የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ጋር የነበረውን የውል ስምምነት ማደሱን አስታወቀ፡፡
ለ12 ዓመታት የክለቡ ስፖንሰር ሆኖ የዘለቀው ሐበሻ ቢራ፣ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት የሚያስቆየውን ውል መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. አስሯል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በዓመት 22 ሚሊዮን ብር የሚሰጥ ሲሆን፣ በተጨማሪም ክለቡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሚሆን ከሆነ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ብር ይሰጣል፡፡
በሌላ በኩል በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የዘገየው የተጫዋቾች የመመላለሻ ባስ፣ ቀድሞ ከተቀመጠለት የገንዘብ መጠን ከፍ በማድረግ በ20.3 ሚሊዮን ብር ግዢ ይፈጸማል ተብሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር የክለቡን ገቢ ለማሳደግ፣ እንዲሁም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ለመሥራት የ5.8 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ተበጅቷል፡፡
እግር ኳስ ከአንድ የስፖርት እንቅስቃሴ በዘለለ፣ ብዛት ያላቸው ደጋፊዎችና ተመልካቾች የሚገኙበት አንዱ የመዝናኛ ዘርፍ ነው። ይህንን የመዝናኛ ዘርፍ ከአልኮል ነፃ የሆኑ መጠጦችን ወደ ተጠቃሚዎች ለማድረስና ለማስተዋወቅ አንዱ መንገድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት ሐበሻ ቢራና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የአጋርነት የውል ካሰሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የውል ስምምነታቸውን እያሻሻሉና እያደሱ መዝለቃቸው ተጠቁሟል፡፡
ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ገንዘብ ወጪ ከማድረግ በዘለለ፣ ለማስታወቂያ አገልግሎት የሚውል በዓይነት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተጠቅሷል፡፡