Wednesday, December 6, 2023

መፍትሔ ያጣው የግጭት አዙሪት የደቀነው አደጋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሐሙስ መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ መነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የውይይቱ አንዱ ማተኮሪያ በኢትዮጵያ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ ስለተጋረጡ የፀጥታ ሥጋቶች ነበር ብሎታል፡፡

ብሊንከን በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ያሉና እየተባባሱ የመጡ የፀጥታ ችግሮች አገራቸው እንዳሳሰባት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ አንድነቷ ብቻ ሳይሆን ሰላሟ የተጠበቀ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሚፈልጉ ብሊንከን ተናግረዋል ተብሏል፡፡  

መፍትሔ ያጣው የግጭት አዙሪት የደቀነው አደጋ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ በንብረት ላይ የደረሰ ውድመት

ብሊንከንና አገራቸው አሜሪካ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አገሮችም ቢሆኑ በተመሳሳይ መንገድ የኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ አሁን አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ለመውጣት ሁሉንም ወገኖች አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል የሚሉ ድምፆች በየአቅጣጫው በዝተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ያለ ምንም ተጨባጭ ሁኔታ የሚስተጋባ የቁራ ጩኸት ሳይሆን፣ አገሪቱ የምትገኝበትን አሳሳቢ ፖለቲካዊ ተክለ ቁመና በማገናዘብ የሚሰጥ ምክረ ሐሳብ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

በኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የሕግ የበላይነት እየተሸረሸረ መንግሥት አልባነት እየተፈጠረ ነው የሚሉ ወገኖች የሚያነሱትን ሐሳብ ተጨባጭ ለማድረግ በርካታ ማሳያዎችን ያነሳሉ፡፡

ከሰሞኑ መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማና ጭልጋ ወረዳዎች የቅማንት ታጣቂዎች መሆናቸው በተነገረ ኃይሎች ወደ 14 ሰላማዊ ዜጎች መታገታቸው መነገሩ፣ በኢትዮጵያ ሥርዓተ አልበኝነት የመስፋፋቱ አንድ ማሳያ ነው ሲባል ሰንብቷል፡፡

ከቀናት ቀደም ብሎ ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አውራ ጎዳና ተብላ በምትጠራው ትንሽ ከተማ ከኦሮሚያ ተነሱ በተባሉ ታጣቂዎች መፈጸሙ የተነገረው ጥቃትና ውድመት፣ በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት አልበኝነት በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃትና ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑ ማጣቀሻ ሆኖ ሲቀርብ ሰንብቷል፡፡

በዚሁ ሰሞን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በሆነው የባቢሌ አካባቢ በሁለቱ ክልሎች የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ እያደገ የእርስ በርስ ጦርነት መልክ እየያዘ መምጣቱን አንዱ ማሳያ ሆኖ ሲቀርብ ታይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት መኖሩን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከቱ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች መታየት ከጀመሩ አምስት ዓመታት መቆጠራቸውን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ የፖለቲካ ለውጥ በአገሪቱ በተደረገ ማግሥት በባንዲራ ቀለማትና ለፖለቲካ ኃይሎች በሚደረጉ የድጋፍ ሠልፎች መዘዝ ትንንሽ ግጭቶች መፈጠር መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

በሒደት በለገጣፎ አካባቢ ሕገወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ ስም የተፈጠረው ግጭት ይነሳል፡፡ በቡራዩ የደረሰው ማንነት ተኮር ግድያና ጥቃት ደግሞ የፖለቲካ ለውጡ ምንነትን በተመለከተ ጥያቄ ያስነሳ ነበር፡፡ በአማራ ክልል የትግራይ ክልል መተላለፊያ መንገድ መዘጋትና አልፍ ገደም እያለ ይከሰት የነበረው ግጭት ኢትዮጵያ አደጋ እንደገጠማት አስረጅ መሆኑ ይነገራል፡፡

ወደ ሥልጣን ገና እንደ መጣ በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ከፌዴራሉ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ማፈንገጥ የሚታይበት በክልሉ ባለሥልጣናት የተመራ ጥቃትና ግጭትን በማስቆም ሥራ የተፈተነው የለውጡ መንግሥት፣ በተከተሉት ወራትም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ሲፈተን ነው የቆየው፡፡ ለውጡ በመጣ በጥቂት ወራት ያጋጠመው የጌዴኦ አካባቢ ማንነት ተኮር ጥቃትና ማፈናቀል አገሪቱ ከቀውስ ጋር ተያይዞ ስሟ በተደጋጋሚ እንዲነሳ ያደረገ ነበር፡፡

የትግራይ ጦርነት እስከፈነዳበት ጊዜ ድረስ አገሪቱ ከቀውስ አዙሪት ሳትላቀቅ ሁለት ዓመታት መሻገሯ ይታወቃል፡፡ በተለይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይከሰት የነበረው ግጭት እጅግ ደም አፋሳሽ ነበር፡፡ በአማራ ክልል በቅማንት፣ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አካባቢ ይደርሱ የነበሩ ግጭቶችም የተደጋገሙ ነበሩ፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የፖለቲከኛው የአቶ ጃዋር መሐመድ ቤት በፖሊሶች ተከበበ በሚል በመላው ኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ግጭትና ውድመት፣ መንግሥት ራሱ ባመነው ከ86 ያላነሱ ንፁኃንን የቀጠፈና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ራሳቸው በፓርላማ ስለሁኔታው ባስረዱበት ወቅት፣ እሳቸው ሥልጣን ከያዙ ወዲህ 113 ግጭቶች መከሰታቸውን ተናግረውም ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) የግጭቶችን አኃዝ፣ እንዲሁም የጉዳት መጠን በመዘርዘር ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የከፋ ቀውስ እንዳልገጠማት ተከራክረውም ነበር፡፡ የጉዳቱና የቀውሱ ሁኔታ እንደ አሜሪካ ባሉ የሠለጠኑ አገሮች ከሚደርሰው የጦር መሣሪያ ነውጠኝነት አደጋ ጋር እንኳ ሊነፃፀር የማይችል ስለመሆኑ ለማስረዳት ጥረት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነበር፡፡

በሒደት ግን እንደታየው የኢትዮጵያ የግጭት አዙሪት በቁጥርም ሆነ በአውዳሚነት አደገኝነቱ በእጅጉ እየሰፋ ነበር የሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2013 ዓ.ም. ‹‹መንግሥት ያለ አይመስልም ነበር›› በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት፣ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ፣ በሐረሪና በአዲስ አበባ አካባቢዎች የደረሰው ቀውስ ከባድ እንደነበር አመላክቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሰፊው ሲደርስ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት የማንነት፣ እንዲሁም የዞንና የክልልነት ጥያቄዎችን ታኮ በቀድሞው የደቡብ ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ በትግራይ ክልል ጦርነት እስከ ተጀመረበት ጊዜ ድረስ ይኼው የግጭት አዙሪት አድማሱን አስፋቶ በሰላም የኖሩ ክልሎችን ጭምር እያዳረሰ ነው የቀጠለው፡፡

በጊዜው ለእነዚህ ሁሉ በየአቅጣጫው ለሚደርሱ ሁከቶችና ግጭቶች ምንጭ በመሆን፣ እንደ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ የመሳሰሉ ኃይሎች ነበሩ ተጠያቂ ሲሆኑ የቆዩት፡፡ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔን የመሳሰሉ ኃይሎች ላይ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ በመውሰድ ችግሩን ማስቆም ይቻላል የሚለው አመለካከትም፣ በወቅቱ በብዙኃኑ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ሰፊ ቅቡልነት ያገኘ አመለካከት እስከመሆን የደረሰ ነበር፡፡

በዚህ መሰል የፖለቲካ ከባቢ አየር ውስጥ ሆና ወደ ጦርነት የገባችው ኢትዮጵያ የገጠማትን ጦርነትም ሆነ ሲፈትናት የዘለቀውን የግጭት አዙሪት በስተመጨረሻ በድል እንደምትወጣ የብዙዎች እምነት ነበረ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ሳይሆን ቀረ፡፡ ጦርነቱ ለሁለት ዓመታት ዘለቀ፡፡ በየአካባቢው የሚገጥሙ ግጭቶችና ቀውሶችም መልክና አውዳሚነታቸውን ቀይረው መከሰት ቀጠሉ፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እኩል በወለጋ የተለያዩ ዞኖች ያጋጠሙ ተደጋጋሚ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች እስካሁንም አለማባራታቸው ይታወቃል፡፡

በደቡብ ክልል የማንነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ታከው የሚፈጠሩ ቀውሶችም በዚህ ወቅት ተከታትለው ነበር የተፈጠሩት፡፡ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም አሰቃቂ ግጭቶች ማጋጠማቸው ቀጥሎ ነበር፡፡ አጣዬ (ኤፌሶን) በምትባለዋ የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከተማ የደረሰው ተደጋጋሚ ውድመት ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለው የቀውስ አዙሪትን ክብደት ማሳያ ሊባል እንደሚችል ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ በጋምቤላ ክልል በ2014 መገባደጃ በ2015 መቀበያ ግድም ያጋጠመው ግጭት፣ ቀውሱ በአገር ላይ ጭምር አደጋ ይዞ እየመጣ መሆኑን ቀድሞ የጠቆመ ምልክት መሆኑ በብዙዎች ይወሳል፡፡

በጋምቤላ ከተማ ኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በጥምረት ጥቃት በመክፈት የክልሉን መንግሥት ሥልጣን የመቀማት ሙከራ አደረጉ መባሉ፣ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ሲጠናከር ወዴት እንደሚሸጋገር አንድ ማሳያ ነው ተብሎ ነበር፡፡

የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ቢቋጭም በየቦታው የሚፈነዱ፣ በመንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች መበራከት ግን ሌላ ዓይነት ሥጋት እየደቀኑ መሆኑ ይነገራል፡፡

ልክ እ.ኤ.አ. ከ1769 እስከ 1855 በኢትዮጵያ እንደ ነበረው ዘመነ መሣፍንት ወቅት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በየአካባቢው በሚፈጠሩ የጎበዝ አለቆች ልትከፋፈል ትችላለች የሚል ሥጋት እየተፈጠረ ነው፡፡

ሰላማዊ ዜጎችን በማገት ገንዘብ የሚጠይቁ የታጠቁ ቡድኖች መብዛታቸው፣ እንዲሁም በየአካባቢው መንግሥትና መንግሥታዊ መዋቅሮችን የሚገዳደሩ ኃይሎች መፈልፈላቸው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሥርዓት አልበኝነት እንዳያነግሥ እየተፈራ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ኃይሎችም ሆነ ከመንግሥት መዋቅር ውጪ የሆኑ አካባቢዎች በአገሪቱ እየበዙ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ልክ እንደ መንግሥታዊ አካል ሁሉ መንግሥትን ተክተው ግብር እያስከፈሉና በራሳቸው መንገድ ሕግና ሥርዓትን እናስከብራለን እያሉ አንድን አካባቢ የሚቆጣጠሩ ኃይሎች በተለያዩ ክልሎች መብቀል መጀመራቸውም ይሰማል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ልክ ጎረቤት ሶማሊያ እንዳለፈችበት መንግሥት አልባነትና ሥርዓት የለሽነት ሁሉ ኢትዮጵያም ልትገባ ትችላለች የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

በሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ1991 የዚያድ ባሬ መንግሥት መገርሰሱን ተከትሎ ፑንትላንድና ሶማሌላንድ የተባሉ ራስ ገዝ ግዛቶች ተገንጥለው ተፈጠሩ፡፡ ይህ ሳያንስ ለ20 ዓመታት የሶማሊያ የጦር አንጃዎች አገሪቱን በጎሳ ጦርነት ዘፍቀዋት ቆዩ፡፡ ለረዥም ዓመታት አንድ ወጥ መንግሥት ለመፍጠር ስትቸገር የኖረችው ሶማሊያ፣ አሁንም ድረስ የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማቆም እንዳቃታት ይታወቃል፡፡

ይህ የሶማሊያ ታሪክ በኢትዮጵያ እንደሚደገምና ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚፈጠር የሚናገሩ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ በተለያዩ ክልሎች የፌዴራል መንግሥቱ የማይደርስባቸውና በተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የሚተዳደሩ አካባቢዎች መብዛት፣ በቋፍ ላይ ያለውን የአገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ለመንግሥት አልባነት የመጋለጥ አደጋ የሚያጠናክር ሥጋት እንደሆነ እየተገመተ ነው፡፡

በአንድ ወቅት በዩቲዩብ በተለቀቀ ቪዲዮ ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ፣ ‹‹እነዚህ ጦርነቶች ካልቆሙ ሩዋንዳንም ሆነ ሶሪያን የሚያስንቅ በጣም ዘግናኛ የሆነ ዕልቂት በኢትዮጵያ ይመጣል፤›› በማለት መናገሩ ይታወሳል፡፡ ጃዋር በአሜሪካ በተካሄደ መድረክ የተናገረው ነው በተባለው በዚሁ ንግግሩ ላይ በለውጡ ማግሥት አገር የሚመሩ ኃይሎች ኢትዮጵያን እናበለፅጋለን ቢሉም ግባቸው ምንም ይሁን የሄዱበት መንገድ ‹‹አገሪቱን ያፈራረሰ፣ አገሪቱን ያዳከመ በሕዝቦች መካከል ያለው ቅራኔ ወደ ጠላትነት እንዲያድግ ያደረገ፣ የመንግሥትን አቅም ያዳከመ፣ መንግሥት ሲዳከም በምትኩ በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ አንጃዎች እየበቀሉ አገርን በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ የፈጠረ ነው፤›› በማለትም ገልጾ ነበር፡፡

የታመመ ሰው ከሕመሙ መጀመርያ ለመውጣት መታመሙን አምኖ መቀበል እንደሚኖርበት የጠቆመው ጃዋር፣ ‹‹እስካሁን በተኬደበት መንገድ መሄድ አያዋጣም፤›› ብሏል፡፡ መንግሥት በዋናነት ጦርነት ማቆም እንዳለበት የተናገረው ጃዋር፣ ‹‹በኢትዮጵያ ከእንግዲህ በጦርነት የሚፀና ሥርዓት የለም፤›› በማለትም ተናግሯል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ከሕወሓት ጋር የተደረገውን ጦርነት፣ ‹‹100 ሰዎች ልንፈታው በምንችል ችግር 100 ሺዎች ያለቁበት›› ሲልም ይጠራዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ብዙ ዓይነት ግጭቶች አሉ ያለው ጃዋር፣ እነዚህን ጉዳዮች በጦርነት እንፈታለን ማለቱ ችግሩን ወደ ባሰ ሁኔታ ማባባስ በመሆኑ አገራዊ የሰላም ጥሪ አድርጎ፣ ተኩስ በማቆም ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲመጡ ማድረግ የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት መሆን እንደሚኖርበትም ጠቁሟል፡፡ ጃዋር በንግግሩ በጦርነት የምትመጣ ኢትዮጵያ እንደማትኖር ነው ያሰመረበት፡፡

ይህን መሰሉን የጃዋር ጥሪ ከተመፃዳቂነት የቆጠሩ ወገኖች ግን በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ባስነበቡት ጽሑፍ የጃዋርን ፖለቲካዊ ቁመና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይጥሉታል፡፡ ዮናስ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፋቸው ጃዋር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለተፈጠሩ ቀውሶች ከማንም በፊት ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባው ነው የሞገቱት፡፡

ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት፣ እንዲሁም ወደ መንግሥት አልባነት እየተንደረደረች ነው የሚሉ ወገኖች ይህ ሥጋት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩን ያወሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአማራ ክልል መንግሥት ከፋኖ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለውን ጦርነት አንዱ ምልክት አድርገው የሚያስረዱ አሉ፡፡

በአማራ ክልል ስላለው ጦርነት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለው የሰላም መደፍረስ በአገሪቱ ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው አደጋ የተጠየቁት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፣ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ይላሉ፡፡  

የአማራ ክልል ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከትግራይ ክልሎች ጋር እንደሚዋሰን፣ ከዚህ በተጨማሪም ከኤርትራና ከሱዳን ጋር እንደሚዋሰን የጠቀሱት አቶ ሙሉዓለም፣ ‹‹አሁን ያለውን ግጭት በሰላም መፍታት ካልተቻለ አገራዊና ቀጣናዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ማዕከል ነው የሚሉት ተንታኙ፣ ‹‹ልክ እንደ ትግራይ ጦርነት በከበባ የሚፈታ ችግር በአማራ ክልል የለም፤›› ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ‹‹በሥርዓት ለውጥ ይመለስልናል›› ወደ የሚል ደረጃ መሸጋገሩን ጠቅሰው፣ ትግሉ የህልውና በመሆኑ በኃይል እንደማይቆም አስረድተዋል፡፡  

‹‹ወደ መንግሥት አልባነት መሄዳችን ብቻ ሳይሆን ወደ እርስ በርስ ዕልቂት እያዘገምን መሆናችን ያሳስበኛል፡፡ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል መንገድ በገዥው ወገን እየተቀየሰ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ በአውራ ጎዳና ከተማ የተፈጸመው የአማራ ተወላጆችን የማፈናቀልና የማፅዳት ዘመቻ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ የሚቀሰቅስ ዓይነት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ይህን ዓይነቱ ጥቃት መቆም አለበት፤›› ሲሉ አቶ ሙሉዓለም ይናገራሉ፡፡

አሁን የእርስ በርስ ጦርነት የተፈለገ እንደሚመስል የተናገሩት ተንታኙ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ተከሰተ ማለት በርካታ የውጭ ተዋንያን እጃቸውን የሚያስገቡበት ነው የሚሆነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡ የእርስ በርሱ ጦርነትም ሆነ አሁን ያሉ ቀውሶች ሄደው ሄደው የመበተን አደጋን ሊጋብዙ እንደሚችሉ ነው አቶ ሙሉዓለም ያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ በዋናነት የማዕከላዊውን ፖለቲካ የሚዘውሩት የሦስቱ ብሔሮች በዋናነት የአማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ ብሔሮች የፖለቲካ ልሂቃን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ እስካሁን እንደታየው ከሆነ ደግሞ ከሦስቱ ወገኖች የወጡ ልሂቃን አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ የፖለቲካ ሚና መጫወታቸው እያጋደለ መምጣቱን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነትና የመበታተን አደጋ ተጋርጦባታል በሚባልበት በዚህ ወቅት የማዕከላዊውን ፖለቲካ ለመግራት አቅምና ብቃቱ ኖሯቸው ወደ ዳር ያፈገፈጉ የሌሎች ብሔሮች የፖለቲካ ልሂቃን በዝምታ መዋጣቸው ሊበቃ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የሃዲያ፣ የከምባታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የካፋ፣ የስልጤ፣ የጌዴኦና የሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ልሂቃን በተቻለ መጠን የማዕከላዊው ፖለቲካ እንዲቃና የድርሻቸውን እንዲወጡ በርካቶች እየወተወቱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -