በአሰፋ አደፍርስ
አገሬ ኢትዮጵያ ማን ይሆን ወገንሽ? የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ ሲበላሽ፣ ታዛቢ ያጣሽ ወገን የራቀሽ፣ መከራና ችጋር ተታውሮሽ ደረስኩልሽ የሚል ወገን ያጣሽ፣ የሰው ልጅ በገንዘብ ተውተብትቦ ግርማሽን ቀንሶ እንዳልሆነ ሆኖ ሊያዋርድሽ ደፋ ቀና ሲል ማየቱ አልገረመሽ?
ዋ አንቺ አገር ስንቱን አየሽ ስንቱንስ አሳለፍሽ?
አገሬ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ተስፈኛ፣
ወደቀች ጠፋች ሲሏት በተዓምር የምትነሳ፣
ለጠላት የማትመች በእግዜር ጥበብ ነዋሪ፣
ሁሌም በአምላክ ፍቅር የተመላች ንፅህት ውድ አገሬ አይዞሽ በሀብት በገንዘብ የማንደለል ልጆችሽ አለንልሽ፣
በዓለም አደባባይ ስምሽን ለማንሳት ወደኋላ የማንል ቆራጥ ልጆችሽ አለንልሽ፣
ወገን ከወገኑ አክርሮ ሲጣላ፣ ወንድም ከወንድሙ እንደ አውሬ ሲባላ እሰየው ይላል ያ የጠላት ተኩላ፡፡ ይህች ማስታወሻዬ ግራ ለተጋቡ ወገን ዘመዶቼ ማመላከቻ ስትሆን፣ የጥንቷ አገሬ በወገን አልጠግብ ባይ ልጆቿ የመጨረሻ ዕድሏ ሆነና ለውርደት መዳረጓ እጅግ ስላበሳጨኝ መልዕክቴን ለእኔ መሰል ተቆርቋሪዎች ለማድረስ ተነሳሳሁ።
የቀደምቷ አገሬ የታሪክ መሠረት እናቴ አገሬ ጌታ ክርስቶስ የወደዳት በቅዱስ መጽሐፍ የተወደሰች፣ የቀለም ልዩነትን የማታስተናግድና የሁሉ እኩል አገር የነበረችና አሁንም ያለች፣ ወደፊትም የምትኖር አገሬ ኩራቴና መከበሪያዬ ናት፡፡ ዋ አንቺ ኢትዮጵያ ታሪክሽን ዓይተው ማገናዘብ አቅቷቸው በአዳዲስ ዓለማዊ አመለካከት ያሸበረቁ መስሏቸው፣ ያለማወቅ ክፉ በብልጭልጭ ነገር ተታልለው አንቺን እንደ ትንሽ ሲያዩሽ እንዴት ታዝበሻቸው ይሆን?
አይዞሽ እናቴ ኢትዮጵያ፣ የማስተማሪያ ሰነዱ በግምጃ ቤትሽ መኖሩን ሳይረዱ በከንቱ ደከሙ፡፡ ልናስተምራቸው ብንል ራሳቸውን በማታለል አዋቂ መስለው ሲዘባነኑ አየናቸው፡፡ ዋ ያለማወቅ ብለን ታዝበን ተውናቸው።
ይህንን ካልኩ በኋላ ወደ ተነሳሁበት ወደ አዲሱ ትውልድ የታሪክ እንዝህላልነት ገብቼ፣ አዲሱን የታሪክ መሠረት ላስተምር ተነሳሁኝ። አይ ይቅርታ ማስተማር ሳይሆን ለማስገንዘብ ማለቴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ጥንታዊት የታሪክ አገር መሆኗን የዓለም ታሪክ የመሰከረላት፣ በመጽሐፍ ቅዱስም በቀደምትነቷ የታወቀች ለመሆኗ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ የዓለም ሊቃውንት የሚመሰክሩት ነው። አዎን የማያውቁ እንዝህላሎች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ የታሪክ ምሁር ነኝ ባይ አንዱ እንዲህ ብሎ የለ? ‹‹አፄ ምኒልክ ሲባል በወሬ ሰማሁ እንጂ ታሪኩን አላውቅም፤›› እንዳለው፣ ራሱን ሳያውቅ የ16ኛውን ክፍለ ዘመን ያልተገነዘበ ነውና ምን ይባላል? ወገኖቼ የተነሳሁበት ዋናው ዓላማ ነባሯ አገሬ ባልሆኑ ሰዎች እጅ ወድቃ ታሪኳን ሲሸረሽሩ በማየቴ፣ ያልነበረ ታሪክ ሲፈጠር በመመልከቴና ይህንን ታሪክ ርቆ ሳይሄድና መስመሩን ሳይለቅቅ መስመር ለማስያዝ ያለብን ጊዜ አሁን ነው።
መቼም “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማ” እንዲሉ፣ ተስፋ ሳንቆርጥ እንቀስቅሳቸው፡፡ ማን የበላይ፣ ማን የበታች ሆነና ይሆን ይህ ሁሉ እሽቅድምድም? “ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ” ሆነና ነገሩ፣ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያጡ ወገኖቼ ሲራኮቱ፣ ሲፋጁና ከእኔ በላይ ላሳር ሲሉ ማየቱ አልገረመን ይሆን? ወንዙ ሞልቶ ተትረፍርፎ፣ መሬቱ የገበሬ ያለህ አገላብጠኝ፣ ጎልጉለኝ፣ ዝራብኝ፣ ተጠቀምብኝ እያለ አፉን ከፍቶ ተንሰራፍቶ፣ ወጣቱ ወገኔ አስተምሮ የሚመራው አጥቶ በየመንገዱ ሲንገላወድ፣ ወጣቷ ሕፃን አዝላ ለልጄ የዳቦ መግዣ እያለች ስትለምን፣ እኔ በተንቀባረረ ቤት እየኖርኩ በቀን ሦስቴ እየበላሁ በተንቀባረረ አውቶሞቢል ስንሸራሸር ይህ ይሆን ከወገኔ የለየኝ?
ታዲያ ያለኝን ተካፍዬና የሥራውንም መንገድ አሳይቼ ባልፍ፣ ሁሉም ወገኔ ለቁምነገር እንዲበቃ መንገድ ብከፍት፣ ዋሾነት፣ ሰብቅና ማታለል እርም መሆኑን ባስተምር፣ የምትለምነዋ የሕፃኑ እናት ለልጇ የዳቦ መግዣ ገንዘብ የማግኛ መንገዱን ባስተምራት አይገባት ይሆን? ለምን አይገባትም? በፀሐይ መንከራተቱን ትመርጥ ይሆን? የለም አትመርጥም፡፡ የእኔ የግል ጥቅምን በማስቀደም የአዙሮ ማየት አንገቴ ተጣምሞ እንጂ፣ እሷስ ወዲያውኑ ሠልጥና ሥራ ላይ ውላ ልጇን እንደ ሌሎቹ ለመንከባከብ ጠልታ አይደለም። ወጣቱ ጎረምሳ የሚሠራው አጥቶ በየበረሃው ባክኖ መቅረቱ ሰው ነውና የሰው ፍላጎቱን ለማሟላት በመጓጓቱ፣ ወንድ ነውና ሁሉንም መሞከር አለብኝ በማለት በየጥሻውና በየበረሃው ሲንከራተት፣ ሴቷም ልጃችን በተመሳሳይ ስትውተረተር የባህር ዓሳ ነባሪ ቀለብ ሆነው እየቀሩ ነው፡፡
ዋ የእኔ ነገር ሰው መስዬ ቀና ብዬ ስራመድ አይገርማችሁም? ግማሽ ጎኔ ራቁቱን፣ ግማሽ ጎኔ ለብሶና ተኮፍሶ ዋ ሰው መሆን፡፡ ለ500 ሚሊዮን ሕዝብ የምትበቃ ሀብታም አገር ተሸክሜ በየጊዜው ስለመን የዓለም ምሁራን ምን ይሉኝ ይሆን? ይደሰቱ ይሆን ወይስ ይታዘቡን ይሆን?
እርስ በርስ ስንጠፋፋ፣ ወንድሜን ያለ ርኅራኄ ስገድለውና ሲገድለኝ፣ ሥልጡን ነን ባይ አፋጂዎቻችን እንዴት ይታዘቡን ይሆን? ዋ አንቺ ያልታደልሽ አገር ምን ጎድሎሽ ይሆን ለዚህ የበቃሽው? የአርሲው፣ የባሌው፣ የሶዶው፣ የአቢቹ ግምቢቹው፣ የወላይታው፣ የከምባታው፣ የካፋው፣ ወዘተ. የዚህ ሁሉ ሽማግሌ ምነው ድምፁ ጠፋ? ፈርቶ ይሆን ወይስ ተፀይፎ? እነዚህን ሁሉ ማስታረቅ ነበር ሥራቸው፡፡ ታሪክን አውግተው፣ ምሳሌን ደርድረው፣ ዕርቅ ካልወረደ የሞተ ሰው አስከሬን የመቃብር ጉድጓድ አይገባም ብለው፣ ከዳር ዳር መሬት ወድቀው፣ ለምነውና ተለማምነው ያስታርቁ የነበሩ የአማራውና የሲዳማው ጉምቱ ምን በላቸው ዘንድሮ? ጥንትማ ሽማግሌ ጦር አይፈራ፣ ለንዋይ አይጓጓ፣ ለእውነት ይሞት ነበር፡፡
ዛሬስ፣ ዛሬማ አዛውንትም ሆኑ የእምነት ተጠሪዎች ስልክ በኪሳቸው ይዘው ባልነበሩበት ቦታ አለሁ ማለት ከጀመሩ ሰነባበተ እኮ፡፡ አይገርምም ግን? አትዋሽ፣ አትስረቅና አትጣላ የሚለውን የሚሰብኩ መጥፋታቸው የአየር ንብረት ለውጥ ይሆን እንዲህ ያዳከማቸው? መምሩም ሆኑ ሽማግሌው ወደ ጥንቱ ይመለሱ፣ ስልኩንም ይጣሉት ከኪስዎ፡፡ እኛንም ይገዝቱን በነበረው ሥርዓታችን፣ እባካችሁ እንመለስ ወደ ልቦናችን፡፡ በሰው ታሪክና ወግ አንኩራራ ይብቃን እባካችሁ።
ነባር ቋንቋዎቻችንን ንቀን ምነው በሰው ቋንቋ መንተባተብን መረጥን? ዋ ያለማወቅ የ900 ዓመታት ቋንቋ ተከብሮ የሦስት ሺሕ ሲናቅ ራሴን በጣም ጠልቼ ሌላውን ወደድኩኝ ብዬ ስመፃደቅ። ወገኖቼ ተው በራሳችን እንመካ፣ እንኩራራ፣ የሰው ወርቅ አያደምቅምና።
የቤቱን ዓይናማ እንጀራ ጥሎ የጎረቤቱን ዓይን የለሹን ጥፍጥፍ እንጀራ እንደሚያደንቅ ወስላታ አንሁን፡፡ በራሳችን እንኩራራ፣ እንኮፈስ፡፡ ነገር ግን ሠርተን እንጂ ባልሠራነው በባዶ ሜዳ ማለቴ እንዳልሆነም ተገንዘቡልኝ። አገሬ ኢትዮጵያ ሁሉ ያላት ሁሉ የሞላት ሆና ተቸግራ፣ አፈር የሌላቸው አፈር ከውጭ አምጥተው በጥሩ ውጤት አገራቸውን አጥግበው እኛን ለመርዳት ሲችሉ፣ ሁሉ ያለን ለማኝ ሆነን መገኘት ካላሳፈረን ምን ያሳፍረን ይሆን? የፍጅት ጦርነቱ ራስን ካለማወቅ ሌላ የሚባልለት ይኖር ይሆን? እስቲ መልሱልኝ እባካችሁ፡፡ ወገኖቼ ይህችን የብሶት መልዕክቴን ተነጋገሩባት፣ እንወያይባትም።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