Wednesday, December 6, 2023

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በተሻለ ሊወክለው የሚገባ የፖለቲካ ማኅበር መፈጠር አለበት የሚለው ጥያቄ በአማራ ተወላጆች ዘንድ ሲብላላ ነው የኖረው፡፡ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ተብሎ በእነ አሥራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር) ከተመሠረተው ፓርቲ በኋላ አማራ በአግባቡ የሚወክለው ፓርቲ አጥቷል ሲባልም ቆይቷል፡፡

ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ መአሕድ ስያሜውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብሎ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነት ራሱን መለወጡ ይታወሳል፡፡ በሒደት ግን በተለይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የመኢአድም ሆነ የሌሎች ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱ አይዘነጋም፡፡

ይህን ተከትሎ ነበር እንግዲህ አማራ በአግባቡ የሚወከልበት፣ መብትና ጥቅሞቹ እንዲረጋገጡ አበክሮ የሚሠራ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል የሚል ሐሳብና እንቅስቃሴ መወለድ የጀመረው፡፡ ይህ ፍላጎት እየጨመረ የመጣበት ጊዜ ግን ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ልክ ግዙፍና ኃይለኛ የነበረበት ወቅት መሆኑ ይወሳል፡፡

ኢሕአዴግ በወቅቱ የፖለቲካ ልዩነቶችን የሚጋፈጥበት ትዕግሥት እያጣ አፋኝ የሆነ ሥርዓት እያሰፈነ እንደነበር ብዙ የተባለበት ነው፡፡ አማራ ጥቅሙን ለሌሎች አሳልፎ በሚሰጠው ብአዴን ብቻ መወከል የለበትም፣ የራሱ ሀቀኛ ተወካይ ሊኖረው ይገባል ያሉ ወጣቶች አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት ተነሱ፡፡ እነዚህ ወጣቶች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለመፍጠር ባህር ዳር ከተማ ተሰባሰቡ፡፡

የመንግሥት ጆሮ ጠቢዎችና ደኅንነቶች የፓርቲውን ምሥረታ ሒደትን እንዳያስተጓጉሉት ለማድረግ አንድ ዘዴ መፈለግ ነበረበት፡፡ በአንድ ጀልባ ተሳፍሮ ጣና ሐይቅ ላይ ከሰውም ከቴክኖሎጂ ተነጥሎ ርቆ ውሎ የፓርቲውን የምሥረታ ስብሰባ ማድረግ ወጣቶቹ የወሰዱት አማራጭ ሆነ፡፡

እንዲህ ዓይነት አስገራሚ የምሥረታ ታሪክ ያለፈው አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እነሆ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ፓርቲው ሲመሠረት በብዙ የአማራ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት ያሳደረ እንደነበር ይነገራል፡፡ ፓርቲው የአማራ ሕዝቦችን ጥቅምና መብት ከብአዴን በተሻለ ያስጠብቃል የሚል አመለካከት ፈጥሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ በጊዜ ሒደት ይህ ስሜት እየተቀዛቀዘ ቢመጣም አብን መመሥረቱ አሳድሮት የነበረው ተስፋና ስሜት ከፍተኛ መሆኑ ይወሳል፡፡ አሁን ይህ ፓርቲ ‹‹ብአዴን ቁጥር ሁለት›› የሚል ተቀፅላን ሲሰጠው ከማየት በተጨማሪ፣ የአማራ ማኅበረሰብ የሚወክለው ሀቀኛ ፓርቲ አጥቷል የሚል ቀቢፀ ተስፋ ነው በብዙዎች ዘንድ ሲንፀባረቅ የሚታየው፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወዴፓ) የተባለ አዲስ ፓርቲ ምሥረታውን ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው የአማራ ክልል በዋናነት የወሎ አካባቢ ማኅበረሰብን መብትና ጥቅም አስጠብቃለሁ ብሎ የተነሳ መሆኑን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ፓርቲ ምሥረታውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ግን የአማራ ሕዝብ የሚወክለው ተጨማሪ ፓርቲ አገኘ ከሚለው ይልቅ፣ አንድነቱን ጠብቆ እንዳይቀጥል የሚያደርግ አደጋ እንደገጠመው በሥጋትነት እየተነሳ ነው፡፡

የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን መመሥረት የተፈለገው ክልሉን ብሎም የአማራ ሕዝቦችን የበለጠ ለመከፋፈል ታስቦ ነው የሚል ስሞታ በስፋት እየተነሳ ሲሆን፣ የአማራ ክልልን በጎጥና በቀዬ ከመከፋፈል በተጨማሪ በአንድነት ቆሞ ለመብቶቹና ለጥቅሞቹ እንዳይታገል እንቅፋት መፍጠር በመፈለጉ ነው ፓርቲው የተፈጠረው የሚል ስሞታም እየተነሳ ነው የሚገኘው፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ነፃነት ጣሰው ግን፣ ሁኔታው ከዚህ ፍጹም በተቃራኒው እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሪፖርተር ቢሮ ሪፖርተር ቲዩብ ስቱዲዮ በአካል ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ፓርቲው የወሎ ማኅበረሰብን ብሎም የመላው አማራ ሕዝብን እንደሚወክል ተከራክረዋል፡፡

‹‹የፓርቲያችን ምሥረታ ዋና ዓላማ የወሎ ሕዝቦች ተሰደውና ተበትነው በብዙ ችግር መኖራቸውን ታሳቢ በማድረግ፣ እንዲሁም በአካባቢያቸው የልማት ዕጦት እያጋጠማቸው መኖራቸው ሊያበቃ ይገባል በሚል ነው፡፡ በዋናነት ሰፊ የልማት ፕሮግራሞችን ለወሎ ይዘን ነው የተነሳነው፤›› ብለዋል፡፡

ርዕዮተ ዓለማችን ‹‹ዴሞክራት›› ነው ሲሉ በአጭሩ የጠቀሱት አቶ ነፃነት፣ ‹‹ፌዴራል ሥርዓትን ነው የምንከተለው›› በማለትም አክለዋል፡፡ ‹ከሌላው ለየት የሚያደርገን ልማታዊ መሆናችን ነው፤›› ሲሉም ነበር የተናገሩት፡፡

ለፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ነፃነት ፓርቲያችሁ ብልፅግና ጠፍጥፎ የሠራው ነው ይባላል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የፓርቲያቸው ምሥረታ ሒደት ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን የጠቀሱት አቶ ነፃነት፣ ‹‹ሲጀመር ብልፅግናም አንድ ፓርቲ ነው፡፡ እኛን ለማደራጀት የሚችልበት አቅምም ሆነ ኃይል የለውም፡፡ የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ራሱን ችሎ የተመሠረተ ነው፤›› በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ራሳችንን ችለን ነው የቆምነው ቢሉም ነገር ግን የፓርቲው መመሥረት የቀደሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረት ሒደትን እያስታወሰ ይገኛል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት በሕገ መንግሥት ጭምር ዕውቅና አግኝቶ ቢታወጅም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ሥልጣን ከያዘው ኃይል ተፅዕኖ ተላቀው አያውቁም ነው የሚባለው፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች መንግሥት በቀጥታ ተፅዕኖ በሚያሳድርበት በምርጫ ቦርድ አማካይነት ለፈለገው ቡድን ዕውቅና እየሰጠ ለማይፈልገው ደግሞ ዕውቅና እንደሚነፍግ በሰፊው ሲነገር ቆይቷል፡፡ መንግሥት አንዳንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመከፋፈል በውስጣቸው ጣልቃ እየገባ ለመከፋፈል ይዳርጋቸዋል የሚል ስሞታም ሲሰማ ነበር፡፡

የአንዳንዶችን ሕጋዊ ዕውቅና፣ ማንነትና ቢሮ ነጥቆ ለሚፈልጋቸው የፖለቲካ ማኅበራት እየሰጠ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አዳክሟል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ይቀርባል፡፡

‹‹ኦብኮ፣ ኦብኮና ኦብኮ›› በሚል ርዕስ እንደ ሪፖርተር ያሉ ጋዜጦች እስኪዘግቡት ድረስ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ክፍፍል ከፍተኛ መነጋገሪያ ፈጥሮ ነበር፡፡ የእነ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬና የእነ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የፓርቲ ይገባኛል ውዝግብ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ጡዘት ውስጥ ገብቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ‹ተልዕኳችንን ጨርሰናልና መንግሥት ቀሪ ክፍያችንን በገባው ቃል መሠረት ይፈጽምልን› በማለት ያቀረቡት የንዘብ መጠየቂያ ደብዳቤ በጋዜጦች ታትሞ እስኪጋለጥ ድረስ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ኦብኮን ለመከፋፈል ለተወሰኑ ቡድኖች ድጋፍ አድርጓል የሚለው ጉዳይ ሲያወዛግብ ነበር፡፡

በምርጫ 97 ማግሥት ኢሕአዴግን በከባዱ የተቀናቀነው የቅንጅት ፓርቲ ምዝገባ ጉዳይ የማይረሳ ውዝግብ መፍጠሩ አይረሳም፡፡ ቅንጅት ሕጋዊ ዕውቅናውን በማግኘት በምርጫው ወቅት የነበረውን ማንነትም ሆነ ጥንካሬ ሳያጣ እንደሚቀጥል ብዙ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቅንጅት የተባለው ሕጋዊ ዕውቅና የሚገባው ለእነ አቶ አየለ ጨሚሶ ነው የሚል ፍርድ በመሰጠቱ፣ በስተመጨረሻ ትልቁ ቅንጅት የመበታተንና የመዳከም አደጋ እንደገጠመው አይዘነጋም፡፡

ከቅንጅት የወጡ ሰዎች ያደራጁትና በዋናነት ወጣቶችን አሰባስቦ የነበረው የአንድነት ፓርቲም ቢሆን በመጨረሻ የመፍረስ አደጋ የገጠመው፣ በዕውቅና ውዝግብ መሆኑ ይወሳል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት አንድነትን ወክለው የገቡትና በፓርላማው ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን፣ ‹‹ፓርቲያችንን በተሳካ መንገድ በማፍረስዎ እንኳን ደስ አለዎት፤›› ሲሉ በፓርላማ ስብሰባ እንደተናገሩት ሁሉ አንድነት በውዝግብ ፈርሶ ቀረ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ የማንነትና የዕውቅና ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የመከፋፈል አደጋ ገጥሞት ያውቃል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ በታየው የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ባህል አንድ ማኅበረሰብ የራሴ የሚለው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖረው ሆን ተብሎ የመከፋፈል ሥራ ይከናወን ነበር የሚል ስሞታ ሲስተጋባ ቆይቷል፡፡

ጠንከር ብለው የወጡ ወይም የተደራጁ፣ የመንግሥትን ሥልጣን ይቀናቀናሉ ተብለው የሚገመቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊ ዕውቅናና በማንነት ባለቤትነት እየተሳበበ ሆን ተብሎ እንዲከፋፈሉ ይደረጋል የሚል ስሞታም ይቀርባል፡፡ በዋናነት ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ የአማራ ሕዝብ (ክልል) ጠንካራ ፓርቲ እንዳይኖረው፣ ሆን ተብሎ የፖለቲካ አሻጥር ይሠራል የሚል አቤቱታ ነው የሚሰማው፡፡

ይህን ሐሳብ የሚቃወሙት አቶ ነፃነት ጣሰው ግን ወሎን ማሰባሰብ አማራንም ሆነ የአማራ ፖለቲካን መከፋፈል አለመሆኑን ሞግተዋል፡፡ ‹‹ወሎ ላይ መሥራት ከአማራ መነጠል ማለት አይደለም፡፡ እኛ ልማታዊ ፓርቲ ነን፡፡ ልማት ከቀዬ በመጀመር ወደ ክልል፣ ከክልል ደግሞ ወደ አገር እንዲስፋፋ በማድረግ የተለያዩ ሕዝቦች እንዲተሳሰሩ እናደርጋለን እንጂ ማንንም አንከፋፍልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ወሎ አብሮነትን እንጂ ጠብ አያውቅም፡፡ በየሄደበት አካባቢ ጥላቻ አያውቅም፡፡ ለዘመናት ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርን ያውቅበታል፡፡ ፓርቲያችን እነዚህን እሴቶች ወደ ክልሉና ወደ መላው አገሪቱ እንዲሰፉ ያደርጋል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ ‹‹ወሎን እንሠራለን ብሎም እንገነባለን ስንል በምትኩ ኢትዮጵያን እንሠራለን ማለት ነው፤›› በማለት ነበር የፓርቲያቸው ምሥረታ ከአማራ መከፋፈል ጋር እንደማይገናኛ ለማስረዳት የሞከሩት፡፡

