ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማዕከል ያደረገ አዲስ ከተማ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሊመሠረት መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢንጂነር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ለሪፖርተር እንደተናገሩት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታቀደው የህዳሴ ግድብ ከተማ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት የሚተነፍስበት ይሆናል።
‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ የሚፈጥረው ዕድል አዲስ ከተማ እንዲመሠረት የሚያስገድድ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢንጂነር)፣ ለሚመሠረተው አዲስና ዘመናዊ ከተማ የሀብት ምንጭ የሚሆነው ከግድቡ ጀርባ በሚታቆረው ውኃ መሆኑን አስረድተዋል።
በግድቡ አካባቢ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ምቹ መሆኑንም ሚኒስትር ሀብታሙ (ኢንጂነር) ተናግረዋል።
‹‹ከተማን ለመፍጠር ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች አንዱ ኢነርጂ (የኤሌክትሪክ ኃይል) ነው፣ ህዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ኢነርጂ አዲስ ከተማ ለመፍጠር ያግዛል፣ ሌላው የመጠጥ ውኃ ሲሆን በግድቡ የሚተኛውን ውኃ በማጣራት ለከተማ የሚያስፈልግ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ ይቻላል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የግድቡ ውኃ የሚፈጥረው የቱሪዝም መዳረሻነትና በውስጡ የሚፈጠሩት ደሴቶች፣ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኮርቻ ግድብ የሚፈጥረው ምቹ ዕይታና መስዕብ፣ የዓሳ ሀብትና የዓሳ ምርትን የማቀነባበር ሥራ የመሳሰሉት ከተሜነት እንዲፈጠር ያስገድዳሉ። ስለዚህ ይህንን ዕድል መጠቀም የግድ ነው፤›› ብለዋል።
በህዳሴ ግድቡ እያንዳንዳቸው ከአምስት ሔክታር በላይ ስፋት የሚኖራቸው 70 ደሴቶች የሚፈጠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንዱና ትልቁ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ደሴት 2,800 ሔክታር ስፋት እንደሚኖረው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው አጠቃላይ የውኃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን፣ ይህ ውኃ ከግድቡ ጫፍ ተነስቶ ወደኋላ እስከ 246 ኪሎ ሜትር ድረስ ርዝማኔ እንደሚኖረውና፣ ግድቡ ውኃውን ጨምሮ የሚያርፍበት የቦታ ስፋት ደግሞ 1,740 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሚሆን የተመለከትናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የከተማው መመሥረት ለህዳሴ ግድቡ ከለላና ጥበቃ እንደሚሆን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሚፈጠረው ከተማ ማንኛውም ዜጋ ለመኖር ቢያስብ እንዲሁም ዜጎች ቦታውን እንደ ከተማ በመመልከት በከተሜነት ቢኖሩ ሕይወታቸውን በማሻሻል ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በአካባቢው ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በማገዝ ለውጥ የማምጣት ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ ለበርካታ ኢትዮጵያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም ገልጸዋል።