Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕፃናትን ከካንሰር ለመታደግ በለስ የቀናው ‹‹ማቲዎስ››

ሕፃናትን ከካንሰር ለመታደግ በለስ የቀናው ‹‹ማቲዎስ››

ቀን:

ማቲዎስ ወንዱ ገና በጨቅላ ዕድሜው ሉክሚያ በተባለ የደም ካንሰር በሽታ ተጠቂ ሆነ፡፡ በበሽታው የተያዘው ልጃቸውን ለማሳከም ወላጆቹ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው፣ ሕክምናው ይገኛል በተባሉባቸው የአገር ውስጥም ሆነ የባህር ማዶ የሕክምና ተቋሞች ቢሄዱም የልጃቸው ሕይወት ሊተርፍ አልቻለም፡፡ ወላጆቹ ትንሹ ልጃቸውን በሕይወት ለማዳን ብዙ ጥረት ቢያደርጉም መስከረም 13 ቀን 1996 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷቸዋል፡፡

ሕፃናትን ከካንሰር ለመታደግ በለስ የቀናው ‹‹ማቲዎስ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ጀማል ተማም

በደም ካንሰር ሕመም ልጃቸውን ገና በለጋ ዕድሜው በሞት የተነጠቁት ወ/ሮ አምሳለ በየነና አቶ ወንዱ በቀለ እሱን የሚዘክርና በሕመሙ እየተሰቃዩ ያሉትን ወገኖች ለመደገፍ ያለመ አንድ ውጥን ይዘው ብቅ አሉ፡፡ የማቲዎስ ቤተሰቦች ሐዘኑን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር በተመሳሳይ ሁኔታ በካንሰር ሕመም የተጠቁ ልጆች ያላቸው ቤተሰቦችን ለመርዳትና ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መርዳት ሳይችሉ ሲቀሩ ከሚገቡበት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለመታደግ የሚሠራ ድርጅት ለማቋቋም ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ እነሆ ያለሙት ውጥናቸው ሰምሮ ሚያዝያ 9 ቀን 1996 ዓ.ም. ‹‹ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ›› ለመመሥረት ችለዋል፡፡

ድርጅቱም መጀመርያ ትኩረቱን የሕፃናት ካንሰር ላይ በማድረግ ተልዕኮውን የጀመረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የካንሰር ቁጥጥርና ዕርዳታ ለሚሹ የካንሰር ሕሙማን ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ጀማል ተማም ይገኙበታል፡፡ አቶ ጀማል ኑሮዋቸውን በጉንችሬ ያደረጉ ሲሆን፣ በደም ካንሰር በሽታ ተይዞ የነበረውን ልጃቸውን ለማሳከም እላይ እታች ብለው ተስፋ መቁረጥ ላይ ሲደርሱ በአንድ አጋጣሚ በተቋሙ በኩል ድጋፍ ማግኘት መቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡

በካንሰር በሽታ የተያዘውን ልጃቸውን ለማሳከም ከብቶቻቸውን ሳይቀር መሸጣቸውን ያስታወሱት አቶ ጀማል፣ ልጃቸው በአሥር ዓመቱ ለዚህ በሽታ እንደተጋለጠ ይናገራሉ፡፡ በበሽታውም ከተያዘ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሕክምና ተቋሞች በመሄድ ሕክምናውን ሲከታተል እንደነበር በመጨረሻ ግን በሽታው ሥር የሰደደ በመሆኑ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ይጻፍለታል፡፡

ሕፃናትን ከካንሰር ለመታደግ በለስ የቀናው ‹‹ማቲዎስ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራቾች

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ከተጻፈለት በኋላ ሕክምናውን ለማግኘት ከፍተኛ የሆነ ወጪ ማውጣታቸውን የተናገሩት እኝህ አባት ከረዥም ጉዞ በኋላ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ድጋፍ ማግኘቱን ይገልጻሉ፡፡

በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲም የትራንስፖርት፣ የሕክምና፣ የአልጋና የምግብ ወጪ እየተሸፈነላቸው ልጃቸው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

የሕክምና አገለግሎቱን ካገኘ በኋላ እዚያው ተቋሙ ውስጥ አልጋ ተሰጥቷቸው እንዲቆዩ መደረጉን የተናገሩት እኝህ አባት፣ ልጃቸው በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ነፃ ሊሆን መቻሉን ያስረዳሉ፡፡

ልጃቸው በአሁኑ ወቅት 17 ዓመት እንደሆነው ከበሽታውም አገግሞ ትምህርቱን እየተከታተለ መሆኑን ጠቅሰው፣ የካንሰር በሽታን በአግባቡ መከታተል ከተቻለና ተገቢውን የሆነ የሕክምና አገልግሎት ከተገኘ በፍጥነት መዳን ይቻላል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የአሥር ወር ልጇ የፕላስቶማ የካንሰር በሽታ ተጋላጭ የሆነባት ወ/ሮ ዘይና አብዱ እንደገለጸችው፣ አንድ ልጇን ለማሳከም አቅም ስታጣ በሰዎች ትብብር ወደ ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መምጣት ችላለች፡፡

