Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልባህላዊው የዘመን መባቻ

ባህላዊው የዘመን መባቻ

ቀን:

‹‹የመስቀል በዓል የበዓላት ሁሉ አውራ ሆኖ ከመታየቱ በተጨማሪ በዓሉ እንደ ዘመን መለወጫ የሚቆጠርና ለአዲሱ ዓመት የደስታ የጤንነት እንዲሆን ከመመኘት ጋር የተያያዘ ነው፤›› ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለዩኔስኮ የመስቀልን በዓል በተመለከተ የላከው ሰነድ፡፡

የመስቀል በዓል መስከረም 17 ቀን የሚውል ሲሆን፣ በየብሔረሰቡ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር መሠረት የመስከረም አጋማሽና ብራነቱን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ብሥራት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

ለአብነትም ወላይታዎች ‹‹ጊፋታ››፣ ሀዲያዎች ‹‹ያሆዴ››፣ ካምባታዎች ‹‹መሰላ››፣ ቦሮ ሽናሻዎች ‹‹ጋሪዎሮ››፣ ካፍቾ ‹‹ማሽቃሮ››፣ የም ‹‹ሄቦ››፣ ጋሞ ‹‹ዮ ማስቃላ›› እያሉ የዘመን መባቻዎቻቸውን በበዓለ መስቀሉ ዋዜማ ያከብሩታል፡፡ ችቦ ይለኩሳሉ፣ ለበዓሉ የሚስማማውን ባህላዊ ምግብ ይመገባሉ፡፡

‹‹ጊፋታ››

‹‹ዮዮ ጊፋታ›› የወላይታ ባህል አዋቂዎችና ጥበበኞች የጨረቃን ዑደት ስሌት መሠረት በማድረግ፣ ማኅበረሰቡ ከክረምት ወደ ብራ፣ ከጭጋጋማ ድባብ ወደ ብርሃናማ ዓውድ፣ ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲስ ዓመት የሚደረገውን ሽግግር የሚያበስሩበት ነው፡፡ የአዲስ ዓመት ዕቅዳቸውና ጥረታቸው እንዲሳካ አምላክን የሚማፀኑበት የተስፋና የተምሳሌት በመሆኑ ጊፋታ በየዓመቱ ይከበራል፡፡   

ከወላይታ ዞን አስተዳደር ድረ ገጽ ስለ ጊፋታ ጥንተ ነገር እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

ባህላዊው የዘመን መባቻ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዮዮ ጊፋታ

የጊፋታ በዓል ትርጉም

 ‹‹እንደ ብሔሩ የታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎች ጊፋታ በብሄሩ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቅያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡

 ‹‹ጊፋታ ማለት ባይራ(ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡ ጊፋታ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አእዋፋትና የቤት እንስሳትም ጭምር በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ/ካሌንደር አለው፡፡ በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡ በበዓሉ ‹‹ጊፋታ ጋዜ አቡና ጋይሌ›› ተብሎ ይዘፈናል፡፡ ይህም የበዓሉን ታላቅነት ለመግለጽ ነው፡፡

አቆጣጠሩ

‹‹አሮጌው ዓመት እየተገባደ ሲሄድ በቀደመው ጊዜ በንጉሡ አማካሪዎች አማካይነት የዘመን ቆጠራ ባለሙያዎች ወደ ቤተመንግሥት ይጠራሉ፡፡ ከዚያም ሌሊት ሌሊት እየወጡ የጨረቃን ዑደት መነሻ ለማወቅ የጨረቃን አራት ክፍሎች ማለትም /ፖኡዋ፣ ጡማ፣ ጤሯ፣ ጎባና/ በየትኛው ክፍል እንደሚውል የዓመቱን የቆጠራ ምልክቶች ይዘው መጥተው፣ የሙሉ ጨረቃዋን ዑደት ተመልክተው ያበስራሉ፡፡ ከዚያም ኮከብ ቆጣሪዎቹ በዓሉ የሚከበርበት ቀን በትክክል ለንጉሡ ከነገሩ በኋላ ሽልማት ይዘው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ቀጥሎም ንጉሡ የበዓሉን መቃረብ ለሕዝቡ ‹በጫላ ኦዱዋ› (አዋጇ) በየገበያውና የሕዝብ መሰብሰቢያ እንዲነገር ያደርጋል፡፡ 

የአመጋገብ ሥርዓት

‹‹የጊፋታ ዕለት ከንጋት ጀምሮ ቤት ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡ እናቶች ከተዘጋጀው ዳጣ ለዕለቱ የሚበቃውን ከፍለው ቅቤ በመጨመር በእሳት ያንተከትካሉ፣ ቂጣ፣ ቆጮ ያዘጋጃሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ‹ኤርጊያ› የሚባለውን ያልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ተቆርጦ ሳሎን ላይ በመሬት እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡ አባት ካመጣው ሥጋ መካከል ጥሬ የሚበላውን በማዘጋጀት፣ በቢላዋ እየቆረጠ በኮባው ቅጠል ላይ ዙሪያውን ያስቀምጣል፡፡ ቆጮና ቂጣም በተመሳሳይ ሁኔታ ይደረጋል፣ በመሃል በመሃሉ ዳጣ በርበሬ በወጪት ተደርጎ ይቀመጣል፡፡ ማዕዱ ከቀረበ በኋላ ከዓመት ዓመት በሰላም ያሸጋገረን አምላክ እንደየ አምልኮ ሥርዓታቸው ያመሠግናሉ፡፡ አባት ከሁሉም በፊት ከተዘጋጀው ማዕድ እናትን ያጎርሳል፡፡ በመቀጠል በማዕዱ ዙሪያ የተቀመጡትን ልጆች ሁሉ ያጎርሳቸዋል፡፡ ቀጥሎም የቤተሰቡ አባላት ለየራሳቸው መመገብ ይጀምራሉ፡፡

«ያሆዴ»

የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል ‹‹ያሆዴ›› ይባላል፡፡

አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት ልዩ በዓሉ ነው።

የያሆዴ በዓል ሀዲያ ዘመኑን የሚቆጥርበት ትልቅ በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአዲስ ተስፋ፣ ከልምላሜ፣ ለሀገር ሰላም ፀሎት ከማድረግ፣ ከብርሃን ጋር የሚገናኝ ተደርጎም እንደሚወስድ የሀዲያ ዞን ኮሙዩኒኬሽን በድረ ገጹ ገልጿል፡፡

በክረምቱና ወንዝ ሙላቱ አልፎ ብራ ሲመጣ የሚከበረው የያሆዴ በዓል ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው ያ ሆዴ ጭፈራ ነው። ጭፈራውን ወጣት ወንዶች በአካባቢያቸው ተሰብስበው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ የሚጨፍሩት ባህላዊ ጨዋታ ነው።

በዚህ ዕለት ማታ ፉኒታ (ሆያ ሆየ) የሚጨፈርበትና ጨፋሪዎች ደግሞ ‹‹ከዚህ ቤት ችጋር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ!›› ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ይጨፍራሉ። ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁና ይሸኟቸዋል። በየገቡበት ቤት ሁሉ አተካና እና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችን እየበሉ የቤቱን አባወራንና እማወራ ይመርቃሉ።

እንደ ሀዲያ ዞን እና ኢፕድ አገላለጽ፣ ያሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብና በፍቅር መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት ነው፡፡

‹‹ያሆዴ ያ ሆዴ ያሆዴ …… ያሆዴ ሆ ያሆ

ዱቢንሴ ኢንጃ ጉሎ ……… ዴ ሆ ያሆ

ባሪንሴ ዋሳ ጉሎ ……….. ያሆዴ ሆ ያሆ በማለት ያዜማሉ።

ትርጓሜውም ከጓሮ ቅመም ጨራሽ ከጉድጓድ ቆጮ ጨራሽ እንደማለት ነው።

ለበዓሉ ከሚቀርበው የምግብ ዓይነት በዋናነት የሚጠቀሰው ነው፡፡ አተካና የሚሠራው ከቆጮ፣ ቡላ፣ ከቅቤ፣ አይብ፣ ወተትና ከተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ነው።   

‹‹ሄቦ››

የየም ብሔረሰብ ዘመንን የሚለውጥበት በዓል ሄቦ ይባላል፡፡ ረዥም የዝናብ ወራትን የሚሸፍነው ከሰኔ እስከ መስከረም ሲሆን፣ ከክረምት (መሄር) ቀጥሎ የሚመጣው የመፀው ወቅት ‹‹ማር›ን› ተከትሎ የሚመጣ በዓል ነው ሄቦ።

ሔኖክ ሥዩም ‹‹ቱባ›› በተሰኘው ኅትመቱ እንደገለጸው፣ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት መግቢያ የሚከበረው በዓሉ ከወዳጅ ዘመድ ጋር የሚደረገው መገባበዝና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ልውውጥ ‹‹ፍርኒ ኦቱ›› (የአበባ መለዋወጥ) ይባላል።

ሄቦን ለማክበር ዝግጅቱ የሚጀመርበት መስከረም 14 ቀን ‹‹ካማ ኬሳ›› ይባላል። ‹‹ካማ›› ማር ሲሆን፣ ‹‹ኬሳ›› ደግሞ መውጣት ማለት ነው። ወደ አዲስ ዓመት የሚገባው ቂምና ቅሬታን በማስወገድ ሲሆን ለዚህም በሽማግሌዎች አማካይነት ዕርቀ ሰላም የሚወርድበት ሥርዓት ይፈጸምበታል።  

የሄቦ በዓል እስኪጠናቀቅ ድረስ የየአካባቢው ማኅበረሰብ ተሰብስቦ ይጫወታል፡፡

በየዓመቱ በሚጫወትበት ካኛ (ካንቻ) በሚባል ቦታ ቦጊኛዎች (የቦጋ ተጫዋቾች) በመሰባሰብ የቱቱሩ (የቀንድ መለከት) ድምፅ ያሰማሉ። በየቤቱ ያለውም ይህን ድምፅ ሰምቶ ወጥቶ ይሰበሰብና የሄቦ በዓል ጨዋታ ‹‹ያሆ ያሆ ኤ ያሆ›› እያለ ይጫወታል፡፡ እየዞሩ ይጨፍራሉ። በዚህ መልኩ ከተጫወቱ በኋላ ባህላዊ መጠጡ (ቦርዴ) የማኡሻና ምግብ ኮበና ይቀርባል። ከበሉ ከጠጡ በኋላ አናታቸውን እንዲቀቡ ቅቤ ይሰጣቸዋል። ባናታቸው የተቀቡትን ቅቤ ጋሻቸውን ጭምር በመቀባት፡-

 ‹‹ጎር ዎታውቶ፣

ዎኔትስ ይኔትስ ካታውቶ፣

ሚያስ ፉፍና ፉቱ ኮንተፋው›› – ጎር የሄቦ ጌታ ይባርክዎ፣ ዓመት ዓመት ያድርስዎ፣ ከብቶችዎ ተወልደው እንደ አሸዋ አፈር ይብዛልዎት- ብለው ይመርቃሉ። የሄቦ በዓል ልዩ ግምት ተሰጥቶት በመስከረም 17 ከሚከበረው የመስቀል በዓል ጋር በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ እስከ ጥቅምት መግቢያ ይዘልቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...