ከሁለት ሳምንታት በፊት በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ25,000 በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉበት የጋምቤላ ክልል፣ በቀጣይም በጥቅምትና ኅዳር ወራት ላይ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ይከሰታል የሚል ሥጋት መኖሩ ተገለጸ፡፡
በጋምቤላ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አገልግሎት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ ወልዴ፣ ከአሥር ቀን በፊት በጋምቤላ ክልል በዘጠኝ ወረዳዎችና በከተማው ውስጥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ ከ25 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ሲፈናቀሉ፣ ከ36 ሺሕ በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል፡፡
የአየር ትንበያ እንደሚያመላክተው በቀጣይ ጥቅምትና ኅዳር ወር በደጋማ አካባቢዎች ማለትም በኢሉአባቡር፣ ቄለም ወለጋና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ስለሚኖር፣ በክልሉ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት በክልሉ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለተፈናቀሉ 25 ሺሕ ነዋሪዎች ድጋፍ ሊደረግ መሆኑንም ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በግጭትና በጎርፍ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የአንድ ዓመት ዕቅድ በማውጣት ኮሜቴ አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ፣ የኮሚሽኑ ስትራቴጂካዊ ሎጂስቲክስ ዘርፍ የምክትል ኮሚሽነር አማካሪ አቶ አበበ አባቡልጉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ያቋቋመው ኮሚቴ ለአንድ ዓመት በጋምቤላ ክልል የሚቆይ ቋሚ ቡድን የላከ መሆኑን፣ ቡድኑ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በዘላቂነትና የአጭር ጊዜ ድጋፍ በማድረግ ቆይታ እንደሚያደርግ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
የተያዘው ዕቅድ ዋና ዓላማ ማንኛውንም ሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ ለኅብረተሰቡ ማድረስ፣ እንዲሁም ከሰላምና ከልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን ነው ብለዋል፡፡
ኮሚቴው በአንድ ዓመት ውስጥ በክልሉ በተከሰተው የግጭትና የጎርፍ አደጋ ምክንያት ችግር የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ሥራ ማስገባት፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማደረግ፣ በመልሶ ማቋቋም ወደ ዘላቂ ልማት ማስገባት የሚሉ ግቦችን ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል የተናሩት ዳይሬክተሩ፣ የጎርፍ አደጋው በቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ በሰብልና በቁም እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ትልልቅ ወንዞች አቋርጠውት ስለሚያልፉና ሜዳማ ስለሆነ ዝናብ ከመጣ የትም መሄድ ባለመቻሉ፣ እንዲሁም የመሬት አቀማመጡ ዝቅተኛ ስለሆነ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ነው ሲሉ አቶ ሰይፉ አክለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በየዓመቱ ዝናብ ሲኖር የራሱን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ፣ ነዋሪዎች በቤታቸው ዙሪያ አፈር የመሙላትና ቦይ የመቆፈር ተግባር እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ኅብረተሰቡ የወደመበት ንብረት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አበበ፣ የክልሉ፣ የወረዳዎችና የኮሚሽኑ ተወካዮች ከለጋሾች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ድጋፎች እንዲደርሱ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በግጭት ምክንያት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ወደ ልማት ለማስገባት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ጋር በጋራ በመሆን፣ ቤታቸው ለፈረሰባቸው በመጪው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጊዜያዊ መጠለያ ለመሥራት ማቀዱን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል ያለውን ሀብት የአካባቢው ማኅበረሰብ እየተጠቀመበት አለመሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ፣ ኅብረተሰቡን ወደ ልማት በማስገባት በየዓመቱ በጎርፍ ምክንያት የሚከሰተውን ችግር በራሱ እንዲቋቋም የማድረግ ሥራ ይጀመራል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በየጊዜው በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ምክንያት ተጎጂ እንዳይሆን በወንዝ አካባቢ ያደረገውን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር፣ ከወንዝ አካባቢ ራቅ ወዳለ ደረቃማ ቦታ መኖር እንዲለማመድ የተቋቋመው ኮሚቴ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ድጋፉ ወደ ክልሉ መጓጓዝ መጀመሩን አቶ አበበ አስረድተዋል።
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የደረሰውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት፣ ኮሚሽኑ ባቀረበው ጥሪ ከአሥር በላይ ለጋሽ ድርጅቶች ዝግጁነታቸውን ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት የሚጀመረው ሰብዓዊ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እንደሚሆን የገለጹት አቶ አበበ፣ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴ፣ ፉርኖ ዱቄትና ዘይት ለማዳረስ ዕርዳታ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡሞድ ኡመድ፣ አደጋው በንብረት ላይ ጉዳት በማስከተሉ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ሰሞኑን መግለጻቸው ይታወሳል።