በመጀመርያ ቀን የአሥር ወር ልጇ በዚህ በሽታ ሲያዝ እንደ ቀላል ነገር ማየቷን የምትናገረው ይህቺ እናት፣ አንድ ልጇን ለማሳከም በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፏን ትናገራለች፡፡

በደሴ ከተማ ቤት ተከራይታ ትኖር እንደነበር፣ ልጇንም የዚህ በሽታ ሰለባ መሆኑ ሲታወቅ ቀጥታ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር እንደተጻፈላት ታስረዳለች፡፡

በወቅቱ ሁሉም ነገር ዞሮባት ‹‹መሬት ቢውጠኝ ደስ ይለኝ ነበር›› ማለቷን የምታስታውሰው ይህቺ እናት፣ ከአሥራ አምስት ቀናት በኋላ ከምኒልክ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዳ ሕክምናን ልጇ እንድታገኝ ሪፈር እንደተጻፈላት ትናገራለች፡፡

የአንድ ልጇን ነፍስ ለመታደግ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፏን ገልጻ የሕክምና፣ የአልጋና የምግብ የምትሸፍንበት ወጪ በወቅቱ ምሬት ውስጥ ከቷት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ልጇም የሕክምና አገልግሎቱን እንዲያገኝ በአሥራ አምስት ቀን አንዴ ቀጠሮ እንደሚሰጣት የምትናገረው ይህቺ እናት በአሁኑ ወቅት አንድ ልጇ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ድጋፍ በማግኘቱ ልጇ ከዚህ በሽታ ሊድን መቻሉን ትገልጻለች፡፡

ከዚህ በፊት ልጇ ምግብ እንደማይበላና ተቀያያሪ የሆነ ፀባይ ያሳይ እንደነበር ገልጻ፣ አሁን ላይ ተቋሙ የሕክምና፣ የትራንስፖርት፣ የምግብና ሌሎች መሰል ወጪዎችን እየሸፈነላት መሆኑን ታስረዳለች፡፡

በተለይ አንድ ልጇን ለማሳከም ቀርቶ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ከብዷት እንደነበር የምታስታውሰው ወ/ሮ ዘይና፣ ባለቤቷ ገና የስምንት ወር ነፍሰ ጡር እያለች ትቷት እንደሄደ ገልጻለች፡፡

በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ውስጥ በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን የሕክምና ወጪ እየተሸፈነላቸው መሆኑን ጠቅሳ መንግሥት ለካንሰር በሽታ ትኩረት በመስጠት የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል ትላለች፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የሃያ ዓመታት ጉዞ

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መጀመርያ ትኩረቱን የሕፃናት ካንሰር ላይ በማድረግ የጀመረ ተቋም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የካንሰር ቁጥጥርና ዕርዳታ ለሚሹ የካንሰር ሕሙማን ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በትንሹ ማቲዎስ ስም የተጀመረው የሶሳይቲው ሥራ በእጅጉ አድጎ ዛሬ ለበርካቶች ሕሙማን መድኅን ለመሆን ችሏል፡፡ ሶሳይቲው በአሁኑ ወቅት 1,400 አባላት 500 በጎ ፈቃደኞች፣ 30 ቋሚ ሠራተኞች ይዞ ትልቅ ድርጅት ለመሆን በቅቷል፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ስምንት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ ሲሆን፣ 152 የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸውን በተለያዩ ነገሮች በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ሶሳይቲው ከዚህ በተጨማሪም የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡ የጤና ተቋማት የማይገኙ የመድኃኒትና የላቦራቶሪ ሕክምና ወጪዎችን ይሸፍናል፡፡ ለሕሙማን ቤተሰቦች ለትራንስፖርት የሚሆን ወጪ በየወሩ ይሰጣል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ለሚማሩ ሕፃናት ታካሚዎች ድርጅቱ ሙሉ የትምህርት ወጪያቸውን የሚሸፍን ሲሆን፣ ከተለያዩ ክልሎች እየመጡ በአዲስ አበባ ሕክምና ለሚከታተሉ ሕሙማን 24 አልጋዎች ባሉት ማቆያ ማዕከሉ የመጠለያና የምግብ አገልግሎት በነፃ ይሰጣል፡፡

ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ፣ በውስን አቅሙ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የካንሰር በሽታ ጫናን ለመቋቋም በሚያደርገው አገራዊ ጥረት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ድርጅቱም የአሜሪካ የሕፃናት አካዴሚ ከሚባል ግብረ ሠናይ ድርጅት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ የጤና ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ ያዘጋጀውን የሕፃናትና አዋቂዎች የካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ ሰነድ በማዘጋጀት እንዲተገበር አድርጓል፡፡

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በማኅበረሰቡ አኗኗር ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀስ ድርጅት ለመሆን መብቃቱ ይነገርለታል፡፡ ሥራው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘንድ ዕውቅናና የተለያዩ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...