Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሲቪክ ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበ

የሲቪክ ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

የሰቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማሻሻል፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዳበርና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበ፡፡

በኢትዮጵያ በመማር ማስተማር ላይ የሚንቀሳቀሱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት በአመዛኙ በግለሰቦች ትውውቅ የሚመራ እንጂ፣ በመሠረታዊነት ተቋማዊ በሆኑ መርሆች ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ የተገለጸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፍሪደም ሀውስ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር፣ የሲቪል ማኅበረሰብና ምሁራን የትብብር መድረክን መስከረም 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲካሄድ ነው፡፡

በመድረኩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የምርምር ማዕከላት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የሚዲያና የዴሞክራሲ ተቋማት ተወካዮች ሲገኙ በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በዩኒቨርሲቲ ተቋማት ጥምረት ፈጥረው፣ ለዜጎች መብት መከበርና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች 4,000 ያህል እንደሚሆኑ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲ ተቋማት ቁጥር በመቶዎች ውስጥ ቢሆንም በመካከላቸው ያለው ትብብር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የሲቪክ ማኅበረሰብና የምሁራን ትብብር መድረክ ለሰብዓዊ መብቶችና ለዴሞክራሲ ሒደቶች መጠበቅ፣ እንዲሁም ሁለቱ ዘርፎች በመደጋገፍ ሥራውን በብቃት የሚያከናውኑባቸውን መንገዶችን የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት የምክር ቤቱ የሕግና የፖሊሲ አማካሪ አቶ ዘለዓለም እሸቱ እንደገለጹት፣ ሁለቱ አካለት በበርካታ አገሮች በዩኒቨርሲቲና በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል የሚታየውን ዓይነት ጠንካራ ግንኙነት በኢትዮጵያ የተለመደ አይደለም፡፡

በመሆኑም ይህን ግንኙነት ዘላቂና መደበኛ በሆነ መንገድ ውጤት ሊያስገኙ በሚችሉባቸው ጉዳዮች፣ በተለይም በዴሞክራሲ ምኅዳር ግንባታና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ መሰማራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከዩኒቨርሲቲ ተቋማት የሚወጡ የጥናት ጽሑፎችን ወደ ተግባር በመቀየር የዕውቀት ሽግግር ማድረግና ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚሰጡ ሥራዎችን የመሥራት ልምድ ያልዳበረ በመሆኑ፣ ድርጅቶች አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጥናታዊ ጽሑፎች ከትምህርት ተቋማቱ መደርደርያ ላይ በማንሳት ሕይወት ሊዘሩባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በርካታ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ቢኖሩም ድርጅቶቹ ከዩኒቨርሲቲ ተቋማት ጋር ባለመተዋወቅና ባለመቀራረባቸው የተነሳ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል ያሉት አቶ ዘለዓለም፣ የጥናትና የምርምር ተቋማት ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ አብሮ የመሥራት ባህል ሊዳብር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ለዚህ ይረዳል ላሉት የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከዩኒቨርሲቲ ተቋማት ጋር በመተባበር የጋራ መድረክ ፈጥረዋል፡፡ በውይይት መድረኩ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ረገድ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችና ማነቆዎች፣ የሁሉንም አካላት ትብብር የሚፈልጉ ስለሆነ በሁለቱ መካከል የሚኖረው ጥምረት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡

በጥምረቱ አማካይነት ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ የጥናትና የምርምር ሥራዎች እንደሚከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊፈቷቸው ያሰቧቸውንና መፍትሔ የሚሹ ችግሮችን ለመፍታት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች፣ በትምህርት ተቋማት ዕገዛ የሚደረጉ ጥናቶች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው አቶ ዘለዓለም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...