Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን እንደገና ሥራ እንዲጀምር ከኦሮሚያ ክልል ጋር ንግግር እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን እንደገና ሥራ እንዲጀምር ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ አስታወቀ፡፡

ከመንግሥት ኩባንያዎችና ልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነውን ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን፣ በድጋሚ ሥራ እንዲጀምር ማምረቻው ከሚገኝበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን፣ የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ማምረቻ ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ በመቆየቱ ምንም ዓይነት ሥራ አለማከናወኑን አቶ አብዱራህማን ገልጸዋል፡፡

‹‹በፀጥታ ችግርና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ማምረቻው ተዘግቶ ኪሳራ አጋጥሟል፡፡ ከገጠሙ ችግሮች ማገገም እንዲችል የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ከክልሉ መንግሥት ጋር ውይይት እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኘውን የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ዕምቅ ሀብት እንዲያለማ በ2007 ዓ.ም. በ15 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ ከገጠመው ችግር በማገገም ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስፈልገውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሆኑ ተቋማት ጋር ትብብር እንዲፈጥር ማስቻልና የባንክ ብድር እንዲያገኝ ለማድረግ ግሩፑ ዝግጁ መሆኑን አቶ አብዱራህማን ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሆልዲንግና አስተዳደር ሥር የነበረ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ ማዕድን ሚኒስቴር፣ በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ሥር ከተጠቃለሉት 26 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት እንዲያለማ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ፣ በማዕድን ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሥራዎችን ማከናወን የሚችል ተቋም ነው ሲሉ አቶ አብዱራህማን  ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን አዶላ ወርቅ፣ የቀንጢቻ ታንታለምን ጨምሮ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ኮርፖሬሽኑ በሥሩ አድርጎ ይሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም. በጉጂ ዞን የሚገኘው የቀንጢቻ ታንታለም ምርት ፈቃዱ ተሰርዞ ለኦሮሚያ ማዕድን ሼር ካምፓኒ መሰጠቱ አይዘነጋም፡፡

ነዳጅን ጨምሮ በተለያዩ የማዕድን ዘርፎች እንዲሠራ በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቅ የነበረው ኮርፖሬሽን፣ በፋይናንስ እጥረትና አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የተለያዩ የማዕድን ፕሮጀክቶቹ ተወስደው ለሌላ አካላት መሰጠታቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲዘገብ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ በሚኒስትሮች  ምክር  ቤት  ማቋቋሚያ ደንብ ከፀደቀ በኋላ፣ ታኅሳስ 20 ቀን  2014 ዓ.ም. የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመፍጠር መመሥረቱ ይታወቃል፡፡

ለኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ራሔል ጌታቸው በመደወል ኮርፖሬሽኑ ሥራውን ያላከናወነባቸውን ምክንያቶች ለማወቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች