Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገቡት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዘመናዊ ኮርፖሬት አስተዳደርና ፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ሥራ ላይ መዋሉ ይታወቃል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች አመራርና አሠራርን መከታተል፣ መብት ማስከበርና ሌሎችም የተለያዩ ዓላማዎች ለማሳካት፣ በበላይነት የሚቆጣጠረው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ነው፡፡ 

አስተዳደሩ እነዚህን ዋና ዓላማዎች ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ በየዓመቱ ሲተገብር ቆይቷል፡፡  

በእነዚህ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት የ2015 በጀት ዓመት ክንውን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ አፈጻጸሙም አወንታዊ እንደነበር ሪፖርተር የተመለከተው የአስተዳደሩ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ይጠቁማል።

የልማት ድርጅቶቹ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ካሳመዘገቧቸው ጠንካራ አፈጻጸሞች አንዱ ተሰብሳቢ የነበሩ ሒሳቦችን በማጥራትና በብድር አመላለስ ረገድ ያስመዘገቡት ውጤት ተጠቃሽ ነው። ከዚህ አኳያ አፈጻጸማቸው ሲመዘንም፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የነበረበትን ተሰብሳቢ ሒሳብ ለማጥራት ባደረገው ጥረት ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን ሪፖርቱ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 10.20 ቢሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳቦችን በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ አቅዶ 10.49 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 103 በመቶ ማሳካቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ36 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሰ ብድሮችን ለመክፈል በያዘው ዕቅድ መሠረት 141.9 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመክፈል ወጥኖ 141.2 ሚሊዮን ዶላር የከፈለ ሲሆን፣ በአፈጻጸሙም ከዕቅዱ 99 በመቶውን እንዳሳካ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ 

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞው ሜቴክ) ደግሞ በበጀት ዓመቱ 374.17 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 419.94 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፡፡

በተሰብሳቢ ሒሳብ ረገድ የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት 127.30 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 122.2 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅድን 96 በመቶ ማሳካቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 10.9 ቢሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ ለመሰብሰብ አቅደው በድምሩ 11 ቢሊዮን መሰብሰባቸውንና ይህም ከዕቅዳቸው 101 በመቶውን ማሳካት እንደቻሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የልማት ድርጅቶች ሽያጭ ገቢን ማሳደግ ረገድ በበጀት ዓመቱ የልማት ድርጅቶቹ ከሚያመርቱት ምርትና አገልግሎቶች ሽያጭ 44.69 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው፣ በበጀቱ ዓመቱ ማብቂያ 45.3  ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘታቸውን፣ ይህም ከዓመቱ ዕቅዳቸው 101 በመቶ ማሳካቱን ሪፖርቱ ይገልጻል። ይህ አፈጻጸም በ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 27 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

የተገኘው ገቢ ከተቋማት ድርሻ አንፃር ሲታይም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 48 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 29.2 በመቶ፣ የኢትዮጰያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት 9.2 በመቶ፣ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ 5.8 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 4.1 በመቶ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት 2.7 በመቶ፣ ብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት 0.6 በመቶ፣ የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን 0.29 በመቶ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን 0.05 በመቶ ማበርከታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡  

የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ትርፍ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ በ2015 በጀት ዓመት በአስተዳደሩ ተጠሪነት ሥር የሚገኙ ዘጠኝ የልማት ተቋማት ከግብር በፊት 6.69 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ዕቅድ ይዘው፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 8.7 ቢሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብ ከዕቅዳቸው 123 በመቶ ብልጫ ያለው ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል። ይህ አፈጻጸም ከ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር በ61 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

የተገኘው ትርፍ በተቋማት ድርሻ ሲታይም፣ በቀዳሚነት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትርፍ ከተገኘው አጠቃላይ ትርፍ 78.9 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 5.1 በመቶ ድርሻ ይዟል። የኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ደግሞ 6 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ 4.4 በመቶ፣ ፖስታ አገልግሎት 2.8 በመቶ፣ ዕዳና ሀብት አስተዳደር 1.4 በመቶ፣ እንስሳት ጤና ጥበቃ 1.3 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ 

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ በበጀት ዓመቱ በነበረባቸው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪ አኳያ ትርፍ ማስመዝገብ አለመቻላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

የልማት ድርጅቶቹ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማሳደግ ረገድ በበጀት ዓመቱ አምስት የልማት ድርጅቶች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በስፋት እንዲያቀርቡ የማበረታታት ጥረት ተደርጓል። በዚህም መሠረት አምስት ተቋማት ተቋማት 440.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ ይዘው የተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይም አራት ድርጅቶች 392.2 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት የዕቅዱን 82 በመቶ አሳክተዋል፡፡

