- እኔ እምልክ…?
- ውይ… ውይ… በመጀመሪያ እንኳን በሰላም መጣህ፡፡
- እሺ …ምን ልትጠይቂኝ ነበር?
- ይህን ያህል ጊዜ የቆያችሁት ለስብሰባ ነው?
- ስብሰባ ብቻ አይደለም።
- ከስብሰባ ውጪ ምን ነበር?
- በተለያዩ መሪ ሐሳቦች የተዘጋጁ ሥልጠናዎችን ስንወስድ ነበር።
- የምን መሪ ሐሳብ?
- አንደኛው ‹‹ከዕዳ ወደ ምንዳ›› በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ሥልጠና ነበር።
- አንደኛው ስትል፣ ሌላም ሥልጠና ነበር ማለት ነው?
- አዎ።
- ስለምን ነበር ሌላኛው?
- ‹‹ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የኢትዮጵያን ብልፅግናን ማረጋገጥ›› በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ሥልጠና ነበር።
- ይገርማል ሁለት ሥልጠና ነዋ ስትወስዱ የቆያችሁት።
- ኧረ ከሁለት በላይ ነው።
- ሥልጠናው?
- አዎ!
- ሌላው ሥልጠና ስለምን ነበር?
- ‹‹መፍጠርና መፍጠን›› በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ሥልጠና ነበር።
- ወይ ጉድ፡፡
- ሥልጠናዎቹ ሲጠናቀቁ ደግሞ ጉብኝቶችን ማድረግ ጀመርን።
- የምን ጉብኝት?
- ‹‹ሀብት መፍጠርና ማስተዳደር›› በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ጉብኝት ነበር።
- ምንድነው የጎበኛችሁት?
- ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችንና የሌማት ትሩፋት አምራቾችን።
- በፌስታል ይዘህ የመጣኸው ምንድነው?
- ከሌማት ትሩፋት አምራቾች የገዛሁት ነው።
- ምንድነው?
- ጥቅል ጎመን፣ ፓፓዬ፣ አቩካዶ ምናምን ናቸው።
- መሪ ሐሳብ አለው?
- ምኑ?
- የገዛኸው፡፡
- የምን መሪ ሐሳብ?
- ‹‹ከሌማት ቱሩፋት ለሚኒስትር እራት›› የሚል መሪ ሐሳብ።
[ክቡር ሚኒስትሩ ለመሥሪያ ቤታቸው ተጠሪ ለሆነው የአየር ትንበያ ኃላፊ ጋር ደውለው እየተቆጡ ነው]
- ከሁለት ሳምንት በፊት በሚቀጥሉት ቀናት ደረቃማ የየአር ሁኔታ እንደሚኖር ተንብያችሁ ነበር። አይደለም?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ይህ ትንበያ ሳምንት ሳይሞላው፣ በሚቀጥሉት ቀናት ዝናባማ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንዴት ትላላችሁ!
- ምን ማድረግ እንችላለን ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት? ምን ማለት ነው?
- እያየነው ማለቴ ነው።
- ምኑን ያያችሁት?
- ሲዘንብ።
- የተሰጣችሁ ኃላፊነት የመጪዎቹን ቀናት እንድትተነብዩ አይደለም እንዴ?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ታዲያ ምንድን ነው ችግራችሁ?
- ያው ያለንበት ሁኔታ የሚታወቅ ነው። ኃላፊነታችንን እንዳንወጣ የሚያደናቅፉ ብዙ ችግሮች አሉ።
- አስፈላጊው የትንበያ መሳሪያ ተሟልቶላችኋል፣ ምንድነው ችግራችሁ?
- በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የፈጠረው ተግዳሮት አንዱ ነው።
- ግጭቶቹ በእግረኛ የሚካሄዱ አይደሉም እንዴ?
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት? እናንተ የሰማዩን አይደለም እንዴ የምትተነብዩት?
- በዚያም ቢሆን ችግር አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ችግር?
- ጥርት ያለ ትንበያ እንዳናገኝ እየጋረደን ነው።
- ምኑ?
- የመንግሥት ደመና!
- መቼም አደናቀፈኝ ለማለት ምክንያት አታጡም።
- እንደዚያ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- ነው እንጂ! ቆይ ግን ፖለቲካ ተንብዩ ብትባሉ ምን ሊውጣችሁ ነበር?
- እሱማ ቢሆን ቀላል ነበር ክቡር ሚኒስትር።
- ቀላል ነበር?
- አዎ፣ ይሻለን ነበር።
- እንዴት?
- የምንተነብየው ፖለቲካ ቢሆን?
- እ…?
- ያው ይበዛዋል ማለት ብቻ ነበራ ሥራችን።
- ይበዛዋል?
- አዎ!
- ምን?
- ነፃ አውጪ!