Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መሥራች የቦርድ አባላቱን መረጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አምስት መንግሥታዊ ድርጅቶች 25 በመቶ ድርሻ በማዋጣት የአክሲዮን ማኅበሩን አቋቁመዋል

እየተቋቋመ ያለው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር) እና አቶ ዘመዴነህ ንጋቱን ያካተተ፣ መሥራችና የመጀመሪያ ሰባት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን መረጠ፡፡

በሰብሳቢነት የተመረጡት የቀድሞ የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሴፈስ ካፒታል አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ አመራር የነበሩት፣ በአሁኑ ጊዜም በብሔራዊ ባንክ አማሪከ የሆኑት አቶ ህላዌ ታደሰ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራች የነበሩት እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚና ቢዝነስ አማካሪው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ያዝሚን ወሀብረቢ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪዋ ወ/ሪት ሂንጃት ሻሚል፣ የኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) እና የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ የቦርድ አባላት በመሆን ተመርጠዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መሥራች የቦርድ አባላቱን መረጠ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ ከሚገኙ አራት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን በአምስት መሥራች አባላትነት የሰነዶች ሙዓለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበርን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን 25 በመቶ በማጣዋት አክሲዮን ማኅበሩን መሥርቷል፡፡

ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ካፒታል እንደሚያስፈልገው የተገመተው አክሲዮን ማኅበሩ፣ በአምስቱ ድርጅቶች ከተዋጣው 25 በመቶ ድርሻ ከፍተኛውን መጠን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንደሚሸፍነው ተገልጿል፡፡

አራቱ የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ናቸው፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩን መቋቋሚያ መመሥረቻ ስምምነት ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የሚቀረውን የ75 በመቶ ድርሻ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ የግል ድርጀቶች ለመሸጥ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በቀጣይ ሦስት ወራትም አጠናቆ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

የተሾሙት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አዳዲስ የሚገቡት ባለአክሲዮኖች ምዝገባ ከተጠናቀቀና ጠቅላላ ጉባዔ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ ለዕጩነት እንደሚቀርቡ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ከፍተኛ አመራር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢንቨስተሮች ቦርድ ማየት ስለሚፈልጉ አሁን ቦርድ ተሹሟል፡፡ በቀጣዩቹ ሦስት ወራት የኢንቨስተሮችን ምዝገባና ቀሪዎቹን ባለአክሲዮኖች ምዝገባ እናጠናቅቃለን፤›› ሲሉ ጥላሁን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

አሁን ያሉት የቦርድ አባላት ማኅበሩን ለማቋቋም ታስቦ በመንግሥት የተመረጡ መሆናቸውን፣ ወደፊት የቦርድ አባላት አሿሿም በአክሲዮን ድርሻ መጠን እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ ቦርዱና ባለአክሲዮኖቹም በጋራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደሚሾሙ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች