- በትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች የተከናወነው መርዶ የማርዳት ሥነ ሥርዓት ተነቀፈ
በዳንኤል ንጉሴ
በአገር መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጆችን በይቅርታና በምሕረት እንዲለቀቁ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት፣ የፌዴራል መንግሥት የምርኮኞችን ጉዳይ በማንሳቱ ምክንያት መጓተቱን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው ይህንን የተናገሩት የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ከፓርቲያቸው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር በመሆን፣ መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
‹‹በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ባደረግናቸው ግንኙነቶች በርከት ያሉ ክሶች ተዘግተዋል፡፡ በርከት ያሉ በማንነታቸው ምክንያት ታስረው የቆዩ የትግራይ ተወላጆች የተቻለንን ሠርተን አስፈትተናል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ከፌዴራል መንግሥት ጋር በተነጋገርነው መሠረት ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች እንዲፈቱ የሚያስችል ሥራ በተጠናከረ መንገድ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሠራዊቱ አባላትን በይቅርታና በምሕረት የሚለቀቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሲነጋገር እንደነበር አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በተደረገው ውይይትም ጥሩ መግባባት ተደርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ በኋላ ላይ ግን የፌዴራል መንግሥት ‹‹በእጃችን ከሚገኙ ምርኮኞች ጋር የተያያዘ ሐሳብ በማንሳቱ ሒደቱ ተንቀራፏል፤›› ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ከሚገኙ ምርኮኞች ጋር በተያያዘ አነሳ ያሉት ሐሰብ ምን እንደሆነ ግን አቶ ጌታቸው አልተናገሩም። ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ማድረግ ያለበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ጌታቸው አያይዘውም በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች አሁንም በአማራ ክልልና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል። ‹‹በአማራ ክልል ታስረው የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ያሉበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነው፤›› ብለዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም፣ ‹‹በርከት ያሉ እስረኞች ቁጥራቸውና ስም ዝርዝራቸው ሳይቀር በእጃችን አለ። እነዚህን ለማስፈታት ቀጣይነት ያለው ሥራ ያስፈልገናል፤›› ሲሉ አክለዋል።
የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በበኩላቸው ሕወሓት ራሱን በመፈተሽ ሁሉንም ውስጣዊ አሠራሮቹን በተለይም ስትራቴጂዎቹ፣ ፕሮግራሞቹና ሕገ ደንቦቹ አሁን ላለው ፖለቲካ በሚመጥን መንገድ እንዲስተካከሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
‹‹ሕወሓት ሕዝባዊነቱ ብቻ ነው ሊቀይረው የማይችለው›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ከዚህ ውጪ ሁሉም ዓይነት የውስጥ አሠራር መፈተሽ አለበት፣ የማይፈተሽና የማይታይ ነገር አይኖርም፤›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላምና ፀጥታን እንዲሁም ሙስናና ተጠያቂነትን የማስፈን ችግር መኖሩን ጠቅሰው ተጠያቂነት ሙሉ ለሙሉ መረጋገጥ አለበት ሲሉ አስረድተዋል።
ሕወሓት በሙስና የተሳተፉ የፓርቲው አባላት ላይ የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ እንዲሁም ወንጀለኞችን በመያዝ ደረጃ ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንደሚያግዝ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የበለጠ እንዲጠናከርም ሕወሓት የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እንደሚሠራ ሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ተጠያቂነትን ለማስፈን ከታች ካሉት ባለሥልጣናት ሳይሆን ከላይ ካሉት ባለሥልጣናት እንደሚጀመር ሊቀመንበሩ ጠቅሰው፣ ሆኖም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ብቻ ተብሎ የጅምላ እስር ውስጥ እንደማይገባ ይልቁንም በማስረጃና ፍፁም ግልጽ በሆነ መንገድ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን በፖለቲካዊ መንግድ ለማስመለስ እንደሚሠራ፣ በዚህም ምክንያት ይህ አጀንዳ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲያዝ መደረጉን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
ሕወሓት በቅርቡ ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በፓርቲው ውስጥ የአመራር ችግር መኖሩን በጥልቀት በመገምገም በፍጥነት ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰኑንም ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ የትግራይ ተወላጆች ሰማዕትነታቸውን የሚመጥን ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ የተናገሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ሰሞኑን በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች ሥነ ሥርዓትን ባልጠበቀ መንገድ የተከናወነ መርዶ የማርዳት ተግባር ተከናውኗል፡፡ የሰማዕታትን ክብር የማይመጥን ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ማኅበራዊ ቀውስን ያስከተለ ጭምር በመሆኑ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል።
አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ እሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ካለፈው ግንቦት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በጦርነቱ የተሰው ሰማዕታትን ማንነት የማጣራት ሥራ በተሟላ ደረጃ ሲያከናውን ቆይቷል። በርከት ያሉ ሰማዕታት መኖራቸውን ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ፣ ስማቸው የተዋጉበትና የተሰውበትን ቦታ አጣርቶ ለማወቅ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ አስረድተዋል።
‹‹ይህ ከተከናወነ በኋላ ለሰማዕታት የሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ክብራቸውን በሚመጥን ብቻ ሳይሆን፣ አቅም ባይኖረንም የሰማዕታት ቤተሰቦች ካሳ ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ሳይመቻች መከናወን ስለሌለበት፣ ለዚህ የሚሆን አቅም ለማግኘት ትልቅ ፈተና ሆኖብን ነበር፤›› ብለዋል።
‹‹ሥነ ሥርዓቱን ባልጠበቀ መንገድ መርዶ ማርዳት ለሰማዕታቶቻችን አይመጥንም። ሰማዕቶቻችን በከፈሉት ዋጋ አንፃራዊ ሰላም እንድናገኝ ስላደረጉን የምንኮራበት በመሆኑ፣ ይኼን ከግምት አስገብተን ለክብራቸው በሚመጥን መንገድ ልናደርገው ይገባል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ በትግራይ ክልል ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሐዘን ቀን እንደሚታወጅና ሥርዓት ያለው ማርዳት እንደሚከናወን ገልጸዋል።