በአማራ ክልል በዝናብ እጥረት ሳቢያ በስምንት ዞኖች የተከሰተው ድርቅ በመጪው ታኅሳስ ወር ችግሩ የከፋ እንደሚሆን፣ የክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በዝናብ እጥረት ሳቢያ ሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በአንዳንድ ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ሳቢያ ኅብረተሰቡና እንስሳት ለችግር መጋለጣቸው ተገልጿል፡፡
በእነዚህ ዞኖች በዋናነት የተከዜ ተፋሰስን ተከትሎ ሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ኸምራና ሰሜን ወሎ ትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ በሰሜን ሸዋ ዞን በግሪሳ ወፍ ሳቢያ አራት ወረዳዎች ለችግር መጋለጣቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው አባተ ተናግረዋል፡፡
በስምንቱ ዞኖች ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ለዚህ የሚሆን ሀብት ለማሰባሰብ በክልሉ የተወከለ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የትምህርት ቢሮ ኃላፊና ሌሎችም አመራሮች በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመፍታት የሀብት የማሰባሰብና ችግሩን ለማስረዳት አዲስ አበባ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም የተፈቀደ የመጠባበቂያ ዕርዳታ እየተሠራጨ መሆኑን፣ ተጨማሪ በጀት ተፈቅዶ የግዥ ሒደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በተወሰነ መጠን የመደበው ዕርዳታ መኖሩን ገልጸው፣ በኃላፊነት ዜጎች እንዳይጎዱ የክልሉ የልዑካን ቡድን ተጨማሪ በጀት ለመጠየቅ መላኩን ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ በድርቁ ሳቢያ የተቸገሩ ዜጎችን ለመርዳት ምን ያህል ዕርዳታ ያስፈልጋል ብሎ ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልገውን መገመት እንደማይችሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በድርቁ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙት እንስሳት መሆናቸውን፣ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ሰዎች ለረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
ድርቁ የክልሉን አብዛኛው ቦታ ያዳረሰና ሰፊ ሽፋን ያለው በመሆኑ፣ ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ከወዲሁ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በተለይም የድርቁ ሁኔታ በተንሰራፋባቸው ቦታዎች ተንቀሳቅሶ መረጃ ለማሰባሰብም ሆነ ዕርዳታ ለመስጠት የፀጥታው መደፍረስ ማነቆ ሆኖበታል ብለዋል፡፡
በዚህም ሁኔታ በዞኖቹ የተከሰተው የድርቅ ሁኔታ እስከ መጪው ታኅሳስ ወር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን፣ ኅብረተሰቡ ተከታታይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አታለል አቦሃይ በበኩላቸው፣ በአማራ ክልል ድርቅ መከሰቱንና ዋግ ኸምራና ጃናሞራ አካባቢ ደግሞ ችግሩ የጎላና በየዓመቱ በቋሚነት የሚረዱ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይም ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች በቋሚነት ሲረዱ የቆዩት መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጀቶች እንደነበር፣ ድርጅቶቹ ዕርዳታ ካቋረጡ ስምንት ወራት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡
እነዚህን አካባቢዎች ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች ድርጀቶቹ ዕርዳታ በማቋረጣቸው፣ መንግሥት ለአራት ሚሊዮን ዜጎች የሚሆን ዕርዳታ ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡
ከአማራ ክልል በተጨማሪ የድርቅ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች ዕርዳታ መላኩን ጠቁመው፣ ክልሎች የቅድሚያ ቅድሚያ ለችግር የተጋለጡ ብለው የለዩትን ያሠራጫሉ ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ድርቅ ከተከሰተባቸው አንዱ ጃናሞራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ አካባቢ ብቻ 86,000 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
ለእነዚህ ዜጎች የሚሆኑ አስቸኳይ ዕርዳታ በተያዘው ሳምንት መላኩን ገልጸው፣ ለትግራይና ለሌሎች ችግር ላለባቸው ቦታዎች ዕርዳታ እየሄደላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በቋሚነት በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የሚረዱበት አሠራር እንዳለው ገልጸው፣ የፌዴራል መንግሥት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት የክምችት አቅሙን እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ በፀጥታ ችግር ምክንያት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት እንዳልቻለ ቢገልጽም፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ግን በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕርዳታ አለመስተጓጎሉን አስታውቋል፡፡