Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪዎችንና አዳዲስ ድርጅቶችን ያገናኛል የተባለው ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪዎችንና አዳዲስ የሥራ ሐሳቦች ያሏቸውን ዜጎች በአንድ መድረክ ያገናኛል የተባለው ‹‹እንቆጳ ጉባዔ››፣ የፊታችን ጥቅምት 1 እና 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዲጂታል ኢንተርፕርነርሽፕ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ባደረገው ጉባዔ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የዘርፉ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚገኙ ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የእንቆጳ ጉባዔ ኢተርፕረነሮች፣ ኢኖቬተሮች፣ ቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎችም የሚገኙበት መድረክ መሆኑንና ይህም በሥራ ዕድል ፈጠራ ሁሉም ተመሳሳይ ራዕይ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንተርፕረነርሺፕ ባህል ግንባታ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን ዕምቅ ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳደግ ዕድል እንደሚሰጥ፣ በዲጂታልና በኢንተርፕረነርሺፕ ያለውን አቅም በማሳየት የሥራ ዕድሎችን ለማጎልበትና ለማሳደግ እንደሚረዳ አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈልገው ልክ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ የጉባዔው ትልቁ ግብ ነው፡፡

ከክህሎት ሚኒስቴር በተጨማሪ የጉባዔው አዘጋጅ የሆነው የሎውሮንዶ ኤንድ አሶሼትስ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ በርናርድ ሎውሬንዶ እንደተናገሩት፣ ኢንተርፕረነርሺፕ የአሜሪካንና የጃፓንን ዕድገት የቀየረ ነው፡፡

የሳምሰንግ፣ የሶኒ፣ የፎርድ ምርቶች የተገኙት ኢንተርፕረነርሺፕ ውስጥ በነበሩ ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ተቋማትም በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዳያገኙ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡

በእነዚህ አገሮች ኢንተርፕረነሮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከሥራ ዕድል ፈጠራ በተጨማሪ፣ ኢንዱስትሪዎች እንዲቀይሩና እንዲያዘምኑ መንስዔ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ሥራዎቻቸው እንዳይታዩ ያደረገው፣ ኢንዱስትሪዎችና ጀማሪ ድርጅቶች የሚገናኙባቸው ሁኔታዎች ባለመፈጠራቸው ነው ብለዋል፡፡

‹‹እንቆጳ ጉባዔ›› የአገር ውስጥና የውጭ ኢንዱስትሪዎች እንዲገናኙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ተቋማት ከሥራ በተጨማሪ አዳዲስ ሐሳቦች ያሏቸው በመሆናቸው፣ ዘርፉን በዘላቂነት ለማዘመን ትልቅ ዕድል ይሰጣሉ ብለዋል፡፡

ጉባዔው በዩኤንዲፒ፣ በቪዛ፣ በኢት ስዊችና በሌሎች ድርጅቶች አጋርነት የሚሰናዳ እንደሚሆን፣ የሚሳተፉ አካላትም (ተቋማት) የተወሰነ ክፍያ እንደሚከፍሉ ተጠቁሟል፡፡

የዘርፉ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ሥራ ፈጣሪዎችና ሌሎች ድርጅቶች እንደሚሳተፉና በአጠቃላይ የ26 አገሮች ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች