Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበኦሊምፒክ   ተሳትፎ  ኖሮት  በመሠረተ  ልማት  እየተፈተነ  ያለው  የውኃ ስፖርት

በኦሊምፒክ   ተሳትፎ  ኖሮት  በመሠረተ  ልማት  እየተፈተነ  ያለው  የውኃ ስፖርት

ቀን:

በኦሊምፒክ ጨዋታ ከሚከናወኑ መካከል የውኃ ስፖርት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ በሐይቅ የታደሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ስፖርቱን ለመዝናኛነት እየተጠቀሙና ክህሎታቸውን እያሳደጉ በተለያዩ ውድድሮች ሲካፈሉ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ቢሾፍቱና ኮምቦልቻ የዋና ስፖርተኞችን በማብቃት ይታወቃሉ፡፡

በኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ተቋቁሞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከአራት አሠርታት በላይ ቢያስቆጥርም በመሠረተ ልማት ዕጦት እየተፈተነ በአኅጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሁም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በተደረጉ የሪዮና ቶኪዮ ኦሊምፒኮች እንዲሁም ዘንድሮ በፈረንሣይ ፓሪስ በሚከናወነው ኦሊምፒክ ተሳታፊነቷን ቀጥላለች፡፡

ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ስፖርቱን ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶቹን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠረት ደምሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቷ አስተያየት ከሆነ ፌዴሬሽኑ የውኃ ስፖርቱን ለማሳደግ፣ ለማስፋፋት እንዲሁም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡

በዚህም መሠረት አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ከተረከበ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በየክልሉ ባሉ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ሥልጠናዎችን  በመስጠት፣  የልምምድ ቁሳቁሳቁሶችን በማቅረብ ለክልሎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ለአኅጉርና ዓለም አቀፍ የውኃ ስፖርቶች ውድድር ከክልሎች ጋር በቅርበት በመሥራት ብሔራዊ ውድድሮችን በግዮን ሆቴል እያዘጋጀ መቆየቱን ፕሬዚዳንቷ ያስረዳሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ የታዳጊዎችን ጨምሮ ሦስት ብሔራዊ ውድድሮች በግዮን ሆቴል ማከናወን የቻለ ሲሆን፣ ስፖርተኞችን በመለየትም በዓለም አቀፍ መድረኮች ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ አንዱ የተሳተፈችበት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ጋና ባዘጋጀችው የመላ አፍሪካ ውኃ ስፖርት ውድድር  ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ዞን 3 ታንዛኒያ ላይ ታዳጊዎችን ይዛ የቀረበችበት ሌላኛው የአኅጉር ተሳትፎዋ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

እምብዛም በአገር ውስጥ ትኩረት የማይሰጠው የውኃ ስፖርት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ግን ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከዓለም  የውኃ  የስፖርት  ፌዴሬሽን   ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሚገኝና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመካፈል አቅሙን እያሳደገ እንደመጣ ወ/ሮ መሠረት ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሀንጋሪ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ በአውስትራሊያና በጃፓን መካፈል ችላለች፡፡ በተለይ በሀንጋሪና በጃፓን በተደረጉ የማጣሪያ ውድድሮች አትሌቶቹ ባገኙት ውጤት መሠረት በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹የአኅጉርና ዓለም አቀፍ ተሳትፏችን እያደገ መጥቷል፡፡ ውጤቱ አመርቂ ባይሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ልጆቻችንን ውጤታቸውን እያሻሻሉ መጥተዋል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የውኃ ስፖርቶች ለኢትዮጵያ የሚገባው ዕድል እየሰጠ እንደሚገኝ የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር በመሆኗ በዘርፉ የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተገቢው ስፖርተኛ እንደማይመረጥ ይልቁንም ተገቢ ያልሆኑ ዋናተኞች ያለ አግባብ ዕድል እንደሚሰጣቸው ወቀሳ ይቀርብ ነበር፡፡

በተለይ ከሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከስፖርተኛ  ምርጫ ጋር በተያያዘ ውዝግብ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም እንደ ወ/ሮ መሠረት ማብራሪያ ከሆነ ተገቢ ስፖርተኛ ለመምረጥ ወቅታዊ አቋም ሳይለካ ተሳታፊን አይመረጥም፡፡

  ‹‹ከዚህ ቀደም ተገቢው ስፖርተኛ አይመረጥም የሚል ቅሬታ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ማንኛውም ዋናተኛ ያለው ወቅታዊ አቋም ሳይለካ ተሳታፊ አናደርግም፡፡ ሁሉም ባላቸው ውጤት አንፃር አገራቸውን እንዲወክሉ ይደረጋል፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለመጀመርያ ጊዜ አምስት ዓለም አቀፍ ዳኞችን በውኃ ዋና ማስመዝገብ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ይህም ዓለም አቀፍ የውኃ ፌዴሬሽን የሰጠውን ኮታ በአግባቡ ለመጠቀም ከሌሎች አገሮች እኩል ዓለም አቀፍ ዳኞችን ማብቃት መቻሉ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ባሻገር ፌዴሬሽኑ በሀንጋሪና ታይላንድ ሁለት ልጆች የትምህርት ዕድል (Scholarship) እንዲያገኙ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ውክልና እንዲኖራት ፌዴሬሸኑ ያለውን አቅም አሟጦ እየተጠቀመ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ያስረዳሉ፡፡ በአንፃሩ ግን ፌዴሬሽኑ ከፋይናንስና  ወቅታዊ  አገራዊ ሁኔታ አንፃር ውድድር ማድረግ አለመቻሉ ይወሳል፡፡ የመዋኛ ገንዳ ዕጦት አንዱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ወ/ሮ መሠረት ያስረዳሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን ለማከናወን የሚያስችል የራሱ የመዋኛ ገንዳ ባለመኖሩ፣ ለግዮን ሆቴልና ለቢሾፍቱ እየከፈለ ውድድሮችን ለማድረግ መገደዱን ፕሬዚዳንቷ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

‹‹ስፖርተኞች በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን መወከል ስላለባቸው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የማጣሪያ ውድድሮችን እናከናውናለን፡፡ የፋይናንስ ውስንንትና የማወዳደሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተነ ይገኛል፤›› በማለት ወ/ሮ መሠረት ይገልጻሉ፡፡ የመወዳደሪያ ሥፍራውን ዕጦት ለመቅረፍ የመሬት ጥያቄ ከፌዴሬሽኑ የቀረበ መሆኑን የሚያነሱት ፕሬዚዳንቷ፣ መሬቱ የባለቤትነት ጥያቄ ስለቀረበበት አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አሁንም ጥያቄውን ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አቅርበው በጉዳዩ ላይ እየተመካከሩበት እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

ክለቦችን የማቋቋም ትልም

የውኃ ስፖርት በቅርቡ ግን ክለቦችን ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ወ/ሮ መሠረት ለሪፖርተር ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ መሠረት አንድ ስፖርት ፌዴሬሽን ተብሎ ሊጠራ የሚችለው አምስትና ከዚያ በላይ ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳደሮች ሲኖራቸው እንደሆነ ያስቀምጣል። በተመሳሳይ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፌዴሬሽን የመሆን ሕጋዊ ዕውቅና የሚያገኙት በትንሹ አምስት ክለቦችን ማቋቋም ሲችሉ ነው።

በዚህም መሠረት በፌዴሬሽን ደረጃ የክለብ ምሥረታ ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነት መጀመሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣  መከላከያና አየር ኃይል ክለብ ለማቋቋም ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ጠቁመዋል። ይህም ክለቦች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት ውድድር ተፎካካሪ ዋናተኞችን እንዲፈሩ ይረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...