Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚገኘው ኢኮኖሚውን በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን ነው›› ውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር/ኢንጂነር)፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ

በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ዘርፉ በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ በተፈጠሩ የተለያዩ ቀውሶች ሳቢያ ተንገራግጯል ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ሁኔታዎችን ማባባሱን የዘርፉ ተዋንያን ሲገልጹ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በተለያዩ ሰበቦች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ እየታየ ያለው ተግዳሮት ኮንትራክተሮችን በእጅጉ እየፈተነ ብቻ ሳይሆን፣ ከጨዋታ ውጪ እያደረገውም ነው የሚለው አስተያየት ተደጋግሞ እየተነገረ ነው፡፡ በዋጋ ንረትና በተያያዥ ችግሮች ምክንያት በጅምር የቀሩ ፕሮጀክቶች በርካታ ሲሆኑ፣  ፕሮጀክቶቹን ከቆሙበት ለማስቀጠል መፍትሔ ይሆናሉ ተብሎ የታመነባቸው ዕርምጃዎችም ለውጥ አላመጡም ይባላል፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ ከባድ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያለውን አሁናዊ ችግርና ቀጣይ ዕጣ ፈንታና የመፍትሔ ሐሳቦች በተመለከተ ዳዊት ታዬ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱ ከሆኑት ከውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር/ኢንጂነር) ጋር ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በስፋት ይነገራል፡፡ አብዛኞቹ ኮንትራክተሮችም ከሥራ ውጪ እየሆኑ ነው ይባላል፡፡ በተለይ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ያጋጠመው ችግር ብዙዎችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ለበርካታ ፕሮጀክቶች መቆም ምክንያት መሆኑም ይሰማል፡፡ ይህንን ግልጽ ችግር በመገንዘብ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ምን አስገኝተዋል? በአጠቃላይ ችግሩን እንደ ባለሙያ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፍኖተ ካርታና የአሠራር ስትራቴጂው ላይ በትክክል ተብራርቶ እንደተቀመጠው፣ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ሲከሰትና የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በቀላሉ ይጎዳል ይባላል፡፡ ሁለተኛው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ ዕቃዎች ከውጭ የሚያስመጣ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገዋል፡፡ የሦስተኛ ዓለም አገሮች  እንደሚገጥማቸው ችግር ሁሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት ኢንፖርት ሰብስቲትዩሽን (ተኪ ምርቶች) ላይ መሥራት ዋነኛ ሒደት ነው ይላል፡፡ ሦስተኛው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላለመግባባት ተጋላጭ ስለሆነ በአማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች መጠቀም፣ በጊዜ መፍትሔ እየሰጡ ጉዳቱን የመቀነስ ዕድሉን ያሰፋል ይላል፡፡ እነዚህ ነገሮች እስካልተተገበሩ ድረስ የሚከሰተው ነገር ሁልጊዜ ችግር ሆኖ ሥራ ተቋራጩንም ባለቤቱንም ችግር ውስጥ ይከታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጠንክረን መሥራት ያለብን በተቀረፀው ስትራቴጂ መሠረት መፍትሔዎቹን ለመተግበር መሞከር ነው፡፡ እርግጥ ነው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ግልጽ በመሆኑ፣ መፍትሔውም በስትራቴጂው ላይ የተቀመጡትን መሠረታዊ ጉዳዮች መነሻ በማድረግ መፍታት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ጥቅል የሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን በትክክል ማውረድ ተችሏል? መተግበር ካልተቻለስ?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- እንደ መፍትሔ የተቀመጡ ጥቅል ጉዳዮችን በፍጥነት መፍታት ካልቻልን፣ ውይይት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባሉበት ለተከሰቱ ጉዳቶች ማካካሻ መፍጠር ተገቢው መንገድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የመንገዶች ባለሥልጣን የፕራይስ ስካሌሽን ካፕ (የዋጋ ጭማሪ ገደብ) አንስቷል፡፡ ሁለተኛ ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ለተፈጠሩ ችግሮች በአማካሪ ድርጅት ጥናት እያስጠና ነው፡፡ የሚደርስበት መፍትሔ ጊዜ መፍጀቱ እንዳለ ሆኖ በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡   

ሪፖርተር፡- ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁናዊ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋናው ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት በርካታ ፕሮጀክቶች ተስተጓጉለዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር መፍታት ካልተቻለ ፕሮጀክቱን ማስቀጠል አይቻልም ይባላልና ለዚህስ መፍትሔው ምንድነው ነው?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- የኢንፖርት ሰብስቲትዩሽን (ተኪ ምርት) እና የውጭ ምንዛሪ ችግሮች ላመጡት የዋጋ መናር ለሕንፃዎች በተወሰነ ዕፎይታ በ‹‹ፒፒኤ›› እና በኮንስትራክሽንና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በኩል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ በተለይ በአብዛኛው በዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ላይ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ፍንጭ ተሠርቶ ነበር፡፡ አተገባበሩን ስላልተከታተልኩት መፍትሔውን ያምጣ አያምጣ ለመናገር ይቸግረኛል፡፡ በተለይ በጊዜ መጓተት ያለውን ችግር ከፈቱት የተሰጠው መመርያ መፍትሔ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የመፍትሔ ዕርምጃዎች ናቸው ተብለው የተላለፉ ውሳኔዎችና የተሰጡ ተስፋዎች በተጨባጭ ካልተተገበሩ ችግሩን አያባብስም? በተለይ የዋጋ ንረቱ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ ስለሚነገር፣ በርካታ ኮንትራክተሮች በመፍትሔ ዕጦት ሥራቸውን አቁመው እስከ መቼ ይቀጥላሉ?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- የሥራ ተቋራጮች ከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያሉት፡፡ አቅማቸው በተከሰተው የዋጋ ንረት ሳቢያ ተንገራግጯል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ ችግሮች አሉ ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ተቀራርቦና ተነጋግሮ የአገርንም ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ መሞከር ነው፡፡ ሁሉም ችግሮች በተጨባጭ ያሉ ናቸው፡፡ ያለበለዚያ ችግሩን እያሰፉ ከመሄድ በስተቀር መፍትሔ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት አንድ ላይ በመሆን ተነጋግረውና የተፈቀዱ መንገዶችን እያሰፉ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ማድረግ ቢቻል ነው የእኔ ግንዛቤ፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው በውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ዋጋ መዋዠቅ ተወሰነ ችግር ውስጥ እንዳለ ግን ይገባኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አሁን የፕሮጀክቶች በብዛት አለመኖር ይሁን ወይም ደግሞ አቅርቦቱ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ ባላውቅም፣ በሲሚንቶና በብረት ዋጋ ላይ የተወሰነ አዝማሚያ እየተመለከትን ነው፣ ይህ ጥሩ ነው፡፡ የዋጋ መረጋጋቱ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁናዊ ችግሮችን ለመፍታት ሙከራዎቹ ተሳክተዋል ተብለው አይታሰቡም? በሙከራዎቹ አለመሳካት ደግሞ የፕሮጀክቶችን የመጠናቀቂያ ጊዜ እያረዘመ መምጣቱ ወጪያቸውን በዚያው ልክ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርና አገርንም ዋጋ የሚያስከፍል እየሆነ ነው? ስለዚህ በኮንትራክተሮችም ላይም ሆነ በአገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ምን መደረግ ይኖርበታል ተብሎ ይታመናል?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- በቅርርብ መነጋገር ነው የመፍትሔው አንዱ አካል፡፡ እውነቱን አለመካድ ነው ትልቁ ነገር፡፡ በሁሉም በኩል የተፈጠረውን ነገር ሳይክዱ በትብብር ለመሥራት ከተቻለ ምንም ይሁን ምን የሆነ መፍትሔ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ቢያብራሩልኝ?