Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽንኩርት ነጋዴዎች ላይ የእስር ዕርምጃ የወሰደው ሐረሪ ክልል በዳቦ ነጋዴዎች ላይም እቀጥላለሁ...

በሽንኩርት ነጋዴዎች ላይ የእስር ዕርምጃ የወሰደው ሐረሪ ክልል በዳቦ ነጋዴዎች ላይም እቀጥላለሁ አለ

ቀን:

የሽንኩርት ዋጋን ያለቅጥ አንረዋል ባላቸው የሐረር ከተማ ነጋዴዎች ላይ የእስር ዕርምጃ የወሰደው የሐረሪ ክልል ንግድ ልማት ኤጀንሲ፣ በዳቦ ነጋዴዎችም ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ፡፡

የሽንኩርት ዋጋን ያላግባብ ያስወድዳሉ ያላቸውን ሦስት ዋና ዋና ነጋዴዎችን ጨምሮ 17 የሽንኩርት አከፋፋዮችን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በሽንኩርት ነጋዴዎቹ ላይ ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ቀደም ብሎ የማወያየት ሥራ መከናወኑን፣ የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሸሪፍ ሙሜ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ባቢሌ አካባቢ የተፈጠረውን የአንድ ቀን ግጭትና መንገድ መዘጋት ተጠቅመው በሽንኩርት ላይ የተጋነነ ዋጋ ጨመሩ፡፡ ነጋዴዎቹን ቢሮ ድረስ ጠርተን ከማወያየት ባለፈ ቦታው ድረስ ባለሙያ በመላክ ሁኔታውን ገምግመናል፡፡ በጉዳዩ ላይ በመተማመን ዋጋውን ለማስተካከል ቃል ገብተው ቢሄዱም፣ ዋጋውን ባለማስተካከላቸው ወደ ዕርምጃ ተገብቷል፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

ዕርምጃ የተወሰደባቸው የሽንኩርት ነጋዴዎቹ በሐረር ከተማ ብቻ ሳይሆን፣ በዙሪያው ባሉ አካባቢዎችም የማከፋፈል ሥራ የሚሠሩ ዋና ዋና ነጋዴዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡ ከ110 እስከ 150 ብር አሻቅቦ የነበረው የአንድ ኪሎ የሽንኩርት ዋጋ ከዕርምጃው በኋላ መስተካከሉንም ነው የተናገሩት፡፡

ቢሯቸው በሕገወጥ ንግድ ለመበልፀግ በሚፈልጉና ዋጋ ያላግባብ በሚያንሩ ነጋዴዎች ላይ ተከታታይ ዕርምጃዎች እንደሚወስድ አቶ ሸሪፍ ገልጸዋል፡፡

‹‹ዳቦ ቤቶችንና ነጋዴዎችን በቀጣይ ሳምንት ቢሯችን ሰብስቦ ያናግራል፡፡ የዳቦ ግራምና ዋጋ የሚያጭበረብሩ እንዲያስተካክሉ የአንድ ሳምንት ወይም የአሥር ቀን ገደብ ይሰጣል፡፡ ማስተካከያ ባላደረጉ ላይ ግን ልክ እንደ ሽንኩርት ነጋዴዎቹ ሁሉ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ሲሉም ዕቅዳቸውን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ከሃማሬሳ ዘይት ፋብሪካ ንግድ ሚኒስቴር በፈቀደው መሠረት ቢሯቸው 238 ሺሕ ሊትር ዘይት ተረክቦ በቀጥታ ለኅብረተሰቡ ማሠራጨቱን ጠቁመው፣ በየመሥሪያ ቤቱ ለሠራተኞች፣ እንዲሁም በሸማቾች በኩል ለተጠቃሚዎች ተሠራጭቷል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በእሳት አደጋ ሱቆቻቸው የወደሙባቸውን የሐረር ሸዋበር በተለምዶ ታይዋን ካርቶን ገበያ ነጋዴዎችን መልሶ ማቋቋም የተመለከተ ጥያቄ ኃላፊው ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ከአደጋው በኋላ የተቋቋሙት ሦስት ኮሚቴዎች ጥናታቸውን ጨርሰው አለማቅረባቸውን አቶ ሸሪፍ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ በክልሉ ርዕሰ መስተደድር የቅርብ ክትትል ይደረግበታል፡፡ ሦስቱ ኮሚቴዎች ሥራቸውን ጨርሰው ሲያቀርቡ ነጋዴዎቹን መልሶ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ ይከናወናል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...