- ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው?
- ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር።
- እና ምንድነው ያስገረመሽ?
- እኔንጃ ብቻ ተሳስተው ያቀረቡት ዜና ሳይሆን አይቀርም።
- ምንድነው?
- ሦስት ሰዎች በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ ይላል።
- ታዲያ ምኑ ነው ያስገረመሽ?
- የኖቤል ሽልማት በሰላም ዘርፍ ብቻ ነዋ የሚሰጠው።
- ተሳስተሻል።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው?
- እኛ ባለፈው ያገኘነው የሰላም ሽልማት አይደለም እንዴ?
- ነው።
- ታዲያ?
- በሌሎች ዘርፎችም ለዓለም ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሽልማቱ ይሰጣል።
- እንደዚያ ነው?
- አዎ።
- ታዲያ ለምን በሌላ ዘርፍ አትወዳደሩም?
- አትወዳደሩም?
- አዎ። ሽልማቱ በሌላ ዘርፍም የሚሰጥ ከሆነ ለምን አትወዳደሩም?
- አትወዳደሩም የምትይው ማንን ነው?
- እናንተን ነዋ! መቼም የምታሸንፉ ይመስለኛል። በዚያ ላይ ደግሞ
- በዚያ ላይ ደግሞ ምን?
- ዕድለኛ ናችሁ።
- ቀልደኛ ነሽ?
- ቀልዴን አይደለም።
- በምን ዘርፍ እንወዳደር?
- በአንዱ ብትወዳደሩ የምታሸንፉ ይመስለኛል።
- እኮ በየትኛው?
- በልማቱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ እየጠራ ያለውን የእጅ ስልካቸውን ተመለከቱና ደዋዩ አንድ ወዳጃቸው ባለሀብት መሆናቸውን ሲያውቁ አነሱት]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ሰሞኑን በተደጋጋሚ ብደውልም ስልኩ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው እያለ አስቸገረኝ።
- አዎ። ወጣ ብዬ ነበር።
- ከአገር ውጪ ነበሩ?
- አይ …እዚሁ ነው።
- ምነው፣ በሰላም?
- በሰላም ነው። የካቤኔ አባላቶች አንድ ላይ ሆነን የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት እያደረግን ነበር።
- ኦዎ … እርሶዎም እዚያ ነበሩ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- የት ማለትህ ነው?
- ፍለጋ መሰለኝ፣ ብቻ በቴሌቪዥን ተመልክቼ ነበር።
- ምን ፍለጋ?
- አዲስ ፕሮጀክት፡፡
- ለምን? ምን ያደርግልናል?
- ለማስፋፋት አስባችሁ እንደሆነ ብዬ ነዋ!
- ምኑን?
- ፕሮጀክቱን።
- የትኛውን ፕሮጀክት?
- የገበታውን ነዋ!
- የምን ገበታ ነው የምትለው?
- አንዴ ለአገር አንዴ ለትውልድ የምትሉትን ገበታ ማለቴ ነው።
- እህ… ገባኝ ገባኝ። የጉብኝቱ ዋና ዓላማው ለዚያ ባይሆንም አንድ ቦታ ግን አግኝተናል።
- የፈራሁት ሊመጣ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድነው የምትፈራው?
- አዋጡ የምትሉትን ነዋ ክቡር ሚኒስትር።
- ለምንድነው የምትፈራው? ለአገር የሚደረግ አስተዋጽኦ አይደል እንዴ?
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- ምክንያቱም እኛ እናዋጣለን እንጂ ከገበታው ተቋድሰን አናውቅም።
- አልገባኝም?
- እኛ እናዋጠለን፣ ከገበታው የሚበሉት ግን ሌሎች ናቸው ነው።
- እንዴት?
- እኔ ለገበታ አዋጣ በተባልኩ ቁጥር አዋጣለሁ።
- እሺ?
- የጀመርኩትን ፕሮጀክት ለማስፋፋት ላቀረብኩት የመሬት ጥያቄ ግን መልስ የሚሰጠኝ አላገኘሁም። ከእኔ በኋላ ጥያቄ ያቀረቡ ሌሎች ባለሀብቶች ግን ያለ ችግር ያገኛሉ።
- አንተስ ለገበታ አዋጥቻለሁ ብለህ መሬት ትጠይቃለህ?
- ምን ማድረግ ነበረብኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ቢያንስ ለአንድ ሚኒስትር ሌላ ተጨማሪ ነገር ማድረግ አለብህ።
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- የጀመረውን ቤት ግንባታ መጨረስ ሊሆን ይችላል ወይም ሌላ ነገር።
- ሌላ ነገር ምን?
- እሱ እንደምትመርጠው ሚኒስትር ይለያያል።
- ስለዚህ ሌላ ገበታ አለብህ እያሉኝ ነው።
- የምን ገበታ?
- ገበታ ለሚንስትር!