Sunday, December 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፕሬዚዳንቷ የፓርላማ ንግግር አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ይጠበቃል!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የሁለቱም የምክር ቤት አባላትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ዲፕሎማችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግር በይፋ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፕሬዚዳንቷ የመክፈቻ ንግግር የ2015 ዓ.ም. የመንግሥት ዕቅድ አፈጻጸምና የዘንድሮ ዕቅድ አስመልክቶ መሠረታዊ ጉዳዮች እንደሚነሱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን አስጨንቀው የያዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ይታመናል፡፡ በዓለም ተደማጭ እንደሆነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ እንደሚያደርጉት ንግግር (The State of the Union Address)፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአገር አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ይታሰባል፡፡ ፋታ የማይሰጡና አጣዳፊ መፍትሔ የሚሹ በርካታ ችግሮች ባሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈንና የአገር ህልውናን ለማስቀጠል የሚበጅ ንግግር ላይ ይተኮር፡፡

ያለፈው ዓመት አፈጻጸምም ሆነ የዘንድሮ ዕቅድ ሲቀርብ ጥቅል መሆኑ ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ አሁንም ብርቱ ፈተና እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ግን መብራራት ይኖርባቸዋል፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በማኅበራዊና በሌሎች ተዛማጅ መስኮች ጥልቅ ዕሳቤ ያላቸው ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅት ሲደረግ የአገሪቱ ህልውና ጉዳይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት የአገር ብርቱ ፈተና እየሆኑ ያሉት ግጭቶችና ጥቃቶች ጉዳይ ሊሰመርበት የግድ ይላል፡፡ የሕዝባችንን በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላምና ደኅንነት፣ ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ መሥራትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ አንዱ ግጭት አበቃ ሲባል ሌላ ግጭት ውስጥ እየገባች እየደረሰ ያለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በጣም ከመክበዱ በላይ፣ ለብሔራዊ ደኅንነቷና ጥቅሞቿ ጠንቅ የሆኑ ቀውሶች መበራከታቸው ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡ በግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ የሆኑ ወገኖች ጉዳይ የአገር ዕዳ እንደሆነ ይታሰብበት፡፡

የኢኮኖሚው ጉዳይ ሲነሳ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች እየተደመጡ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልሞችና አፈጻጸሞች ከፓርቲ ዕሳቤ ቅርቃር ውስጥ ወጥተው፣ ነባራዊውን አገራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታ በማገናዘብ ዙሪያ ገብ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዙ እንዲሆኑ ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ ስለኢኮኖሚው ዕድገትም ሆነ ተስፋ ሲነገር ከተጨባጩ ሁኔታ ባይርቅ ይመረጣል፡፡ በርካታ ሀብቶችና ፀጋዎች ያሏት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲሆኑ፣ በመስኩ አንቱ የተባሉ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ተሳትፎ ጉዳይ ቸል ሊባል እንደማይገባ መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በድህነት ከሚፈረጁት መካከል ግንባር ቀደም እንደሆነች የሚታወቅ ነው፡፡ የኢኮኖሚ መነቃቃት አለ ተብሎ ተብሎ ቢነገርም፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደሚታወቀው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኖት የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ሕዝባችንን እየፈተኑ ያሉ የምግብ እጥረት፣ የመኖሪያ ቤትና የሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ጉድለት አፅንኦት ይፈልጋሉ፡፡ ችግር ውስጥ ሆነ ስለቅንጦት ማሰብ አይቻልም፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ሙስና በሚባል የዳቦ ስም የሚታወቀው ሌብነትና ዘረፋ ነው፡፡ በዕውቀታቸውና ወገብ በሚያጎብጥ ልፋታቸው ሊታይ የሚችል ለውጥ ማግኘት ያልቻሉ በርካታ ሚሊዮኖች በሚማስኑባት ኢትዮጵያ፣ በደምና በጥቅም ትስስር የተቧደኑ ወረበሎች ሚሊዮን ብሮችን እንደ ተራ ነገር ሲቀራመቱ ከማየት በላይ ህሊናን የሚያቆስል ነገር የለም፡፡ የዘረፋ ማዕድ የሆኑ የመንግሥት ተቋማትና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የጥቂት ምርጦች መጫወቻ እየሆኑ ነው፡፡ ግብር ከሚሰውሩና ከሚያጭበረብሩ፣ ኮንትሮባንድ ከሚነግዱ፣ የመንግሥት ግዥዎችንና ኮንትራቶችን በቀላሉ ከሚያገኙና እንዳሻቸው ከሚፈነጩ ባለሀብቶች ጀርባ በሥልጣናቸው የሚባልጉ የመንግሥት ሹማምንት እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ከዓመታት ልፋታቸው ጠብ የሚል ነገር ማግኘት የተሳናቸው ወገኖች እያደር ወደ ድህነት ቁልቁልት እየተገፉ፣ ንፋስ አመጣሽ የአቋራጭ መንገድ ባለሀብቶች የአገሪቱን አጥንት እየጋጡ ዝም ሲባሉ ያስደነግጣል፡፡ የፕሬዚዳንቷ ንግግር ይህንን ብሔራዊ አደጋ በቸልታ እንዳያልፈው ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ የደሃ አገር ሀብት የጥቂቶች መጫወቻ እየሆነ ስለልማትም ሆነ ዕድገት መነጋገር አይቻልም፡፡

በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ጉዳይ ሌላው ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ሲያስከብር ከማንም ቀድሞ ሕግ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ የመንግሥት የሥልጣን ምንጭ ወይም ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ በሚሰጠው ኮንትራት ተቀጣሪ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንጂ በተግባር የተረጋገጠ ባለመሆኑ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ጤና የጎደለው ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሱ የተለያዩ ዕሳቤዎች ቢኖሩም፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን በተለይ አስፈጻሚው አካል ሥራውን በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ ማከናወን አለመቻሉ አንዱ ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሕግን ያልተከተሉ እስሮች፣ የሕዝብን ሰላምና ጤና የሚጎዱ ድርጊቶችና ሌሎች አስከፊ ክስተቶች አዳማጭ እያጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ማየት ይቻላል፡፡ ብዙ ጊዜ በብልሹ አሠራሮች የሚስተዋሉ አድሎአዊነት፣ ኢፍትሐዊነትና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የችግሮች መብዛት በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጋራ መፍትሔ ለማፍለቅ ይገፋፋሉ፡፡ ሁሉንም የአገር ችግሮች ዘርግፎ ለማቅረብ ቢያዳግት እንኳ የሕዝቡን አጣዳፊ ችግሮች፣ እንዲሁም አገር አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ ያደረጉ ተግዳሮቶችን በቀና መንፋስ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥልቅ የሆነ መከፋፈል ውስጥ እንደገባች በትግራይ ክልል የተካሄደው አውዳሚው ጦርነት፣ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ፍጅት፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና ጥቃቶች ማሳያ ናቸው፡፡ ከግጭት ወደ ግጭት የሚደረገው ጉዞ የሚያበቃበትን የሚያመላክት የጋራ ፍኖተ ካርታ ሊኖር ይገባል፡፡ ማቆሚያ ባጡ ዕልቂቶችና ውድመቶች ሳቢያ እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት አገር አፍርሶ ሕዝብ ከመበተኑ በፊት ይታሰብበት፡፡ በድርቅ፣ በግጭት መፈናቀልና ሊገታ ባልቻለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እየደረሰ ያለው ጠኔና ቸነፈር ጉዳይ ችላ አይባል፡፡ አገርን እንደ ምስጥ እየበላ ያለው ዝርፊያ አደብ እንዲገዛ መላ ይበጅ፡፡ እውነተኛ ንግግርና ድርድር በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጥልቀት ይታሰብበት፡፡ ከፕሬዚዳንቷ ንግግር እነዚህና መሰል ዋነኛ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ይጠበቃሉ!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...

የስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከተካተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ ይሰጥ!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብዓዊ...

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...