ኢትዮጵያ እስካሁን ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች ያገኘችው የአየር ንብረት የፋይናንስ ድጋፍ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ፋሲሊቲ (Global Environment Facility) እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ጋር ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ሲሆን፣ እስካሁን ከተገኘው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፉን ማሳደግ እንደሚጠባቅበትም ተነግሯል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮች እስካሁን ድረስ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር በአየር ንብረት ፋይናንስ አማካይነት አግኝታለች፡፡ ‹‹ይህንንም አሳድጎና አስፋፍቶ መሄድ የሚቻልበትን አቅም መፍጠር ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ከሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነገ ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአራት ቀናት በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ሳንዶካን፣ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የአንድ አገር ሥራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አገሮች በተቀናጀ መንገድ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
‹‹የአደጉ አገሮች (በካይ አገሮች) የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ሁሉ፣ አዳጊ አገሮችም በራሳቸው ፕሮግራምና ዕቅድ ራሳቸው ሊሠሯቸው የሚገቡ ሥራዎች አሉ፤›› ሲሉ፣ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እንደ ምሳሌ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የ17 የአፍሪካ አገሮችና የየመን ተወካዮች የተገኙበት ዓውደ ጥናቱ፣ ዓላማውም ግንዛቤ መፍጠርና የተሻሻሉ ክህሎቶችን በማሳደግ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ፋሲሊቲ (GEF) አማካይነት በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያሳድጉ ነው፡፡
‹‹በተደራጀና በተጠና ሁኔታ የአየር ንብረት ፋይናንስን መጠቀም መቻል አለብን፤›› ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ በእንዲህ ዓይነት ዓውደ ጥናቶች እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ታዳጊ አገሮች ትልልቅ የፋይናንስ አቅሞች የሚጠበቁበትን መንገድ ያስችላሉ ብለዋል፡፡