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- በግልጽ እንደምናየው የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ መካድ የለበትም፡፡ ተከስቷል አልተከሰተም፣ ወይም መረጃውን አቅርብ አታቅርብ እየተባለ ከተሄደ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ መከሰቱን ሁላችንም የምናውቀው በመሆኑ፣ በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ንትርክ ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ደረሰኝ ማምጣት የቻለ አለ፣ ያልቻለ አለ፡፡ ስለዚህ በኖርማል ጊዜ የምናስተናግድባቸውን መንገዶች፣ እያንዳንዷን ማስረጃና ሪከርድ ይዘህ ይህ የምትሠራበት ሒደት ለሁሉም ፕሮጀክቶች ይሠራል ብዬ ለመናገር ይከብደኛል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መታሰብ ያለበት እያንዳንዱን በፕሮጀክት ቤዝ ኮንሰልታንቱና ባለቤቱ ያስተዳድሩት ብለህ ከተውከው፣ ለተጨማሪ አለመግባባትና ፕሮጀክቱን የማዘግየት ዕድል ያመጣል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ካለ የሥራ ተቋራጩና ባለቤቱ (አስገንቢው) ተለያይተው፣ እንደ አዲስ ቀሪው የፕሮጀክቱ ሥራ ጨረታ ወጥቶ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ዋናው ነገር የአድቫንስ ፔይመንት (ቅድመ ክፍያ) ሁኔታ ላይ መነጋገር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከባንኮች ጋር የተገናኘም ስለሆነ በባንኮች ላይ ትልቅ ጫና ሊመጣ ስለሚችል በጥንቃቄ ማስተዳደር ይፈልጋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግንባታ እንቅስቃሴያቸው የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን ቀሪ ሥራ ለጨረታ ማውጣት ግን የበለጠ የፕሮጀክቱን ወጪ ይጨምራ የሚል መከራከሪያ ብዙ ጊዜ ስለሚነሳ ከዚህ አንፃር ይህ መፍትሔ ሊሆን ይችላል?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለሌላ ተቋራጭ በጨረታ መስጠት ራሱ አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በአብዛኛው የግንባታው ባለቤት አካል ከሁለት መነሻ ነው ችግር የሚሆንበት፡፡ አንደኛው እጠየቃለሁ ብሎ ስለሚፈራ ነው፡፡ ኮንትራክተሩም በቂ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ ስለሚቸገር የዶክመንቴሽን ችግር ስላለበት፣ ነገሮችን መፍታት የምትችልበት መንገድ ስለሌለህ ችግር ውስጥ ይከትሃል፡፡ ሁለተኛ ባለቤት ዘንድ ያለው ችግር እውነታውን እንደ እውነት ተቀብሎ መሄድ ቢሞከር፣ የመክፈል አቅሙ ደግሞ ሌላ ሁለተኛ ነገር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ባለበት ደረጃ ለማስተዳደር ባለቤት ጋር መሠረታዊ ችግር የሚሆኑ እነዚህ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ እንደ             ሙከራ የተወሰኑ ፕሮጀክቶችን አንተ ይህንን ነገር ጨርስ ብንልህ ስንት ታስጨምራለህ ተብሎ ይቀመጥ፡፡ ሌሎች ተጫራቾችም ጨረታው ወጥቶ የሚሰጠው ዋጋ ይታይ፡፡ የእነዚህ ልዩነቶች ከፍተኛ መሆን በራሱ መፍትሔ ያመጣል፡፡ ያንን ደፍሮ መቀጠል የሚያስችል መንገድና ዶክመንቴሽን ማበጀት ስላልተቻለ ነው ችግሩ የሚታየው፡፡ አንዳንዶች ላይ ተሠርቶበት ለውጥ ያመጡ አሉ፡፡ በመሆኑም ድምር ሥራዎችን ለአዲስ ኮንትራክተር መስጠት በራሱ አንድ የመፍትሔ አካል ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በተጠቃቀሱት ምክንያቶችም ሆነ በሌሎች ተፅዕኖዎችና ጫናዎች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በጣም ተቀዛቅዟል ይባላል፡፡ አዳዲስ የግንባታ ጨረታዎችም እየወጡ አለመሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህ በአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት አንተም የገለጽከው በኮንስትራክሽን ስትራቴጂው ይህንን ነገር ግልጽ አድርጎታል፡፡ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ሲከሰት ወዲያው የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት የአሜሪካ ኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ሲገባ 2,400 ኮንትራክተሮች በነጋታው አልነበሩም፡፡ ከጨዋታ ውጪ ሆኑ፣ ከስረዋል ማለት ነው፡፡ በዚያ አገር ኪሳራ ማስመዝገብ በቀላሉ የሚስተናገድበት ሕግ ስላለ በዚያ ሒደት ሄደዋል፡፡ እኛ አገር ይህንን ለማድረግ ሰነዱ የለም፡፡ ሕጉ እንኳን ቢኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በእውነታ ደረጃ ስታየው እውነቱ አለ፡፡ የሚካድ አይደለም፡፡ ግን ኮንትራክተሩም ባለቤቱም በሰነድ አስፈጻሚው በሕጉ መንገድ አስኪደው ሊጨርሱበት የሚችሉበት ዕድል አናሳ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመቀበል መፍሔዎች መስጠት ነው፡፡ እነዚህን መፍትሔዎች ለመተግበር የተወሰነ ሞክሯል፡፡ ተቀራርቦ እነዚያ የመጡ የመፍትሔ ሐሳቦች ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችልበትን ሁኔታ መሥራት፣ ቀሪ ካለም እየተነጋገሩ መፍትሔ ማምጣት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁን ታይቶበታል ለተባለው ችግር መንስዔው በግልጽ የሚታወቅ ከሆነ፣ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ እየሰጡ መሄድ አንድ ቁልፍ ነገር ሆኖ ኮንትራክተሮቹ በሥራቸው ላይ ለመቆየት አዳዲስ ሥራዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ግን አዳዲስ የግንባታ ጨረታዎች የሉም እያሉ ነው፡፡ የአዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ አለመኖር ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- አንድ አገር ለተከሰተ ችግር መካሻ ሊሆን የሚችል በቂ ገንዘብ በሌለበት ሁኔታ አዲስ መክፈት ይችላል ወይ የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው፡፡ ካልቻለ ምንድነው የምታደርገው? ያሉትን ላስጨርስ? አቅሜ አይፈቅድም፣ ፕሮጀክቶችን እያወጡ መቀጠሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ደግሞ በሕዝብ ላይ ዋጋ ያንራል ብለው ኢኮኖሚስቶች ከመከሩህ የምትወስደው ዕርምጃ ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶቹ የዋጋ ንረትን ከሚጨምሩ ምክንያቶች አንዱ ፕሮጀክቶች ብዛት መውጣታቸው ነው ካሉም የምትወስዳቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገርንም አቅም መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ተደማምረው ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች በሌሎች አገሮችም የተከሰቱ ናቸውና እኛ በማደግ ላይ ያለን አገር በመሆናችን፣ ለእንዲህ ዓይነት ነገር ተዘጋጅተን ብዙ አንቆይምና ሊያጋጥመን የሚችል ነገር ነው፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ ለኮንትራክተሮች ሥልጠና በምሰጥበት ወቅት ‹‹ዳይቨርሲፊኬሽን›› ያስፈልጋል፣ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ልትቸገሩ ስለምትችሉ ቢዝነሳችሁን ‹‹ዳይቨርሲፋይ›› አደርጉ፣ ያለበዘሊያ ከጨዋታ ውጪ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ብዬ ለማሠልጠን እሞክራለሁ፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ነገሮች በብዙ አገሮች ይከሰታሉ፡፡ የሠለጠነው ዓለም በራሱ የሕግ አግባብ የሚያይበትና የተወሰነ የሚለውጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ ይህንን በማድረግ ዕድሜያቸው እንዲረዝም ይደረጋል፡፡ እንደ እኛ ያሉ አገሮች ደግሞ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ችግር ሲያጋጥም ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር አደጋውን ተጋርቶ ከችግር ለመዳን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥትም እኮ ፕሮጀክቶች ባለመኖራቸው ማግኘት ይገባ የነበረውን ጥቅም እንደሚያሳጣው ይረዳል፡፡ ሁሉም ነው ተያይዞ ችግር ውስጥ የሚገባው፡፡ ብዙ ጊዜ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የመጀመርያ ተጎጂ ስለሚሆን ነው እንጂ ችግሩ ሁሉም ላይ ይንፀባረቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አሁን ካለበት ችግር አውጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና እንዲቀጥል ለማድረግ እንደ ባለሙያ የሚታይዎት ተስፋ ምንድነው?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- የዋጋ ማረጋጋት፣ ኢንፖርት ሰብስቲትዩሽን (ተኪ ምርቶች) ላይ ብዙ መሥራት፣ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ሥራ ብቻ ሳይገደቡ ወጣ ብለው የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ አሁን የተከሰተውን ችግር ደግሞ በጋራ ቁጭ ብሎ አደጋውን ተጋርቶ ለማዳን መሞከር ከተቻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ የእኔ ተስፋም ይህንን በማድረግ ለውጥ ይመጣል የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አቅም ለማሳደግ በተጨባጭ ምን መደረግ አለበት? አሁን በግልጽ እንደሚታየው በአገር ውስጥ ያሉትን ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚወስዱት ውጭ ኮንትራክተሮች ናቸውና ቢያንስ ይህንን እንዲያገኙ ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ኢንጂነር ውብሸት፡- አንዱ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር በሰብ ኮንትራት የሚሠሩበትን መንገድ ማበጀት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊሠሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶቻችን ለይቶ ሰብ ኮንትራት አድርጉ ብሎ አቅጣጫ መስጠትም መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በእኛ አገር ባለሙያዎች ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን የውጭ ባለሙያዎች እንዳይሠሩ በማድረግና የመሳሰሉትን በማድረግ አቅማቸውን ማጎልበት ይቻላል፡፡ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚገኘው ኢኮኖሚውን በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን ነው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...