገርና መወዛገብ ውስጥም ሊገቡ አይችሉም፡፡ ወይም አለመግባባቱና ጭቅጭቁን ተሻግረውት ደልዳላው ሜዳ ላይ ወጥተዋል፡፡

ብዙዎቹ እንደሌላው ዓለም ሁሉ በታሪካቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ አስከፊ ጦርነቶችና አገዛዞችን ማሳለፋቸው ቢታወቅም የዛሬው ትውልድ በሥልጣኔና በዕድገት የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ከማንቃት ባሻገር፣ በማይበጀው ትርክትና ጥላቻ ላይ እንዲጠመድ አይፈልጉም፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ሥር በሰደደበት መስተጋብር ውስጥ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለእኩልነትና ለአንድነት በመጠቀም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህና ሌሎች በርካታ አገሮችን አብነቶች ስንፈትሽ የአገራችንስ ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይገባዋል የሚል ተጠየቅ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ፣ መንግሥትንም ሆነ መላውን የፖለቲካ ልሂቃንም እባካችሁ ከዘር፣ ከጎሳና ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥተን በአንድ አገር በእኩልነትና በመተሳሰብ፣ እንደሚኖሩ ሕዝቦች ተደማምጠን፣ በሠለጠነ መንገድ እንጓዝ ለማለት እንሻለን፡፡ ለመሆኑ የአንድ ወገን የበላይነት ሳይንፀባረቅ በእኩልነትና በፍትሐዊነት በአገረ መንግሥቱም ሆነ ከጋራ ኬኩ መጠቀም የማይቻለው ለምንድነው?

በመሠረቱ ከላይ እንደተጠቆመው የአገራችን አንዱ ትውልድ በጎሳ ፌዴራሊዝምና ከራር ብሔርተኝነት ሲነጉድ በመቆየቱ፣ ሁላችንንም ጎሰኛና መንደርተኛ እያደረገን መጥቷል፡፡ ቢያንስ ስለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አንድነት ደንታ ቢስ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በዚህ አካሄድ ከቀጠልን የጋራ ቤትና በታሪከ “የእኛ” ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላለፋችን ዋስትና ሊኖረን አይችልም፡፡ ልማት፣ ሰላምና ብልፅግናንም ማሰብ ከንቱ ምኞት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡

       እንዲያው ከላይ ያነሳናቸው አገሮችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የአገረ መንግሥት ጥንካሬ እንተወውና አሁን ማን ይሙት የብሔር ፌዴራሊዝም አዋጭና ዘላቂ የአገር አንድነት የሚያስከብር ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በዚህ ደረጃ መገኘት ነበረብን? እንደ አገር “ተለወጥን!” እያልንስ ይህን ያህል አገራዊ ትርምስ (ተዟዙሮ የመሥራት፣ በየአካባቢው ተረጋግቶ የመኖር፣ የማልማትና የመጠቀም ሥጋት ተባብሶ) ይታይ ነበር? ለይቶልን ወደ ጦርነት ለመግባትና ለመጨካከን እንበረታ ነበር ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው በሌላው ዓለም እምብዛም ባልተስፋፋና እየቀረ በመጣበት ሁኔታ፣ የሥርዓቱ አካሄድ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና የፈጠራ ተረክ የሞላበት መሆኑ እንደማያዛልቅ በመገንዘብ ትርክቶችን ማስተካከልና አብሮ የሚያኖር አገረ መንግሥት መገንባት ይበጃል፡፡ ይህ እየታየ ያለው ከግጭትና አለመግባባት የማያወጣ ጉዞ ግን፣ በሁሉም  አካባቢ  መካረርና የመስገብገብ ፍላጎት እንዲባባስ ከማድረግና አገር ከማዳከም ውጪ የሚያስገኘው ፍሬ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ በመሠረቱ በጎሳ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ትግል በየትኛውም ዓለም ቢሆን አሁን በዚህ ዘመን የሌለ ሲሆን፣ በነበረበት የቀደሙት ጊዜያትም አገሮችን በኪሳራ ያዋረደ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡

     በእርግጥ በአገሪቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት መተግበሩ በራሱ ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ ትልቁ ፈተና ግን ክልሎች በዋናነት በብሔር ንፍቀ ክበብ በመካለላቸው በዘር የተደራጁ ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሰሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳሻቸው በመገንባታቸውና በማዘዛቸው አጉል ፉክክርና ትከሻ መለካካት እንዲጀምር አድርጓል፡፡ ከክልል ወርዶ ዞኖችም፣ በተለይ በብሔር የተቋቋሙቱ (እንደ ወላይታ፣ ጌዴኦ፣ ጉራጌ…) የራሳቸውን የብሔርተኛ መንገድ እየተከተሉ ነው፡፡ በዚህ ላይ የፌዴራሉ መንግሥት ደከም ያለ ሲመስል መፋጠጥ ስለመምጣቱ ቀደም ሲል በትግራይ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የሆኑት ማሳያዎች ናቸው፡፡

እንግዲህ ዛሬ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠልም ሆነ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን ጠብቃ እንድትሄድ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ፍልሚያ የሚካሄድበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ አገርን ወደኋላ የሚመልሱና የተጠረቃቀሙ ተግዳሮቶችም አላላውስ እንዳሉን በግልጽ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሌሎች አገሮች ተሞክሮን ጭምር በመጥቀስ፣ እንደ ዜጋ የመፍትሔ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈልገውም፣ የችግሮቹ ሁሉ ሰንኮፍ ከዘር ፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ይህን ለመሻገር ደግሞ የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት በግልጽ የሚያረጋግጥ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ጅምርን ዳር ማድረስና በልበ ሙሉነት የኅብረተሰቡ ውሳኔ መሬት ላይ ማውረድ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...