በገነት ዓለሙ
በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ‹‹የዓለም ማኅበር፣ የዓለም ማኅበር፣ ለዘላለም ይኑር፣ ለሰላም ለፍቅር›› እያለ ሲያስዘምረን፣ ሲያስተምረን ዛሬም ድረስ ይህንን የጠቀስኩትን አዝማችም ራሱን፣ ዜማውን ጭምር ከእነ መዝሙር አስተማሪዬ ስም ጋር አስታውሳለሁ፡፡ አግባብ ያለው ነገር ወይም አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር፣ ወይም ተፈጠረ በተባለ ወይም የተፈጠረ በመሰለው ቁጥር አዕምሮዬ ውስጥ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተዘጋጅቶ፣ ተጥዶ፣ ዝግጁ ሆኖ የተቀመጠው ማጫወቻ ዛሬም ድረስ እነሆ ለ60 ዓመት ያህል የሚያሰማኝ መዝሙር፣ የመዝሙር አዝማች ነው፣ ከእነ ዜማው፡፡ ‹‹የዓለም ማኅበር… ለዘለዓለም ይኑር፣ ለሰላም ለፍቅር››ን ወደፊትም ሳስታውሰው እኖራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ይህንን የመሰለ ሚና የሚጫወት፣ እንዲህ ያለ ተፅዕኖ ያለው ሥራ ውስጥ የገቡት አገሪቷ የመንግሥታቱን ድርጅት ከመሠረቱት 51 አገሮች መካከል አንዷ በመሆኗ ብቻ አይደለም፡፡ አዎ፣ እውነት ነው አገራችን ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም. (ጁን 26 ቀን 1945) የድርጅቱን መመሥረቻ ሰነዶች ከፈረሙት አገሮች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ኅዳር 4 ቀን 1938 ዓ.ም. ማፅደቂያውን ሰነድ አስገብታለች፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እነሆ ከመጀመሪያው የመንግሥታቱ ድርጅት (1946 እስከ 1947) በእኛ 1939 ዓ.ም. አንስቶ አንደኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ተብሎ በተቆጠረው አሁን ሰባ ስምንተኛው ላይ በደረሰው ጉባዔ አባልም ተካፋይም ሆና ዘልቃለች፡፡ ‹‹የዓለም ማኅበር … ለዘለዓለም ይኑር ለሰላም ለፍቅር››ን ትምህርት ቤትና ትምህርት ውስጥ ያስገባው ግን ከዚህ በላይ ያለ፣ ድርጅቱ ከመቋቋሙ በፊት፣ እንዲያውም ለድርጀቱ መቋቋም ዋነኛ ምክንያት የሆነውና ኢትዮጵያ ላይ የደረሰባት እንቢ ለሕግ ያለ፣ ዕድሜ ለጉልበት፣ ለጥጋብ፣ ለዕብሪት ብሎ ሰላምና ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ራሷን ለማጥፋት የተነሳ የጉልበተኛ ጥቃት ሰለባ በመሆኗ ጭምር ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጄኔቭ በዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ፊት ሰኔ 30 ቀን 1928 ዓ.ም. ስለኢትዮጵያ ያደረጉት ንግግር፣ ያቀረቡት አቤቱታና የጠየቁት ዳኝነት ይዘት ራሱ፣ እንዲሁም የዚህ ንግግር ታሪክ ነው፡፡
ዛሬ ሰባ ስምንተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በሚካሄድበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የጠቅላላ ጉባዔው መደበኛ ስብሰባ አንድ ብሎ መቆጠር ከጀመረበት ከ1946 (1939 ዓ.ም.) ጀምሮ ኢትዮጵያ ተካፋይ ሆና ኖራለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዘለዓለም ይኑር ለሰላም ለፍቅር ማለት ዛሬም ራሱ ተመድ በሚሰይማቸው፣ ተከብረው አክብረው እንዲውሉ/እንዲባጁ ጭምር በሚያደርጋቸው ቀኖች፣ ሳምንታትና ዓመታት አማካይነት ቢጣርም፣ ቢተጋም፣ ዓለም በሥልጣኔ ቢመነደግም ዓለም አሁንም የጡንቸኛዎች፣ የጉልበተኞች፣ የአፄ በጉልበቴዎች፣ የግፈኞች፣ የገፋፊዎች ዓለም መሆኑን ይልቁንም አባብሶና በአሳሳቢ ደረጃ ቀጥሎበታል፡፡
ባለፉት 500 ዓመታት ከሞላ ጎደል የመንግሥታትን ግንኙነት ሲገዛ የነበረው፣ ኢትዮጵያም በተወረረችበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥቷ የተማጠኑት፣ በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ከመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር ወዲህ የተቋቋመው ወይም የነገሠው ዓለም አቀፋዊ ሕግ (ኢንተርናሽናል ሎው) በራሱ አቅምና ማዕቀፍ ውስጥ ሳይቀር አስገዳጅነት የሌለው የቢሻኝ ውሳኔና ምርጫ ሆኗል፡፡ በተለይ፣ በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ወዲህ ዓለም አቀፋዊ ሕግን እንኳንስ ሌላው ዓለም፣ ሌላው አገር፣ እንኳንስ ‹‹አጨብጫቢው›› የአውሮፓ ኅብረት አሜሪካ ራሷ አፍታትታ የማታብራራው ልዩነቱም ይህ ነው የማትለው፣ ነገር ግን በጉልበተኝነትና ‹‹በማን አባቱ ይናገረኛል›› መንፈስና ስሜት ያወጣችውና አዲስ ያወጣችው ‹‹Rules Based Order›› የሚባል ‹‹ሕግ›› እና ‹‹ሥርዓት›› ዓለም አቀፋዊ ሕግን ገልብጦ፣ ሽሮና ተክቶ በሚንፈላሰስበትና ሌላውን ዓለም በሚያብጥበት ዓለም ውስጥ እንገኛለን፡፡
ድሮም ቢሆን ተመድ (የመንግሥታቱ ድርጅት) የሚሠራው፣ መሥራት የሚችለውና የሚላወሰው ትልልቅና ጉልበተኛ አገሮችና ኃይሎች ከሁሉም በላይና በመጀመርያ ደረጃ ደግሞ አሜሪካ በፈቀደችለትና ይሁን ባለችው መጠን ነው፡፡ የተመድ ሥራና ክንዋኔ ሁሉ የሚከናወነው በዚህ የታላላቅ መንግሥታት፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካ (የውጭ) ፖሊሲና ጥቅም በሚፈቅደው ማዕቀፍ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በዚህ የተመድ ውስንና የተገደበ አጥር ግቢ ውስጥም ቢሆን ተቋሙ ማንም ክፍለ ዓለም ወይም አገር ብቻውን ከሚያደርገው በላይ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ማከናወን የቻለ ድርጅት ነው፡፡ በተመድ ጥላ ሥር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፣ ጥቅም ላይ ባይውሉም ወይም ተፈጻሚነት ባያገኙም በርካታ መሣሪያዎች ተፈጥረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የሚደረገው ነገም፣ ከነገ ወዲያም ተመድ መላወስና መንቀሳቀስ የሚችለው ጉልበተኞቹ ስለፈቀዱለት፣ የሚፈቅዱለትም ከጥቅማቸው ጋር የሚገናዘብ አጋጣሚ ‹‹በል›› ሲላቸው እንጂ የሕግ አስገዳጅነት ኖሮ አይደለም፡፡ ዛሬ ደግሞ አሁን አሁን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ወዲህ ደግሞ ‹‹ደንቦች ላይ የተመሠረተ ሥርዓት›› ወይም ‹‹Rules Based Order›› የሚባለው የአሜሪካ የብቻ ‹‹መጫወቻ›› ዓለም አቀፋዊ ሕግን የተካበት፣ በሕግ አምላክ እንኳን ተብሎ የማይማፀኑበት፣ ከዚህም የተነሳ በጉልበታችሁ አምላክ የሕግ አምላክን ተክቶ የተዘባነነበትና የነገሠበት ጊዜ ውስጥ ደርሰናል፡፡
አሜሪካ ለምን ይህን ታደርጋለች? ‹‹ለዘለዓለም ይኑር ለሰላም ለፍቅር›› እያልን የምንለምንለትን፣ የምንለማመነውን ማኅበራችንንና ሰላምንና ደኅንነትን ጭምር አሜሪካ ለምን ታምሳለች? በምንስ ምክንያት አሜሪካ ኢንተናሽናል ሕግን ‹‹ደንቦች ላይ የተመሠረተ ሥርዓት›› (Rules Based order) በሚባል ነገር ማፍረስ ትፈልጋለች? በአቅማችንም ቢሆን መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 6 (2) ‹‹Supremacy of the National Government›› በሚባለው ድንጋጌው በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ፣ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት የሚወጡ ሕጎችና መንግሥት በሕግ መሠረት የሚገባቸው ውሎች የአገር የበላይ ሕጎች ናቸው በማለት፣ ለእነዚህ የበላይ ሕጎች ዜጎችም፣ ዳኞችም ተገዥ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ እግረ መንገዳችንንም የ1948ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 122 ይህ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ተካፋይ ከምትሆንባቸው ከኢንተርሲዮናል ውሎች፣ ከዓለም ስምምነቶችና ግዴታዎች ጋር በአንድነት ሆኖ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የበላይ ሕግ ይሆናል፡፡ ወደፊትም የሚሠሩ ሕጎች፣ ድንጋጌዎች፣ ፍርዶች፣ ውሳኔዎች ሁሉ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የማይስማሙ ሲሆኑ፣ ዋጋ የሌላቸውና የማያገለግሉ ይሆናሉ ብሎ እንደሚደነግግ እናስታወስ፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 9 የሕገ መንግሥት የበላይነት (በእንግሊዝኛ ደግሞ Supremacy of the Constitution) በሚለው ድንጋጌው የሚከተለውን ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 9 1) ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ 2) ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎችም ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ 3) በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኃን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡ 4) ኢትዮጵያ የፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 (የመሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶች የተደነገጉበትንና የተዘረዘሩበትን የሕገ መንግሥቱን ምዕራፍ ሦስት ሲያስተዋውቅ፣ ሲከፍትና በተለይም ተፈጻሚነትና አተረጓጎማቸውን ሲደነግግ) የሚከተለውን ይወስናል፡፡
አንቀጽ 13 1) በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ 2) በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩ መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች፣ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ፡፡
ከፍ ሲል አንድ ጥያቄ አቅርቤ፣ በተለይም ለምን አሜሪካ ኢንተርናሽናል ሕግን ‹‹Rules Based Order›› በሚባል ነገር መተካትና መሻር የዓለም ማኅበርንም ማመስ ትፈልጋለች ብዬ ጠይቄ፣ እግረ መንገዴንም ብዬ፣ በአሜሪካ ሕግ ውስጥ የዓለም አቀፍ ስምምነትን ቦት አሳይቻለሁ፡፡ ወዲያውም በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ የዓለም አቀፍ ሕግ ያለውን ቦታ፣ በመጠኑም ቢሆን ታሪክ ጭምር አመላክቻለሁ፡፡ በዚህ አማካይነት ያነሳነውን ጥያቄ ወደ መመለስ ከባድና ነገር ግን ተገቢ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ይህንን ስል መልሱ የእኔ ነው ያልኩ እንዳይመስልብኝ ግልጽ የማድረግ ግዴታ አለብኝ፡፡ በጭራሽ፡፡ ዓለምን ከሌሎች መካከል አደጋ ላይ የጣለው የዩኤስ አሜሪካ በተለይም ከ1991 (ድኅረ ቀዝቃዛ ጦርነት) ወዲህ ማናለብኝነት፣ ማን አባቱ ያዘኛል ባይነት የፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ሕግን ትርጉሙ ባልተነገረና ቅጡ ባልታወቀ ‹‹Rules Based Order›› የመተካትና የመሻር ሸር በተቃራኒው አምጦ የወለደው ንቅናቄ የዚህን መልስ ማፈላለጉ አንዱ አነስተኛው ወይም መነሻው የትግሉ አካል ነው፡፡ ይህን በመሰለ ጥናት ውስጥ አሜሪካ ብቻዋንም ሆነ ከሌሎች ጋር ሆና ዓለም አቀፋዊ ሕግን አሽቀንጥራ ጥላ በዚህ በተጠቀሰው ‹‹ደንቦች ላይ የተመሠረተ ሥርዓት›› መተካት የምትፈልግበት ምክንያቶች አላት፡፡
አንድ ሁለት ብለን በአጭሩ እንመልከታቸው፡፡ አንደኛና መጀመርያ ነገር አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ ሕግ የሚባለውን ነገር የሚያቋቁሙት የዋና ዋናዎቹ ብዙ ስምምነቶች አካል አይደለችም፡፡ ለምሳሌ ኢንተርናሽናል ‹‹ሒውማኒቴሪያል ሎው›› ወይም የጦርነት ሕግ ወይም የቀይ መስቀል ሕግ የሚለውን ሕግ ከሚያቋቁሙት ውስጥ ብዙዎቹን መሠረታዊዎቹን የ1977 ዓ.ም. የጄኔቫ ኮንቬንሽን ፕሮቶኮል የሚባለውን ጭምር ፈራሚ አይደለችም፡፡ የሮም ሕገ ደንብ (ወይም የዓለም አቀፋዊው የወንጀል ፍርድ ቤት) ፈራሚ አይደለችም፡፡ የክላስተር ኮንቬንሽን የሚባለውን አልፈረመችም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን የሚባል ከሴፕቴምበር 1991 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለም በሙሉ ያፀደቀው ኢንተርናሽናል ሕግ አለ፡፡ መላው ዓለም በሙሉ ያፀደቀውን፣ የገዛ ራሱ ሕግ ያደረገውን ስምምነት ያልፈረሙበትና ያላፀደቁት ሁለት አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ ዩኤስ አሜሪካና ሶማሊያ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ሳውዝ ቻይና ሲ (ደቡብ ቻይና ባህር) የሚባል ቦታ ባለ የአጎራባች አገሮች አለመግባባት ውስጥ ገብታ መፈትፈቷ፣ ባለጉዳይም ዳኛም መሆኗ የሚገርመው የ14 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ሳይገድባት ነገር ትፈልጋለች ተብላ ብቻ ሳይሆን ‹‹ሎው ኦፍ ዘ ሲ ኮንቬንሽን›› የሚባለውን ያገባኛል የምትለው ጉዳይ የሚገዛበትን ስምምነት ፈራሚ፣ ገዥም ሳትሆን ነው፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያመላክቱት አሜሪካ ኢንተርናሽናል ሕግ ውስጥ የሚያኮራ በምሳሌት የሚጠራ ባህልና ወግ የላትም፡፡ በዚህ ሕግ አምላክ ብላ የምትማጠነው በዚህ ሕግ ይሁንብኝ የምትለውና የምትምልበት ብዙ የሚያዋጣ ልምድ የላትም፡፡ ስለዚህም ቻይናን ‹‹ቀንደኛ›› ባላንጣዋን ቻይናን አሜሪካ የባህር ሕግን ጠርታ፣ በእሱ ይዤሻለሁ ተከልከይ በሕግ የምትልበት አፍም የላትም፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ሕግ ምትክ ትርጉምም፣ ልክም፣ መልክም፣ ቅጥም የሌለው ‹‹Rules Based Order›› የሚባል ማደናገሪያ ራስን መረን የለቀቀ መላ ተዘየደ፡፡
አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ ሕግ ከማለት ይልቅ፣ እሱን አሸቀንጥራ ጥላ ‹‹Rules Based Order›› ያለህ የምትልበት ሌላም ሁለተኛ ምክንያት አለ፡፡ አሜሪካ ይህ ሕግ አይገዛኝም፣ ማለትም እዚህ ሕግ ውስጥ አልገባም ብላ ከማማረጥ በላይ የአገሪቱ ሕግ አካል አድርጋ የፈረደችውና ያፀደቀችው ስምምነት ጉልበተኛ፣ ተርጓሚና ደርጋሚም እሷውና መሰል ጉልበተኛ ኃያላን አገሮች ናቸው፡፡ ኃይል የመጠቀም መብትና ሥልጣን የተመድ ቻርተር ከሚፈቅደው ውስን ሁኔታዎች ውጪ መረን ለቆ ገደቡን ሰብሮ አሜሪካኖችና ጓዶቻቸው ወይም ተከታይ ቡችሎቻቸው እንደሚሉት እየተደረገም የዓለም ሰላም ሥጋትና አደጋ ሆኗል፡፡ ‹‹ለሰብዓዊነት›› ብሎ ጣልቃ የመግባት፣ እንዲሁም ‹‹The Responsibility to Protect›› የሚባሉ ሰበቦች እነ አሜሪካን እንዳሻቸውና እንደፈቀዳቸው የእነሱ ጥቅም እብሪትና ፍትወት እንደመራቸው እየተተረጎሙ ምን ያህል እንደተፈታተኑ እኛም አገር ውስጥ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ልብ አድርጉልኝ የሚለን ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ እና ‹‹ኢንተርናሽናል ሎው›› ማለት የተቋቋመ ሕግ (አገሮች ወደውና ፈቅደው የገቡት ስምምነት) ማለት ብቻ ሳይሆን ዳኛም አለው ማለት ነው፡፡ አሜሪካ ከዚህ ይልቅ ‹‹በደንቦች ላይ የተመሠረተ ሥርዓት›› የምትለውን እጅና እግር የሌለው ከእሷ በስተቀር ማንም የማያውቀውን የመረጠችው የአገሬ ሰው እንደሚለው ‹‹ዳኛውም ዝንጀሮ ፍርድ ቤቱም ገደል/አሁን የት ላይ ቆሞ ይነገራል በደል›› እንዲል የመንግሥታቱን ድርጅት የእስካሁን ውስን ጠቃሚነትና አገልግሎት ስለዚህም ሥልጣኔን ራሱን በአፍጢሙ ለመድፋት ነው፡፡
ሦስተኛውና ሌላው አሜሪካ ከዓለም አቀፍ ሕግ ይልቅ፣ በአጠቃላይ ከሕግ ይልቅ እንዳሻኝ መራመድ፣ እንዳፈቀደኝ መሆን፣ እብሪት እንዳደረገኝ መረን መውጣት ይሻላል ብላ ‹‹Rules Based Order›› የሚባለው ይበጀኛል የምትልበት ሌላው ምክንያት አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ ሕግን ይጥሳሉ/ይረግጣሉ ብላ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማትጨክንባቸው በጭራሽ የማትጠይቃቸው ለገዛ አገሯ ሕግ እንኳን የማታስገዛቸው እንደ እስራኤል ያሉ ‹‹ልዩ›› እና አምሳያ የሌላቸው አገሮች አሉ፡፡ እስከዛሬ ድረስ በራሱ በመንግሥታቱ ድርጅት ዕድሜ ልክ መፍትሔ ያጣው የእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ከአገራቸው የተገፉት አገራቸው በጦር ወረራ የተያዘባቸው የፍልስጤማውያን ነገር፣ በተረፈችው ቁራጭ መሬት ላይ እንደ አገር የመቋቋም ትንሽዬ ፍትሕ እንኳን ያጡበት የዓለማችን ታላቁ የሰው ልጅ መብት ረገጣ የአሜሪካና የአውሮፓ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአሜሪካ ተጠያቂነት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ እናም በሕግ አምላክ ማለት አሜሪካንም በሕግ አምላክ ይላል፣ ተከልከል በአዋጅ ብሎ ያወግዛልና ‹‹Rules Based Order›› ማጭበርበሪያ ሆኖ ተገኘ፡፡
እናም ዓለም በዩኤስ አሜሪካ ሩልስ ቤዝድ ሲስተም ብሎ ነገር አልዳኝም ባይ የሆነው፣ ይህንንም እንቢታ በተለያየ አደረጃጀቶች እየተሰባሰበ የሚያሳየው በዚህ ሁሉ ምክንያት ነው፡፡
በዚህ ላይ ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ ሴኔተር ሜነዳይዝን ግብረ አበሮቻቸው ካላቸው ከባለቤታቸውና ከሌሎች ሦስት ሰዎች (ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ) ጋር የሳውዘርን ዲስትሪክት ኦፍ ኒውዮርክ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው የወንጀል ክስ ጎልጉሎ ያወጣውን፣ ዘርግፎ የሚያሳየው ቁም ነገርና ዝርዝር ደካማ አገሮች የጉልበተኛና የኃያል አገር መጫወጫ ብቻ ሳይሆን የተራ ጥጋበኛና የሀብታም ግለሰብ ያሻውን ማድረጊያ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ እንዴት አድርገን ነው የተረፍነው? የሚያሰኝ ነው፡፡
የዩኤስ አሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) ድረ ገጽ መግቢያ ወይም የፊት ለፊት ገጽ ‹‹Leading America’s foreign policy to advance the interests and Security of the American people›› ይላል፡፡
የአሜሪካን ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት ለማራመድ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ መምራት የዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተቀዳሚ ሥራ ነው ማለት ነው፡፡
ተከሳሹ ሴኔተር ተራ ሰው አይደሉም፡፡ ይህን የምለው ሴኔተር ብሎ ተራ ሰው ብሎ ነገር የለም ብዬ ብቻ አይደለም፡፡ የሴኔቱ የውጭ ጉዳዮች/የውጭ ግንኙነቶች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ናቸውና ያ በራሱ የሚያጎናፅፈው ክብርና ሞገስ ከተራ ሴኔተርነት ተርታ የሚያወጣ፣ ከዚያ ውጪ ወደ ላይ የሚተኩስ፣ የትና የት የሚሰቅል ልዩ ጥቅምና ፀጋ መሳይ አገልግሎት የሚያሰጥ ነው፡፡ የክሱን ዝርዝር ሥራዬ ብሎ በዝርዝር ለሚያነብ ሰው (ከፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ በፊት የተከሳሹን እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትና ክብር እያከበረ) ሥልጣን፣ በተለይም ከፍ ያለና ከበድ ያለ ሥልጣን ምን ያህል ትልና ብል ሆኖ እንደሚያነቅዝ፣ አድራጊ አጣሪ እንደሚያደርግ ምሳሌ ሆኖ ያሳያል፡፡ የሚገርመው ክሱ በሚሸፍነው ዘመን ውስጥ ሴኔተሩና ባለቤታቸው ያገኙት በጥሬ ገንዘብ፣ በጠገራ ወርቅ (ጥፍጥፍ ወርቅ) በዓይነት ያገኙት ጥቅም ብቻ አይደለም፡፡ በዚያ ልክ የነቀዙትን ያህል ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች፣ ተራም ቀንደኛም ታጋይ፣ ወኪል ነገረ ፈጅ፣ ወዘተ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ለፕሬዚዳንት ባይደን የኢትዮጵያን ጠላቶች ነገር አደራ ብለው ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያን እንዲያንቅ የተዘጋጀው ኤስ3199 ደራሲ አዘጋጅ እሳቸው ናቸው፡፡
ጉልበተኛም ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ሥርዓቱ ራሱ የወንጀል ክስ የመሠረተበት የሙስና የመንቀስ/የማንቀዝ ተግባር ሊፈጸምበት ዓለም ዓለም አቀፋዊ ሕግን አሽቀንጥሮ ለመጣል፣ ለመገልበጥ ‹‹Rules Based Order›› በሚባል አውሬና ጭራቅ ለመተካት የሚደረገውን ደባና ሴራ የሰው ልጅና የምድራችን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ መዋጋት አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