በየጎዳናው የወዳደቁ ቆሻሻዎችን ለማፅዳት ከላይ ታች የሚሉ እናቶች ቁጥር አያሌ ነው፡፡ እነዚህም እናቶች ጨለማው ለንጋት ጊዜውን ከመልቀቁ በፊት፣ ወጥተው ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ሲሉ ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
በተለይ የሚያፀዱት ሥፍራ ወዲያው ተመልሶ ከግለሰቦች አላግባብ በሚወረወሩና በሚጣሉ የውኃ ፕላስቲክ፣ ሶፍትና በሌሎች ቆሻሻዎች ሲሞላ አይተው ሲናደዱ ማየቱም የተለመደ ሆኗል፡፡
ከተማዋን ፅዱ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ቢሆንም፣ ሰምቶ እንዳልሰማ የመሆን አባዜ ግን ጎልቶ መታየቱ ይበልጥ ችግሩ አባብሶታል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩንም ለማለፍ ሆነ እናቶች ከዚህ ሥራ በተጨማሪ ሌላ የገቢ ምንጭ ባለቤት እንዲሆኑ እናት ባንክ እየሠራ ይገኛል፡፡
እናት ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ በመንገድ ፅዳት ላይ የተሰማሩ ስድሳ እናቶችን ለሦስት ወራት በማሠልጠን ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን፣ መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
‹‹በእናት ለእናት›› ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ መቅደስ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እናት ባንክ መንገድ ፅዳት ላይ ተሠማርተን የምንገኝ እናቶች ተጨማሪ ገቢ እንዲኖረን ልዩ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 8 አካባቢ በመንገድ ፅዳት ሥራ ተሰማርተው መሥራት ከጀመሩ አሥር ዓመታት ያህል ቢያስቆጥሩም፣ በሚያገኙት ገቢ የዕለት ጉርሳቸውንና የልጆቻቸውን ወጪ ከመሸፈን በዘለለ፣ ሌላ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት እናት ባንክ ለሦስት ወራት ያህል የሰጣቸውን ሥልጠና በመጠቀም፣ ከመንገድ ፅዳት ሥራ በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው ሽንኩርትና ድንች በመነገድና ሌሎች መሰል ሥራዎችን በመሥራት የተሻለ ኑሮ እየኖሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ባንኩም ባደረገላቸው ድጋፍ መሠረት በትርፍ ጊዜያቸው እየሠሩ የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ከዚህ በፊት የነበረባቸውን ችግር መቅረፍ መቻላቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ ሥልጠና ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ውድነሽ ኤደር እንደተናገሩት፣ እናት ባንክ በሰጠን ሥልጠና መሠረት የተሻለ ሕይወት መኖር ችያለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ይኖሩ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ውድነሽ፣ እናት ባንክ የሰጣቸውን ሥልጠና በመጠቀም ከመንገድ ፅዳት ውጪ በትርፍ ጊዜያቸው ቆሎ በመሸጥ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን ካገኙ በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ሕይወት እየኖሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ አንድ ልጇቸውንና ወንድማቸውን በመደገፍና ከሚያገኙትም እየቆጠቡ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ዳር ፅዳት ከተሰማሩ ዘጠኝ ዓመት ያስቆጠሩት እኚህ እናት፣ ከዚህ በፊት በሚያገኙት ገንዘብ የቤት ኪራይና የዕለት ጉርሳቸውን እንደማይሸፍንላቸው አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእናት ባንክ በኩል በተደገላቸው ሥልጠና ተጨማሪ ሥራ በመሥራት የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን፣ አንድ ወንድማቸው የአዕምሮ ሕመምተኛ ስለሆነ የእሳቸውን እጅ ጠብቆ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ዳር ፅዳት የተሰማሩ እናቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በሌሎች ነገሮች ላይ ራሳቸውን እንዲችሉ እየሠራ መሆኑን፣ የእናት ባንክ የኮርፖሬሽን አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሐጎስ ተናግረዋል፡፡
እናት ለእናት የተሰኘው ፕሮጀክትም ለአምስት ሺሕ ወገኖች ተደራሽ ለመሆን ያለመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የ60 እናቶችን ወጪ ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለሦስት ወራት ያህል ሥልጠና ወስደው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡
በመንገድ ፅዳት የተሰማሩ እናቶች በትርፍ ጊዜያቸው ሌላ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ሥልጠና መስጠቱን ገልጸው፣ ባንኩም የሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት በሚያጎለብት አሠራርና የዲጂታል ባንኪንግን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የእናቶችን የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ ባንኩ አነጋ ኢንጂነሪንግና እንደዜጋ ማኅበራዊ እንደራሴ ከተሰኙ ተቋማት ጋር ለመሥራት የመግቢያ ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት አነጋ ኢንጂነሪነግ የተሰኘው ተቋም ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ምድጃና ሌሎች ነገሮችን እየሠራ መሆኑን፣ ይህንንም ተረፈ ምርት እናቶች በቀጥታ ለተቋሙ እንዲያቀርቡ የሚያደርግ ስምምነት ባንኩ መፈራረሙን ምክትል ፕሬዚዳንቷ አስረድተዋል፡፡