ይህ አፈጻጸም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 182 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ሪፖርቱ ገልጿል። በበጀት ዓመቱ ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 56.6 በመቶውን ድርሻ ሲይዝ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ደግሞ ከኃይል ሽያጭ 25.8 በመቶ ድርሻ አበርክቷል። በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት 0.33 በመቶ፣ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ደግሞ 0.42 በመቶ ድርሻ ማበርከታቸውን በሪፕርቱ ተዘርዝሯል፡፡ 

የልማት ድርጅቶቹ አማራጭ የአገልግሎት ተደራሽነትና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ክትትል መደረጉን፣ በዚህም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ 10 ሺሕ ትራክተሮችን ሊያመርት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት ከቻይናው ኩባንያ ዋይቲኦ (YTO) ጋር ለመሥራት ስምምነት መፈራረሙ ተጠቅሷል፡፡ 

በበጀት ዓመቱ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ንብረቶችን ለሽያጭ መቅረባቸውን፣ በተያዘው ዕቅድ መሠረት 10,432 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 399.70 ሚሊዮን ማግኘት መቻሉን ተገልጿል፡፡ 

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ድርጅት በ2015 በጀት ዓመት ተኪ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡን ሪፖርቱ አመልክቷል። በዚህ መሠረት ወጪ ሊደረግ የነበረው 185.4 ሚሊዮን ዶላር ለማዳን ታቅዶ፣ 123.6 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 66.6 በመቶ ማሳካት መቻሉን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች መካከል 83.3 ሚሊዮን ዶላር የግብዓት አቅርቦት ግብይት ለመፍጠር ታቅዶ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 89.9 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የግብዓት ግብይት መፈጸሙን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶቹ በበጀት ዓመቱ የፈጠሩት የሥራ ዕድል ያስመዘገቡትን ውጤት ማሳያ ነው። በዚህ ረገድ የልማት ድርጅቶቹ በጋራ በበጀት ዓመቱ በቋሚ፣ በኮንትራትና በጊዜያዊነት ለ92,779 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደው ለ65,371 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

የልማት ድርጅቶችን የምርትና አገልግሎት ወጪን በመቀነስ ረገድም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የልማት ድርጅቶቹ በ2015 በጀት ዓመት በጥቅሉ 272.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የመቀነስ ዕቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 177.5 ሚሊዮን ብር ወጪ በመቀነስ የዕቅዳቸውን 65 በመቶ ማሳካታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የበጀት ዓመቱ የመንግሥት ልማት ድርጀቶችን የሥራ አመራር ቦርድ ለማጠናከር ግብ ተይዞ የተሠራ ሲሆን፣ በዚህ መሠረትም በስምንት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ አመራር የነበሩ 29 የቦርድ አባላት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንና ለ34 አዲስ የቦርድ አመራር አባላት ምደባ መስጠቱን ሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ 

በሌላ በኩል የልማት ድርጅቶቹ የመንግሥትን ትርፍ ድርሻ ክፍያ ገቢ እንዲያደርጉ ክትትል መደረጉን፣ በክትትሉ መሠረት በበጀት ዓመቱ ከሦስት ድርጅቶች 457.3 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዲያደርጉ ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ የልማት ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የቻሉት የትርፍ ድርሻ 46.4 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን፣ ይህም ከዕቅዱ 10.1 በመቶ ብቻ መፈጸሙን እንደሚያሳይ ሪፖርቱ አመልክቷል። 

ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን የተጠቀሰው ዋነኛ ምክንያት፣ የትርፍ ድርሻ መክፈል ከሚጠበቅባቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መካከል የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅትና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት በጊዜው ክፍያ መፈጸም ባለመቻላቸው ነው፡፡  

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፋማነት የተሸጋገረ ሲሆን፣ በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል አልሚዎች የተዘዋወሩ ድርጅቶች ከመደበኛና ውዝፍ ክፍያዎች የተሻለ ክፍያ መሰብሰብ መቻሉ በአዎንታዊ እንደሚታይ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ 

በዕቅዱ አፈጻጸም ሒደት ያጋጠሙ ፈታኝ ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ በሒሳብ መዝጋትና ማስመርመር የዘገዩ ድርጅት መኖራቸው፣ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ባጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች ድርጅቶች በአካባቢው የሚሰጡት አገልግሎት መቋረጡና ሌሎችም ችግሮች ለዕቅዱ አለመሳካት ማነቆ ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች