Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወንጀል ሕጉ ያልተካተቱ የወንጀል ዓይነቶች ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ማነቆ እንዳይሆኑ ሥጋት...

በወንጀል ሕጉ ያልተካተቱ የወንጀል ዓይነቶች ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ማነቆ እንዳይሆኑ ሥጋት እንዳለ ተነገረ

ቀን:

በሥራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋቶች በሚፈቅዱት መሠረት በከፍተኛ ወንጀል ድርጊት ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጥፋቶች በግልጽ አለማካተቱና አለማብራራቱ፣  ወደ ሥራ ሊገባ በዝግጅት ላይ ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖለሲ አፈጻጸም ላይ መሰናክል እንዳይፈጥር ሥጋት መኖሩ ተገለጸ፡፡

በኢትጵያ በሥራ ላይ የሚገኘውን የወንጀል ሕግ በማዘጋጀትና በማሻሻል ሒደት ወቅት፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ ያለው ዕውቀት ውስን በመሆኑም የተነሳም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የሚገለጹ የወንጀል ድርጊቶች ተገቢውን ትኩረት አለማግኘታቸውና አለመካተታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ከፍል መምህር ዮናስ ቢርመታ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የሕግ መምህሩ ይህን የተናገሩት ‹‹የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች›› የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት፣ ‹‹የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ድርጊት የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ያለው የሕግና የተቋማት ቁመና›› በሚል ርዕስ የጥናት ሰነድ ይፋ ባደረገበት ወቅት ነበር፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት ዮናስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚከለክልና በግልጽ የሚዳኝ ሕግ ባለመኖሩ፣ በወንጀል ሕጉ ላይ ጉልህ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በማያሻማ መንገድ በግልጽ በወንጀልነት መፈረጅ የነበረባቸው ወንጀሎች በበቂ አለመዳሰስና ለአብነትም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በወንጀል ሕጉ ላይ ተደንግገው ባለመቅረባቸው፣ አሁን ክስ እየተመሠረተ ያለው በተዛማጅ አንቀጾች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ወደ ትግበራ በሚገባው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኖረው የክስ ሒደት፣ በጦርነትና በግጭቶች ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተጠያቂ ለማድረግ መሰናክል ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ከወዲሁ መቅረፍ  እንደሚያስፈልግ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በሕጉ ካልተብራሩት ወንጀሎች መካከል በዓለም አቀፍ ሕጎች አማካይነት ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚባሉት በተለይም ሥቃይ (Torture)፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት (Crime Against Humanis) የዘር ማጥፋት (Genocide) እና የመሳሰሉትን በግልጽ አለመቀመጣቸውና የሚዳኛቸው የወንጀል ሕግ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በወንጀል ሕጉ ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ያስረዱት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱትን ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በግልጽ የሚከለክሉ የሚዳኙ አንቀጾች መኖር ነበሩባቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በችሎት ወቅት ግርታን በሚፈጥር ሁኔታ የሚታዩ መሆናቸውን፣ አንዳንዶቹ የሚቀርቡ ክሶች የሚታዩት ደግሞ በተጓዳኝ ሕጎች ለአብነትም ‹‹ሕገ መንግሥቱን በመናድ›› በሚሉ አንቀጾች እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን የሚጠቅስ አንቀጽ ቢኖርም፣ ሕገ መንግሥትን ብቻ በመጥቀስ ክስ መመሥረት እንደማይቻል አክለው ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም በወንጀል ሕጉ ያልተጠቀሱ ሕጎች ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት በማድረግ መደንገግ አለባቸው ብለዋል፡፡

በወንጀል ሕጉ መሠረት መከልከል የነበረባቸው ከፍተኛ ወንጀሎች በግልጽ አለመከልከላቸው በሚገባ ተለይቶ ወደፊት በሚሻሻለው የወንጀል ሕግ፣ ወይም የዓለም አቀፍ ሕጎችን በሚመለከቱ ሌሎች አዋጆች መሠረት ውለው ሳያድሩ ምላሽ ማግኘት የሚገባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ በዚህ ሕግ ክፍተት ምክንያት ከባድ ወንጀሎች ያላግባብ በይቅርታ እንዳይታለፉ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም  ዓለም አቀፍ መመዘኛና መለኪያዎችን የተከተሉ የተሟሉ የወንጀል ድንጋጌዎች አለመኖራቸው፣ በሽግግር ፍትሕ ሒደቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሏል፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት ሊቀርፍ የሚያስችልና ሊሟሉ የሚገባቸውን የሕግ ማዕቀፎች ከወዲሁ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ሒደት ውስጥ የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳካትና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍትሕ የማቅረቡ ሥራ ሰፊ ውይይትና ፍተሻ እንዲደረግበትም ተጠይቋል፡፡

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (Lawyers for Human Rights) ዳይሬክተር አቶ አምሐ መኮንን፣ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ውስጥ ምንም ዓይነት ዕውቅና ያልተሰጣቸውና ተብራርተው ያልተቀመጡ የወንጀል ድርጊቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

 በተጨማሪም የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በብቃት ለመምራት ዳኝነት እንዲሰጡ የሚያስችሉ የሥነ ሥርዓት ሕጎች ክፍተት፣ የተቋማት ገለልተኝነት፣ በተለይም የወንጀል ምርመራና የፍርድ ቤት ሒደትን የሚከታተሉ ተቋማት በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት የማይገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የፌዴራል ፖሊስ አሁን ባለው አደረጃጀት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሆኑ፣ የዓቃቤ ሕግን ሥራ የሚሠራው የፍትሕ ሚኒስቴር የካቢኔ አባል መሆኑ፣ ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ አንፃር መፈተሽ እንዳለባቸውና ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ለመዳኘት ተቋማቱም ቁመናቸው በዚያው ልክ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በበርካታ ሪፖርቶች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መፈጸማቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገለጹ ይደመጣል፡፡ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ጉዳይ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሥርዓት ውስጥ መቀመጡን ያስረዱት አቶ አምሐ፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችና የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት መዳኘት አለባቸው ብለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ብቃት ባላቸው ተቋማት፣ ባለሙያዎችና በተሟላ ሕግ ዕርምጃ መወሰድ ሳይቻል እንዳይቀር ሥጋታቸውን ገልጸው ሥራው ከተጀመረ በኋላ የልምድ ማነስ፣ የበጀት እጥረት፣ ወይም ደካማ የሕግ ማዕቀፍ እያነሱ ለማምለጥ መሞከር ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን የሚያጣራና ጠንካራ ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት የተከሰቱ የሕግ ጥሰቶችንና ወንጀሎች እስካሁን በሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ምርመራ እንጂ በገለልተኛ የወንጀል ምርመራ በሚያካሂዱ አካላት አልተካሄደም የሚሉት አቶ አምሐ፣ በቀጣይ የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስከትል የሚችል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቀነት እንዲረጋገጥ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የዓለም አቀፍ የዳኝነት አካላትን በጉዳዩ እንዲሳተፉ ወይም በባለቤትነት የራሳቸውን ሚና እንዳይጫወቱ ዝግ ያደረገባቸው በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ተቋማትን በማጠናከር፣ ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግና ሊያሠሩ የሚችሉ ሕጎችን በማውጣት ሥራው በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንዲከናወን መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...