Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ነው፡፡ የማዕከሉ ባለቤትነት ላይ ቀደም ሲል ተነስቶ የነበረ የይገባኛል ጥያቄ ቢኖርም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በይዞታው ላይ በሕጋዊ ባለቤትነት የተመዘገበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ነው፡፡

የዚህን ማዕከል አገልግሎት ለማጠናከር የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ የስምምነት ማዕቀፎች የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንዲያስተዳድረው ተወስኖ በዚሁ አግባብ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ 

በተለይ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ስምምነቶቹ እየታደሱ፣ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲያስተዳድረውና ከማዕከሉ የሚገኘውን ገቢም ከአስተዳደሩ በእኩል ተካፋይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ የኤግዚቢሽን ማዕከል ዙሪያ የሚገኘውን የመስቀል አደባባይ የተሽከርካሪ ማቆሚያና (ፓርኪንግ) እና ተያያዥ አገልግሎቶችን በተመሳሳይ ሁኔታ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲያስተዳድረው አደርጓል፡፡

ከሰሞኑ ግን የከተማ አስተዳደሩ የሰየመው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቦርድ፣ በከተማ አስተዳደሩና በንግድ ምክር ቤቱ መካከል የነበረውን ውል ማቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ ለንግድ ምክር ቤቱ መላኩን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡ ለንግድ ምክር ቤቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የቆየው ውል ተቋርጧል።

ይህ የአስተዳደሩ ውሳኔ ያልተጠበቀ በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤቱ አካባቢ ድንገጤ ስለመፍጠሩም ሁኔታውን የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ ለተፈጠረው ድንጋጤ ዋና ምክንያት የሆነው ደግሞ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከኤግዚቪሽን ማዕከሉ በየዓመቱ ከወጪ ቀሪ 50 በመቶ ገቢ ያገኝ የነበረ በመሆኑ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተላለፈው ውሳኔ ግን ይህንን ጥቅም የሚያሳጣ በመሆኑ በንግድ ምክር ቤቱ አጠቃላይ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያሳርፍ እኚሁ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያመለክታሉ፡፡    

ንግድ ምክር ቤቱና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የስምምነት ማዕቀፎች ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠሩ መቆየታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ የሚገኘውን ጥቅም በተመለከተ ንግድ ምክር ቤቱ ይፋ ካደረጋቸው ሪፖርቶቹ መገንዘብ እንደሚቻለው የማዕከሉ ዓመታዊ ገቢ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ተችሎ ነበር፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥም ወጪ ተቀንሶና የከተማ አስተዳደሩ ድርሻ ተከፍሎ በዓመት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኝበት ነበር። አሁን ግን ማዕከሉን የማስተዳደር ኮንትራቱ እንዲቋረጥ በመወሰኑ ለንግድ ምክር ቤቱ ጉዳት ነው ተብሏል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ማዕከሉን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ገቢውን ማሳደግ መቻሉንና ለአስተዳደሩም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆኑን የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፣ በቅርቡ የንግድ ምክር ቤቱ 75ኛ እንቅስቃሴና አጠቃላይ ታሪካዊ ዳራን ባመላከተበት መረጃው ላይም ይህንኑ አሥፍሯል፡፡

በተለይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኤግዚቢሽን ማዕከልን በማኔጅመንት ኮንትራት በ1998 ዓ.ም. ተረክቦ ከማስተዳደሩ በፊት፣ ማዕከሉ ለጥቂት ዓመታት በኪሳራ መቆየቱን፣ አንዳንዴም ወጪና ገቢ እየሸፈነለት የዘለቀ ሲሆን፣ አጠቃላይ ገቢውም ቢሆን አነስተኛ እንደነበር የሚገልጸው የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ፣ ዓመታዊ ገቢውም ከአራት ሚሊዮን ብር ያልበለጠ እንደነበረ ያስታውሳል፡፡

ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በርካታና ልዩ ልዩ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ለማካሄድ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አባላትና ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸውና ኩነቶችን ማካሄድ በመቻሉ ነው፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር አብረው የሚሠሩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ግንኙነታቸውን በማጠናከር፣ የውጭ ኩባንያዎችን በተለያዩ ንግድ ትርዒቶች እንዲሳተፉ ማድረጋቸውም የንግድ ትርዒቶች እንዲበራከቱና ገቢም እንዲያድግ አስችሏል፡፡ በኦዲት ሪፖርት መሠረትም የፋይናንስ ገቢ በአማካይ ከ100 በመቶ በላይ እያደገ በመሄድ ላይ መሆኑን የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡፡

ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ በተጨማሪ በዙሪያው የሚገኘው የመስቀል አደባባይ አዲስ ፕሮጀክት የፈጠራቸውን የገቢ ምንጮችን (ማለትም የመስቀል አደባባይ ፓርኪንግ መሠረተ ልማትን) አንድ ላይ አስተሳስሮ ለማስተዳደር ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረበው ፕሮፖዛል ተቀባይነት አግኝቶ ውል ፈርሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የዚህም ውል ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ጋር አብሮ መቋረጡ ታውቋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የንግድ ትርዒት ሥራ እንዲከናወን ለማድረግ ኃላፊነቱን በመውሰድ ሲሠራ የቆየ በመሆኑ የአስተዳደር ኮንትራቱ መቋረጥ የከተማ አስተዳደሩ የሚያገኘውን ተጨማሪ ገቢ ሊያሳጣው እንደሚችል ይታመናል፡፡ 

በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረውን ውል የከተማ አስተዳደሩ ለምን ለማቋረጥ እንደወሰነ ለመረዳት በአዲስ አበባ አስተዳደር የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በቦርድ ሰብሳቢና የከተማዋ የንግድ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ቢኒያም ምክሩ አነጋግረናቸዋል። አቶ ቢኒያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ወደ እዚህ ውሳኔ የደረሰው ከተማውን በሚመጥን መልኩ የኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ለመገንባት ነው፡፡

ዋናው ጉዳይም ቦታውን ለማልማት እንጂ፣ ከንግድ ምክር ቤቱ ለመንጠቅ ታስቦ የተወሰነ አለመሆኑንም አቶ ቢንያም አመልክተዋል፡፡ በማዕከሉ ዙሪያ የነበውን ሒደትና አሁናዊ ውሳኔ በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ከ18 ዓመታት በፊት የገበያ ማዕከላትን ለማስተዳደር ብዙ ልምድ ስላልነበረ፣ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲያስተዳደረው በውል ተሰጥቶት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ውሉም በየጊዜው እየታደሰ የቆየና መጀመርያ የአምስት ዓመት፣ ቀጥሎ የሁለት ዓመትና የዓመት እየተባለ እየታደሰ የመጣ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት  ንግድ ምክር ቤቱ ማዕከሉን የማስተዳደር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ተጨማሪ ልማቶችን በማልማት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በጋራ ሰፊ ልማቶችን ለማልማት ታስቦ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት የቦርድ ሰብሳቢው ይህ ግን ሊሆን አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ 

‹‹እስካሁን ድረስም ንግድ ምክር ቤቱን የማስተዳደሩን ሥራ ብቻ ነው ሲሠራ የቆየው፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ሥራው የሚሠራው ግን ለማዕከሉ በተመደበለት ሥራ አስኪያጅና ሠራተኞች ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡  

ነገር ግን ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጥቶ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ ንግድ ምክር ቤቱ 50 በመቶውን ትርፍ ሲጋራ መቆየቱን የሚገልጹት አቶ ቢኒያም፣ ስለዚህ አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ አሁን ያሳወቀው የገንዘብ ክፍፍል ጉዳይ ሳይሆን፣ ቦታውን በጋራ እናልማ የሚል ሐሳብ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡ አስተዳደሩ የመንግሥትና የግል አጋርነት የሚባል የፕራይቬት ፐብሊክ ፓርትነርሽፕ በማፅደቅ፣ በተለይ በሆስፒታል አገልግሎትና በቤቶች ልማት ላይ ከባለሀብቶች ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ 

በዚህ ዓይነት መንገድ አስተዳደሩ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በመሆን ታሪካዊ የሚባለውን የኤግዚቢሽን ማዕከል ከተማውን በሚመጥን መልኩ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንስ ሴንተር እንዲገነባ በመወሰን፣ ይህንንም ግንባታ ለማካሄድ ቅድሚያ ለንግድ ምክር ቤቱ ይሰጥ ብለው ሊወስኑ ችለዋል፡፡ ቦታውና ንብረቱ የከተማው አስተዳደር ቢሆንም፣ ንግድ ምክር ቤቱ ሲያስተዳድር የቆየ በመሆኑ፣ የንግድ ኅብረተሰቡን አስተባብረው በጋራ ማልማት የሚችሉ መሆኑ ተገልጾላቸዋል፡፡ የሰሞኑ ውሳኔያቸውም ይህ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቢንያም፣ ከዚህ በኋላ ኪራይ እያከራዩ ይህንን ገቢ የመክፈሉ ሒደት ግን እንዲቋረጥ መደረጉን አክለዋል፡፡ 

ዘለቄታው የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቀውም ኤግዚቢሽን እያሳየና፣ እስክሪን እያከራየ በሚገኘውን ገንዘብ ባለመሆኑ፣ ዘላቂ ጥቅም የሚኖረው ቦታው ሊለማ ሲችል ብቻ ስለሆነ፣ አስተዳደሩ ቦታውን ለማልማት ወስኗል ይላሉ፡፡ ልማቱንም በጋራ ለማካሄድ እንዲቻል ለንግድ ምክር ቤቱ ቅድሚያ ዕድል ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡  ይህንን ማድረግ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ምላሻቸውን እንዲሰጡ እየጠበቀ መሆኑን ካደረጉት ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

እስካሁን የነበረው ውል ሊቋረጥ የሚችለውም ቦታውን ማልማት ከተፈለገ በዚያ ቦታ ላይ ጥያቄ መነሳት ስለሌለበት እንደሆነ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ‹‹ብዙ ባለሀብቶች ይህንን ቦታ ለማልማት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም፣ ንግድ ምክር ቤቱ ሲያስተዳድረው ስለነበር ቅድሚያ ለእነሱ ሰጥተናል፤›› ያሉት አቶ ቢኒያም፣ ለንግድ ምክር ቤቱም በደብዳቤም ይህንኑ ያሳወቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ እስካሁን በተመጣበት መንገድ ግን መቀጠል እንደማይችል አመልክተዋል፡፡ 

ወደ ልማት ሲገባ ደግሞ የነበረው ውል መቋረጥ ይኖርበታልና ውሉን አቋርጦ የንግድ ምክር ቤቱን ውሳኔ እንጠብቅ ተብሎ በመጠበቅ ላይ እንደሆነም ከቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ወደ እዚህ ውሳኔ ከተገባባቸው ምክንያቶች አንዱ ንግድና ምክር ቤቱ ለእነዚህን ያህል ዓመት ማዕከሉን ሲያስተዳደር ምንም እሴት ካለመጨመር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለመገንዘብ የተቻለ ሲሆን፣ በዚህ ማዕከል አንድም ተጨማሪ ግንባታ ሳይካሄበት መቆየቱን አግባብ እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡   

‹‹በደርግ ጊዜ የተሠራን አዳራሽ እያከራዩ ገንዘብ መክፈል ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ቢኒያም፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ከተማውን የማይመጥ በመሆኑ የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ኅብረተሰቡን አሰባስቦ በጋራ ማልማት የሚችል ከሆነ ዕድሉ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከተማውን ሊመጥን የሚችል ማዕከል በጋራ ለመገንባት የማይችል ከሆነ፣ ሌሎች የግል ባለሀብቶች ተፈልጎ ቦታውን የሚያለሙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በጻፍንላቸው ደብዳቤም ቦታውን ለማልማት ወደ ሥራ ሊገባ በመሆኑ፣ የትርፍ ክፍፍሉ መቆም ስላለበት ይህ እንዲቆም ተደርጓል ተብሏል፡፡ 

በአዋጅ ከተቋቋመ 75 ዓመታት በላይ ንግድ ምክር ቤት የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅትን እንዲያስተዳድር ስምምነት ሲደርስ ስምምነቱ በመንግሥትና በግል ዘርፍ ትብብር ማዕቀፍን የሚያሳይ በምሳሌነት የሚታይ ነው ተብሎ ነበር፡፡ 

ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ አባላትም ይህንኑ ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አሁን የተወሰደው ውሳኔ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል የተደረሰው በጋራ የመሥራት ልምምድ ይጎዳዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አቶ ቢኒያም ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ አሁንም በጋራ እናልማ ነው ያልነው፡፡ ቅድሚያ ዕድሉንም የሰጠው በጋራ የማልማት ፍላጎት ስላለን እንጂ፣ አስተዳደሩ ውል ሰጪ እንደመሆኑ በፈለገው ጊዜ ውሉን ሊያቋርጥ እየቻለ ድጋሚ በጋራ እናልማ የሚለውን ሐሳብ ያቀረብነው ትብብሩን ለማጠናከር ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከአስተዳደሩ የቀረበለትን በጋራ እናልማ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጠበት አስተዳዳሩ በቀጥታ ልማቱን ለሚያካሂዱ ባለሀብቶች ወደ ማስተላለፍ እንደሚገባ ታውቋል፡፡ አቶ ቢኒያምም ይህንኑ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለመጨረሻው የአስተዳደሩ ውሳኔ የንግድ ምክር ቤቱን ምላሽ ብቻ እየጠበቁ ነው፡፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ከአስተዳደሩ የተሰጠውን ውሳኔ መጀመርያ ላይ ተቃውሞ አቅርቦ እንደነበር ታውቋል፡፡ ሆኖም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ቦርድ ጋር በመገናኘት ባደረጉት ውይይት የአስተዳደሩን ሐሳብ ምላሽ የሚሰጡበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አምባሳደር ብሎ ከሾማቸው የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት ጋር በጉዳዩ ላይ እንደመከረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ነገር ግን የደረሰበትን ድምዳሜ ማወቅ ባይችልም በተሰጠው የጊዜ ገደብ አቋሙን ያሳውቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖችን ግን አስተዳደሩ በሚያስበው ልክ ማዕከሉን በጋራ ለመገንባት ንግድ ምክር ቤቱ አቅም ይኖረዋል ብለው አያምኑም፡፡ በዚህም በዋናነት የሚያቀርቡት ምክንያት ከሰባት ዓመታት በፊት ንግድ ምክር ቤቱ ለዋና መሥሪያ ቤት መገንቢያ የተሰጠውን ቦታ በፋይናንስ እጥረት ሊነባበት ባለመቻሉ፣ አሁንም ለዚህ ግንባታ የሚሆን ፋይናንስ በአጭር ጊዜ ያሰባስባል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ንግድ ምክር ቤቱ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ለመንባትም ሆነ ላለመገንባት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ ይችላልም ይላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ንግድ ምክር ቤቱ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እንዲሰጠን ፕሬዚዳንቷንና ዋናው ጸሐፊውን ለማነጋገር ያደረግናቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች አልተሳኩም፡፡   

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አመሠራረትና ታሪካዊ ዳራውን በሚመለከት ንግድ ምክር ቤቱ በቅርቡ 75ኛ ዓመቱን ሲዘክር ባዘጋጀው መጽሔት ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ ማዕከሉ በ1975 ዓ.ም. ለጎልድ ሜርኩሪ ክብረ በዓል ማክበሪያነት በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ነገር ግን በደርግ ሥርዓት ለልዩ ልዩ አገልግሎትና የአብዮት በዓላትን ለማክበር ከማገልገሉም በፊት በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ሥር የተለያዩ ንግድ ነክ ትርዒቶች ይካሄዱበት እንደነበር የተጻፉ ሰነዶች የሚያመለክቱ መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ማዕከሉ ባለቤት ጋር ተያይዞም አሁንም ብዥታ ያለ ቢሆንም፣ ንግድ ምክር ቤቱ ቀደምት ባለቤትነቱ የምክር ቤቱ እንደነበር እስካለንበት ዘመን ድረስ የማዕከሉ የመብራትና ውኃ ደረሰኞች የሚቆረጡት በምክር ቤቱ ስም መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በደርግ ዘመን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ይተዳደር የነበረውና ንግድ ምክር ቤቱ እንደ ማንኛውም አካል ተከራይቶ የንግድ ትርዒቶችን ያካሄድበት የነበረው ማዕከሉ በሚያዝያ 1986 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ተመልሶ ነበር፡፡ ይሁንና ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ማዕከሉን ለአገልግሎት ምቹ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ፣ በሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እንዲያስረክብ በመታዘዙ አስተዳደሩ ተመልሶ በመንግሥት ስለመያዙ ይኼው የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከባለቤትነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ታኅሳሰ 22 ቀን 1984 ዓ.ም. ለምክር ቤቴ ተመልሶ እንደነበር ንግድ ምክር ቤቱ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ብዙም ሳቆይ እንደገና በመንግሥት ተወስዶ በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር ሲተዳደር ቢቆይም፣ አዋጭነቱ ተጠንቶ የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ለማቀላጠፍና ውጤታማ ለማድረግ የንብረት ባለቤትነቱ ሳይለወጥ ሙሉ ኃላፊነቱና ሥራ አመራሩ ለአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኪራይ እንዲተላለፍ የሚያስችል ስምምነት ደግሞ መስከረም 24 ቀን 1998 ዓ.ም. ተፈርሞ በዚሁ አግባብ ሲሠራ ነበር ተብሏል፡፡.

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች