Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፀጥታ ኃይሎች በተፈናቃዮች ላይ ያደረሱት ጉዳት እንዲመረመርና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጠየቀ

የፀጥታ ኃይሎች በተፈናቃዮች ላይ ያደረሱት ጉዳት እንዲመረመርና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጠየቀ

ቀን:

  • የመንግሥት የፀጥታ አካላት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከመጣስ እንዲቆጠቡ ጠይቋል

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይኖሩበታል በሚባልለት የባቢሌ አካባቢ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት የደረሰው ጉዳት አፋጣኝ ምርመራ ተካሂዶበት፣ ለተጎጂዎች ካሳ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥያቄ አቀረበ፡፡

ኢሰመኮ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ፣ በሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ፣ በአካባቢው የተጠለሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የአካባቢው ነዋሪዎች መጎዳታቸው አሳስቦኛል ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ የጅግጅጋ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰዒድ ደመቀ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምንም እንኳ የተረጋገጠ ቁጥር ባይሆንም በአካባቢው እስከ 200 ሺሕ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይኖራሉ፡፡ ቆሎጂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተኩስ ልውውጡ ወቅት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ካሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም በበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ የተኩስ ልውውጡ መነሻ በግልጽ ባይታወቅም፣ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ተፈናቃዮች፣ እንዲሁም ከተጎጂዎች ሰማነው እንዳሉት ግጭቱ ከኬላ አጠቃቀም ጋር በተገናኘ ምክንያት ስለመሆኑ ሰዒድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በመግለጫው በካምፓላ ስምምነት መሠረት የመንግሥት የፀጥታ አካላት፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደኅንነት፣ አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግጭቱ የቆመ ቢሆንም ሁለቱ ክልሎች በቅንጅት በመሥራት በአካባቢው ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሰላማዊ መፍትሔ በመስጠት፣ የነዋሪዎችንና የተፈናቃዮችን ደኅንነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ሥራ እንዲያከናውኑ ኮሚሽኑ አክሎ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም ለደረሰው ጉዳት ተጎጂዎች እንዲካሱና ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ባለማድረግ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ የፀጥታ ኃይሎች አባላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ‹‹በተለይም ቀድሞውኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አስቸጋሪ ሕይወት ይመሩ የነበሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በኮሚሽኑ መግለጫ ማስታወቃቸው ተገልጿዋል፡፡

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም፣ ‹‹በአፍሪካ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ዕገዛን አስመልክቶ የተደረገው የአፍሪካ ኅብረት ስምምነት (ካምፓላ ስምምነት) መሠረት፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባል፤›› ማለታቸውም ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...