(በአቤ ጉበኛ)
‹‹ስሚኝ እናት ዓለም!››
‹‹እሺ ምንድን ነው የኔ ዓለም?››
‹‹ያቺ ነገር ምንድን ናት?››
‹‹የት አለች? የት ነው ያየኻት?››
ሕፃኑም ዘረጋና እጆቹን ወደ ሰማይ!
ጨረቃዋን አሳያት ስታበራ ባናታቸው ላይ!
‹‹እሷማ ጨረቃ ናት!››
ብላ መለሰች እናት፡፡
‹‹ጨረቃ ማለት ምንድነው?››
‹‹ይኸ ልጅ ምንድነው የሚለው?››
‹‹እናት ዓለም ጨረቃን አንቺም አታውቂያት?››
‹‹እንግዲህ አታስቸግረኝ ጨረቃ ጨረቃ ናት፡፡››
‹‹ጨረቃስ እሺ ትሁን ታዲያ ተዚያ ላይ ማን ሰቀላት?
‹‹እግዚሐር ነው የፈጠራት፡፡››
‹‹እግዚአብሔር ማለት ምንድነው?››
‹‹ይህ ልጅ ምንድነው የሚለው?
እግዚሐር ማለት ሠሪ ነው አንተን እኔን የሠራ!
ጨረቃንም የፈጠራት በሌሊት እንድታበራ!››
‹‹እኔን የሠራ እግዚሐር ነው?››
‹‹አዎን የሠራህ እግዚሐር ነው!››
‹‹ታዲያ አንቺ ምንድኔ ነሽ እናት ዓለም!››
‹‹እኔማ የወለድሁህ እናት ነኝ የኔ ዓለም!››
‹‹እንዴት አድርገሽ ወለድሽኝ?››
‹‹ውልድ! አድርጌ ነዋ በቃ እንግዲህ አታድርቀኝ››
‹‹ምንድነው እናት ዓለሜ ስጠይቅሽ ምትቆጭኝ››
‹‹እሽ የኔ ዓለም ጠይቀኝ››
‹‹እንዴት አድርገሽ ነው የወለድሽኝ?››
‹‹አንተ ልጅ ዝም በል ብያለሁ!››
እራስህ አድገህ ድረስበት፤
አሁን እኔ ሥራ ልሥራበት!››
ብርሃኑ ገበየሁ ‹‹የአማርኛ ሥነግጥም›› (2003)