አሁን በአማራ ክልል ደም አፋሳሽ ጦርነት በፋኖ ኃይሎችና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ደግሞ የአማራ ክልል ፖለቲካ በተገቢው ሁኔታ የሚወክለው ጠንካራ የፖለቲካ ማኅበር ማጣቱ ይወሳል፡፡ የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ የአማራ ብልፅግና የዘረጋው መንግሥታዊ መዋቅር ላልቶ መደበኛ አገልግሎት መስጠት የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱም ይነገራል፡፡ ከአማራ ብልፅግና በመለስ ሲመሠረት ብዙ ተስፋ የተጣለበት አብን ፓርቲም ቢሆን የብልፅግና አገልጋይ ሆኗል የሚል ትችት እየወረደበት ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተጨባጭ አይደለም ቢባል እንኳን በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ሕዝብን አሰባስቦ ማታገል የሚችል ጠንካራ የፖለቲካ አደረጃጀት አለመኖሩን ብዙዎች ይቀበሉታል፡፡ ክልሉ በአግባቡ የሚወክለው ጠንካራ ድርጅት ያጣ ስለመሆኑ ነው በሰፊው የሚነገረው፡፡

ይህን ሁኔታ ከፓርቲያቸው አመሠራረት ጋር በማያያዝ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ ነፃነት፣ ክልሉ እያጋጠመው ባለው ውጣ ውረድ የተነሳ የወሎ አካባቢ ማኅበረሰብ ብዙ በመጎዳቱ የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ለመመሥረት አንድ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል በወቅቱ ያለውን ግጭት አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ደም አፋሳሽ ግጭት በማድረግ ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ይመለሳል ብለን አናምንም፤›› ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ‹‹ሁሉም ኃይሎች ግጭት አቁመው ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጡ እንጠይቃለን፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው ወይም በኢሕአዴግ ዘመን ‹‹የዴድ፣ የዴንና የዴግ›› ፖለቲካ ማኅበራት መፈልፈል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ መባሉ ይታወሳል፡፡ ብዙዎች ‹‹ኦርጅናሉ ነው ወይስ ተለጣፊው›› እያሉ እስኪጠይቁ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅጂ (ኮፒ) መበራከቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ጨምሮ እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡

ለአብነት ያህል በእነ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ይመራ የነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት የተባለውን ከአሥር ያላነሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን አሰባስቦ የነበረውን የፖለቲካ ማኅበር እንደ ምሳሌ ብዙዎች ያወሱታል፡፡ በጊዜው ልክ የዚህ ድርጅት አምሳያ የሆነ የንቅናቄ ድርጅቶችን ያሰባሰበ ደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተባለ የፖለቲካ ማኅበር በኢሕዴግ መፈጠሩንም እነዚህ ወገኖች ያወሳሉ፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ ሆን ተብሎ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለማዳከምና ማኅበረሰቡን በሀቀኝነት የሚወክሉ ፓርቲዎች ለማሳጣት መሆኑ በስፋት ይነገር ነበር፡፡

ቀደም ሲል የወሎ ኅብረት የሚል ማኅበር በማደራጀት አሁን ደግሞ የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመፍጠር እያደገ የመጣው የወሎ አካባቢን ለብቻው የሚወክል የፖለቲካ ኃይል ለመፍጠር የተጀመረው እንቅስቃሴ ምን ውጤት ይኖረዋል የሚለው ጥያቄ በጊዜ ሒደት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ የፓርቲው አመራሮች ወሎንም ሆነ አማራን የመከፋፈል ወይም ኃይል የማሳጣት ዓላማ እንደሌላቸው ለማሳመን ሲጥሩ፣ በተቃራኒው በሚያዩዋቸው ወገኖች ግን በርካታ ጥርጣሬ እየቀረበባቸው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -