Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ የምግብ ፍጆታዎች ሽንኩርት አንዱ ነው፡፡ ሰሞኑን የሽንኩርት ዋጋ በድንገት ጣሪያ መንካቱ፣ በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን አስደንግጧል፡፡

በአዲስ አበባ በተለምዶ ‹‹መሪ ገበያ›› ተብሎ በሚጠራው የግብይት ሥፍራ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ በምርቱ የጥራት ደረጃ ዓይነት ከ120 ብር እስከ 150 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በቄራ፣ በሾላና በሌሎች የአዲስ አበባ የገበያ ሥፍራዎችም የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ መንካቱን ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል፡፡ 

ሰሞኑን የሽንኩርት ዋጋ በድንገት ሰማይ የነካበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማጣራት ሪፖርተር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ሽንኩርት አምራች አርሶ አደሮችን አነጋግሯል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አርሶ አደር አብዮት ግርማ፣ የሽንኩርት ዋጋ የናረበት ምክንያት ከዝናብ ጋር እንደሚገናኝ ይናገራሉ። አቶ አብዮት እንደሚሉት እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ በወቅቱ ከሚጠበቀው በላይ ዝናብ መከሰት በሽንኩርት የተሸፈኑ ማሳዎችን አጥለቅልቆ ምርቱን እንዳበላሸ በመጠቆም፣ በሽንኩርት ዋጋ ላይ ለታየው የዋጋ ንረት አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው ከጣለው ከፍተኛ ዝናብ በተጨማሪ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል። አርሶ አደር አብዮት በሚኖሩበት ምንጃር ሸንኮራ አካባቢዎች የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ ነጋዴዎች እንደ ልብ ገብተው ለመሸመት መቸገራቸው በገበያው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይገልጻሉ።

ምንም እንኳን አቶ አብዮት በሚኖሩበት አካባቢ የሽንኩርት ዋጋ በኪሎ 45 ብር እስከ 49 ብር እንደጥራት ደረጃው እየተሸጠ መሆኑን ቢገልጹም፣ ምርቱ ካለበት አካባቢ ውጪ ያሉ ከተሞች ከዚህ ዋጋ በእጥፍ እንደሚሸምቱ ተናግረዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ አካባቢው የፀጥታ ሥጋት ስላለበት ነጋዴዎች ሽንኩርት ገዝተው በመኪና ለማስጫን ከ50,000 እና ከዚያ በላይ እንደሚጠየቁ አስረድተዋል፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳውም የፀጥታ ችግሩ ሲሆን፣ ሰሞኑን የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ሌላው ምክንያት ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ይገልጻሉ።

በአሽከርካሪዎች ለመፍረድም ከባድ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብዮት፣ እሳቸው ከሚኖሩበት ቦታ የተጫነ ሽንኩርት በደብረ ብርሃን ከተማ ዞሮ ወደ አዲስ አበባና ልሎች ከተሞች የሚሰራጭ በመሆኑ የትራንስፖርት አግልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ለነዳጅ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ እንዲሁም፣ በአካባቢው ያለውን የሥጋት ሁኔታ ደምረው ከፍተኛ እንደሚያስከፍሉ አቶ አብዮት አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ሽንኩርት የሸመቱ ነጋዴዎች ከምንጃር ወረዳ እስከ አዲስ አበባ ገበያ ለማድረስ ከ4,500 እስከ 5,000 ብር የማይበልጥ ክፍያ እንደሚከፍሉ አሁን ግን እስከ ሃምሳ ሺሕ ብር እንደሚጠይቁ ይገልጻሉ፡፡

በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን የመስኖ እርሻ የተስፋፋበት አዲጋላ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት አቶ አሚር መሐመድ በበኩላቸው፣ እሳቸው ብቻ ሃያ ቀረጥ ወይም (ሃያ 50 ሜትር በ50 የሆነ) በሽንኩርት የተሸፈነ ማሳቸው በጎርፍ ሳቢያ መበላሸቱን ተናግረዋል፡፡

ከአቶ አሚር በተጨማሪ ማሳቸውን በሽንኩርት የሸፈኑ አርሶ አደሮችም ከባድ ዝናብ ባመጣው ጎርፍ መውደሙን ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ አሚር ገለጻ፣ አካባቢው ከአዲስ አበባና ሌሎች ገበያ በተጨማሪ በአቅራቢያው ያሉ ከተሞችም የሽንኩርት ምርት የሚገኙት ከሱማሌ ክልል መሆኑን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅትም በድሬዳዋ ከተማ ገበያ ሽንኩርት በኪሎ 100 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከወደሙ የሽንኩርት ማሳዎች ጥቂት የተረፈላቸው አርሶ አደሮችም ላለመክሰር ብለው በኪሎ 100 ብር እየሸጡ እንደሚገኙ አልሸሸጉም፡፡

ሲቲ ዞን ከጂቡቲ ወደብ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃና ለም መሬት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም፣ በአካባቢው ሰሞኑን ባጋጠመው ጎርፍ በሽንኩርት ተሸፍኖ የነበረው ማሳ መበላሸቱን አቶ አሚር አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አስጎር ወረዳ አርሶ አደር በቃና ኩምሳ እንደሚሉት፣ በወረዳው ከዚህ ቀደም ሽንኩርት የሚዘራው በበጋ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በበጋ ወቅት አብዛኛ አርሶ አደሮች ሌሎች ምርትን ወደ ማምረት በመግባታቸው፣ የሽንኩርትና የአትክልት ዋጋ ከፍ እንዲል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክረምት ሽንኩርት ለመዝራት ደግሞ የአየር ፀባይ ሁኔታ አመቺ ባለመሆኑና ቢዘራም እንኳ ውጤቱ ኪሳራ እንደሚሆን ይታወቃል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ ኅብረት ሥራ ማኅበር (ዩኒየን) ሥራ አስኪያጅ አቶ ኩምሳ ጉዲና፣ በክረምት ወቅት ሽንኩርት መዝራት ለአርሶ አደሩ አዋጭ አይደለም ይላሉ፡፡

መቂና ባቱ አካባቢዎች ሽንኩርትን ጨምሮ አትክልት በማምረት የሚታወቁ ቢሆንም፣ በክረምት ወቅት በተለይም ሽንኩርት ማምረት አክሳሪ መሆኑን አርሶ አደሩ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አይደፍረውም በማለት ያስረዳሉ፡፡

የዘንድሮ የሽንኩርት ዋጋ የተጋነነ ሆነ እንጂ በክረምት ወቅት የሽንኩርት ዋጋ ጣሪያ መንካት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በመኸር ወቅትና ዘንድሮ በበልግ ወቅት ለመስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱና ከዚያ በኋላ ደግሞ ሽንኩርት ለማምረት የክረምት መግቢያ ሰዓት በመድረሱ የሽንኩርት ምርት እጥረት መፈጠሩን ያስረዳሉ።

በክረምት ወቅት ሽንኩርት ቢተከልም እንኳን በሽታውን መቋቋም ስለማይችል፣ ከመሬት ሳይወጣ እንደሚበሰብስ አስረድተዋል፡፡

ዩኒየኑ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሌሎች ድርጅቶች ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችን የማቅረብ ኮንትራት ቢኖራቸውም፣ በዚህ ወቅት ምርት ባለመኖሩ ለድርጀቶቹ ጭምር ማቅረብ እንደተቸገሩ ገልጸዋል።

ዩኒየኑ ከመቂና ባቱ በመውጣት ወደ አርሲ ሁሩታ አካባቢዎች ሄደው ለመግዛት ማቀዳቸውና እነዚህ አካባቢዎች ምርቱ ገና ከዚህ በኋላ የሚዳረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምዕራብ ሸማቾች ዩኒየን የግብይት ባለሙያ አቶ ሰኚ ባይሳ በበኩላቸው፣ በዝናብ ወቅት የሽንኩርት ምርት እጥረት ማጋጠሙ የተለመደ መሆኑን ይገልጻሉ።

በዋናነት የሽንኩርት ዋጋ መናር በተለይ በክረምት ወቅት የሚያመርቱ ቦታዎች በጎርፍ አደጋ በመጥለቅለቃቸው ነው ብለዋል፡፡

አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ አካባቢ የሚመረተው የቀላቶ ሽንኩርት በጎርፍ መውደሙ እንደተነገራቸው የገለጹት አቶ ሰኚ፣ ምንጃር ሸንኮራ አካባቢ ደግሞ በፀጥታ ምክንያት ምርቱን ወደ ገበያ ማውጣት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ አንዳንዶቹ የገዙትን ሽንኩርት ለማምጣት የትራስፖርት ዋጋ እስከ 50,000 ብር እንደሚጠየቁ ገልጸዋል፡፡

ዩኒየኑ ባለው ኔትወርክ በስልክ እንደሚገበያዩ ገልጸው፣ ዋጋ በጣም ስለናረ በአሁን ጊዜ ከመግዛት መቆጠባቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ሰኚ ገለጻ፣ በአርሶ አደሩም በኩል ወደ ስንዴ የማድላት ሁኔታ መኖሩንና ይህም እንደ ሽንኩርት ዓይነት ምርቶች ላይ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

በዚህ ወቅት የሽንኩርት ምርት የሚነሳባቸው አካባቢዎች ምንጃርና አርሲ ቡታ ብቻ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም ቦታዎች ሸምቶ ለመምጣት የመኪና ኪራይ ዋጋው የተጋነነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዩኒየኑ ለዘመን መለወጫ ሽንኩርት በኪሎ 54 ብር ከ50 ሳንቲም ሸምተው በዚሁ ዋጋ ለሸማቾች ማቅረቡን፣ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ዋጋው ከፍ በማለቱ አለመግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የተለያዩ ሱፐር ማርኬቶችና የገበያ ማዕከላት የሽንኩርት ዋጋ እስከ 140 ብር እየተሸጠ ቢሆንም፣ የፐርፐዝ ብላክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከገበሬው በተሸጠው የችርቻሮ መደብሮች በኪሎ 25 ብር እየሸጠ ይገኛል፡፡

በዚህም ምክንያት በአንድ አገር ውስጥ የዚህን ያህል የዋጋ ልዩነት መኖር ምክንያቱ በርካቶችን ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡

ከ100 እስከ 140 ከዚያ በላይ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ሲቸበችቡ የቆዩት ምክንያታቸው የሽንኩርት መብቀያ ወቅት አለመሆኑና የፀጥታ ችግር ሳቢያ አንድ መኪና ሽንኩርት ለማስጫን እስከ 50,000 ብር መጠየቃቸውን ይገልጻሉ፡፡

ፐርፐዝ ብላክ በአዲስ አበባ የገበያ ማዕከሎቹ አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ25 ብር በመሸጥ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ድርጅቱ የሽንኩርት ምርትን በዚህን ያህል ዝቅተኛ ዋጋ ሊመሸጥ ያስቻለው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉትን የመስኖ ማሳ ተጥቀሞ በማምረቱና ለማጓጓዝም የራሱን ትራንስፖርት በመጠቀሙ እንደሆነ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የፐርፐዝ ብላክ ባለድርሻና የሕግ አማካሪ የሆኑት ኤርሚያስ ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ዓላማ እድርጎ የተነሳ በመሆኑ ያልተገባ ትርፍ የማግኘት ፍላጎት የለውም፣ ስለሆነም መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን በቅናሽ ዋጋ እያቀረበ ነው፡፡

ሰሚት፣ አያት፣ ሜክሲኮ፣ ዓድዋ ድልድይ፣ ሳር ቤትና ላፍቶና ቡልቡላ በሚገኘው ከገበሬው ሱፐር ማርኬቶች ሽንኩርትና ሌሎችም የምግብ ፍጆታዎችን በቅናሽ እያቀረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

ፓስታ፣ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ በቅናሽ እየቀረቡ መሆኑን፣ እነዚህ ፍጆታዎች ከሌሎች ገበያዎች አንፃር ከአሥር ብር እስከ ሃምሳ ብር ድረስ የዋጋ ልዩነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኤርሚያስ (ዶ/ር) ገለጻ፣ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ማለትም ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመንና ሌሎችም ምርቶች ለገበያ ሲቀርቡ ከአንድ ዲጅት ቁጥር መብለጥ የለባቸውም በማለት ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል፡፡ 

ይህም ማለት የአንድ ኪሎ የሽንኩርት ዋጋ ከአሥር ብር ባነሰ ዋጋ ሊሆን ይገባል የሚል ዕምነት በድርጅቱ በኩል መያዙን የገለጹት የሕግ አማካሪው፣ ፐርፐዝ ብላክ አሁን አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ25 ብር ማቅረቡ ካለው ሁኔታ አንፃር ተመረጠ እንጂ ይህም ዋጋ ውድ ነው ብለዋል። 

ፐርፐዝ ብላክ ሽንኩርት በ25 ብር ለሸማች ያቀረበበት ምክንያት ሰዎች ገዝተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነው ያሉት ኤርሚያስ (ዶ/ር)፣ መንግሥትም በተለያዩ አደባባዮች በኪሎ 45 ብርና ከዚያ በላይ ለሸማች ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

በፐርፐዝ ብላክ ሱፐር ማርኬቶች በፓኬጅ ደረጃ የቀረቡ አማራጮች መኖራቸው፣ ብዙ ዓይነቶች ምርቶችን በጥቅል የያዙ አማራጮች መቅረባቸውን የገለጹት ኤርሚያስ፣ በጥቅል የሚቀርቡት ምርቶች ተደምረው በ446 ብር እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ከውጭ አምስት ኪሎ ሽንኩርት አንድ ሸማች ለመግዛት ቢፈልግ በትንሹ እስከ 600 ብር ሊያወጣ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከገበሬው ሱፐር ማርኬት ፓኬጁን (ጥቅሉን) እንኳን መግዛት ቢፈልጉ በቅናሽና በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብ፣ ነገር ግን ፓኬጁን ያልፈለጉና ሽንኩርት ብቻ ከፈለጉ መግዛት እንደሚቻል የሕግ አማካሪው አስረድተዋል፡፡

የፓኬጁ መዘጋጀት በዋናነት በጥቅሉ ውስጥ የሚገኙ ፍጆታዎች ሙሉ ቅናሽ የተደረገባቸው በመሆናቸው ለሸማቹ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው ከፓኬጁ ውጪ ምርቶችን በተናጥል መግዛት እንደማይቻል ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን፣ ለተቋማት ጭምር ሽንኩርት ብቻ መሸጣቸውን በምሳሌነት አስረድተዋል፡፡

የአንዳንዱ የሸማች ጥያቄ የነበረው ሽንኩርት ብቻውን የመግዛት እንዳልሆነ የገለጹት፣ ከአምስት ኪሎ በላይ መግዛት ቢፈልጉ ለምን? እገደባለሁ የሚል ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ለአንድ ሸማች ከአምስት ኪሎ በላይ መሸጥ ያቆመው አንዳንዶች በብዛት ገዝተው አትርፈው እየሸጡ መሆናቸውን በጥቆማ በመደረሱ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ለቡ አካባቢ በሚገኘው ሰባቱ ሱፐር ማርኬቶች በቀጥታ እየገዙ ውጭ ላይ ዋጋ ጭማሪ አድርገው ሲሸጡ በመያዛቸው መጠኑ እስከ አምስት ኪሎ ግራም ብቻ መገደቡን ተናግረዋል፡፡

የፐርፐዝ ክሊክ አመራር ውይይት በማድረግ ሁሉም ሸማች ተጠቃሚ እንዲሆን ለአንድ ሸማች ከአምስት ኪሎ በላይ እንዳይሸጥ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

የዋጋው ቅናሽ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለዚህ ምላሽ የሰጠ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎቸ በዘመናዊ ከሚያመርትበት ቦታዎች በራሱ ትራንስፖርት ማቅረቡ፣ ለዋጋው ዝቅተኛ መሆን እንደ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከጥቂት ዓመት በኋላ የሽንኩርት ዋጋ በኪሎ ዘጠኝ ብርና ከዚያ በታች የመሸጥ ዕቅድ እንዳለውና ሌሎችም ተመሳሳይ ምርቶች ከአሥር ብር ባነሰ ዋጋ በመሸጥ ታሪክ መሥራት እንፈልጋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በፐርፐዝ ብላክ በተለያዩ አገሮች አካባቢዎች በማሳዎቻቸው ባህላዊ ከሆነው የአስተራረስ ዘዴ ይልቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ስለሚጠቀም አጠቃላይ መጪው ዝቅተኛ መሆኑን የምርቱ መቀነስም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ አስረድተዋል፡፡

የሽንኩርትና መሰል ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ቅናሽ ቀጣይነት እንዳለውና ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ምርቶችን በቅናሽ ሲሸጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች