እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች የመንግሥት ጦርን አስለቅቀው የጎንደር ከተማን መቆጣጠራቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች መሠራጨት ጀመሩ፡፡ የፋኖ ኃይሎች ጎንደርን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረዋል የሚለውን ጉዳይ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም፣ በጎንደር ከተማና በአካባቢው ከበድ ያለ ግጭት መካሄዱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጭምር ዘግበውት ነበር፡፡
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ‹‹የፅንፈኛ ኃይሎች ሰርጎ ገብ ጥቃት›› በጎንደር ዙሪያ እንደነበር ጠቅሰው፣ በወገን ጦር በተሰጠው የአፀፋ ምላሽ ተመቶ ወደኋላ መፈርጠጡን ገልጸው ነበር፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪ ግን የፋኖ ኃይሎች በአካባቢው ወታደራዊ ዘመቻ እንጂ ወረራ እንዳላደረጉ ነው የተናገሩት፡፡ እነዚሁ የጎንደር አካባቢ ምንጮች ፋኖ ጥቃቱን ፈጽሞ በራሱ ጊዜ አፈገፈገ እንጂ አካባቢውን ተቆጣጥሮ የመቆየት ሁኔታ አለመፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ግጭት በውል ቁጥራቸውን መግለጽ የማይቻል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ስላለው ሁኔታ የተጠየቁት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ መደበኛ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ አለመመለሱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፋብሪካ ምርቶችም ሆነ የዕለት ፍጆታ የሚሆኑ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ ተወዷል፡፡ ኅብረተሰቡ በኑሮ ውድነትና በዋጋ አለመረጋጋት እጅግ እየተፈተነ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የትራንስፖርትና መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴም በቅጡ አለመመለሱን ነው አቶ ሙሉዓለም የተናገሩት፡፡ አሁን ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ ይልቅ ግን የሚመጣው ፈታኝ ቀውስ እንደሚያሳስባቸው ነው የገለጹት፡፡ ‹‹እንደሚታወቀው የአማራ ክልል በማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የተነሳ በቅጡ ለመዝራት ተቸግሮ የቆየ ክልል ነው፡፡ ግጭቱ በክረምት ወቅት በመባባሱ የተዘራውን ማሳም በቅጡ ለማረምና ለመኮትኮት አርሶ አደሩ ተቸግሯል፡፡ አሁን ደግሞ የመኸር ምርት መሰብሰቢያ ወቅት ደርሷል፡፡ የተዘራችውንና ፍሬ ያፈራችውን ምርት በቅጡ መሰብሰብ ካልቻለች ክልሉ ለከፍተኛ ችግር ነው የሚዳረገው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል እንደ አገር ትርፍ አምራች አካባቢ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሙሉዓለም፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ መደፍረስ አገራዊ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ነው ግምታቸውን የተናገሩት፡፡
በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እየሆነ ስላለው ሁኔታ መረጃ ይደርሳቸው እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሙሉዓለም፣ ስልክና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በመቆራረጣቸው መረጃ በቀላሉ እንደማይገኝ አስረድተዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን ከሰሞኑ በፍኖተ ሰላም ከተማ በደረሰው ግጭት ሳቢያ የከተማው ሆስፒታል አገልግሎት ለማቋረጥ መገደዱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሆስፒታሉ ዶክተሮች የፋኖ ኃይሎችን ታክማላችሁ በሚል ክስ ሆስፒታሉ በመንግሥት ኃይሎች አገልግሎት እንዲያቆም መደረጉን አውቃለሁ፤›› ሲሉም አገልግሎት ያቆመበትን መነሻ ያሉትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡
የፍኖተ ሰላም ከተማ ሆስፒታልን በሚመለከት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ መረጃዎች እየተሰሙ ነው፡፡ በአማራ ክልል ጉዳዮች የሚዘግቡ ብዙ ተከታይ ያላቸው የማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ሆስፒታሉ አገልግሎት ያቆመው፣ በመንግሥት ኃይሎች ጥቃት ነው የሚል መረጃ በማሠራጨት ላይ ናቸው፡፡
ስለዚሁ ሆስፒታል ጉዳይ ሪፖርተር ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፣ በአካባቢው የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ሁኔታውን ለማጣራት ፈታኝ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በጎጃም አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ስላለው ሁኔታ ለማወቅ በተመሳሳይ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ አልተቻለም፡፡
ሰሜን ሜጫ፣ ደንበጫ፣ ቡሬ፣ አዴት፣ ማንኩሳ፣ ፍኖተ ሰላምና ሌሎች ከተሞች የስልክና የመብራት አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል በሚባል ደረጃ መቋረጡ ታውቋል፡፡ ቋሪት፣ ደጋ ዳሞት፣ ጅጋ፣ ቲሊሊ በመሳሰሉ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ታውቋል፡፡ ጯሂት፣ ደንቢያ፣ ማክሰኚት፣ ሉማሜ፣ መሀል ሜዳና ጥቂት በማይባሉ የክልሉ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
የአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከዘመን መለወጫ በዓል መቀበያ ሰሞን ጀምሮ ከባድ ግጭቶች መከሰታቸውና ይኼው ሁኔታ በብዙ ቦታዎች መቀጠሉም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከባድ ግጭት ከተካሄደባቸው አንዱ በሆነው ሰሜን ሸዋ ራሳ አካባቢ መረጋጋት መታየቱና መከላከያም አካባቢውን ለቆ መውጣቱ ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ከዘመን መለወጫ በዓል ማግሥት ጀምሮ በከባድ ግጭት ውስጥ ባሳለፈችው ደብረ ማርቆስ ከተማ ላለፉት አራት ቀናት ግጭት መቆሙን የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ የስልክ አገልግሎት አልፎ አልፎ በባለገመድ ስልክ ካልሆነ አይገኝም፡፡
በከተማው የተኩስ ልውውጥ መቆሙ ቢነገርም መደበኛ እንቅስቃሴ ግን ገና በተሟላ ሁኔታ አልተጀመረም፡፡ በገመድ ስልክ ቤተሰቦቻቸውን ከማግኘት በዘለለ በአካባቢው የሚኖሩ የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚችሉበት ሌላ አማራጭ አለመኖሩን፣ ስለሁኔታው አስተያየት የሰጡ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በጎጃም፣ በጎንደርና በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ካለው የግጭት ድባብ ከዋጠውና መሠረታዊ አገልግሎቶች ከተቋረጡበት ሰሞነኛ ሁኔታ አንፃር፣ በብዙ የወሎ አካባቢዎች በአንፃራዊ የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን ሪፖርተር በወልዲያ፣ በመርሳና በሸዋሮቢት አካባቢዎች ባደረጋቸው ማጣራቶች ለማወቅ ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ በተለይም በአማራ ክልል ስላለው ግጭትና ቀውስ ሥጋታቸውን እየገለጹ ያሉ ወገኖች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከክልሉ ነዋሪዎች ከሚሰማው አቤቱታ በዘለለ ሁኔታው በግጭት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲሰጠው የሚማፀኑ ድምፆች በርካታ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከእነዚህ ወገኖች አንዱ ሲሆን፣ ከነሐሴ መገባደጃ ጀምሮ እስካሁን ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡
ከነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮና ከዚያም ቀደም ብሎ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ስለመጎዳታቸው በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ፣ ‹‹የሁለቱ ወኖች ግጭት ያለ ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፤›› ሲል ማሳሰቡም ይታወሳል፡፡
የመስከረም ወር ከገባ በኋላም ቢሆን ተከታታይ መግለጫዎችን መስጠት የቀጠለው ኢሰመኮ፣ ‹‹ከትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል አሳሳቢነታቸው የቀጠለ የሰብዓዊ መብቶች›› በሚል መሪ ቃል፣ በቅርቡ የአማራ ክልል ቀውስን በሰፊው የተመለከተ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በበኩሉ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማና በአማራ ክልል በንፁኃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሊቆሙ ይገባል፤›› የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኢሰመጉ በአማራ ክልል ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሳሳቢ ናቸው ስለሚላቸው ችግሮች በተደጋጋሚ ሪፖርቶቹ ሲያወጣ ቆይቷል፡፡ በነሐሴ መጀመርያ፣ ‹‹በአማራ ክልል በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ያለው ውጥረት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተደረገ ጥሪ›› በማለት ሪፖርት ያወጣው ኢሰመጉ፣ ‹‹የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ›› በሚል ርዕስ ደግሞ መስከረም መግቢያ ላይ ተመሳሳይ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ውትወታ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
እነዚህ ሁሉ የሰላም ጥሪዎችና የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳዩ መረጃዎች እየቀረቡ ባሉበት ግን፣ በአማራ ክልል እየተፋለሙ ካሉ ኃይሎች በኩል በሰላማዊ አማራጭ ችግሩን ለመቋጨት ያስችላል የሚል ፍንጭ ሲሰጥ አይደመጥም፡፡
ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ በአብዛኛው መዋቅሩ መፍረሱ ከሚነገረው የአማራ ክልል አስተዳደር በኩል ‹‹ፅንፈኛውን የፋኖ ኃይል አባረህ በለው›› ዓይነት ጠንካራ መግለጫ ሲሰጥ ነው በተደጋጋሚ የሚደመጠው፡፡
ከፋኖ ኃይሎችና ከደጋፊዎቻቸው ወገንም ቢሆን ‹‹አራት ኪሎ እንገባለን›› የሚል መፈክርን ጨምሮ፣ መከላከያውንና የመንግሥት ወገንን ሽንፈት የሚያጎሉ መረጃዎች ናቸው በተደጋጋሚ የሚደመጡት፡፡ ኢትዮጵያ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረም ለሰሜኑ ጦርነት መቋጫ አገኘች ከተባለ ገና አሥር ወራት ሊሆኑ ነው፡፡ አገሪቱ በብዙዎች እምነት በ21ኛው ክፍል ዘመን ደም አፋሳሽ ከሚባሉ ግጭቶች አንዱ የሆነውን የሰሜኑን ጦርነት በመቋጨት ወደ ሰላም መጣች ሲባል፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ጦርነት መቀስቀሱ ከአገሪቱ አልፎ ለቀጣናው የሚተርፍ ቀውስ እንደሚፈጥር የብዙዎች ሥጋት እየሆነ ነው፡፡ ይህ ሥጋት ደግሞ ከአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አልፎ በዓለም አቀፍ መድረኮችም በሰፊው እየተስተጋባ ነው፡፡
ከሰሞኑ በተጠራውና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያን የተመለከተ ሪፖርት ያደመጠው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ ቀውስ ብሎታል፡፡
በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የእንቅስቃሴና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች መቋረጥ ደግሞ ስለጉዳዩ የጠራ መረጃ ለማግኘት የሚገድብ በመሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ነው በዚሁ ስብሰባ ላይ ተደጋግሞ የተደመጠው፡፡
የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሰብሳቢ መሐመድ ቻንድ ኦስማን ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፣ በአማራ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ሲሉ ጠርተውታል፡፡ በትንሹ አንድ ጊዜ የድሮን ጥቃት የመንግሥት ኃይል መፈጸሙ እንደተረጋገጠ የገለጹት ሰብሳቢው፣ በክልሉ እየተካሄደ ያለውና ሲቪሎችን ሰለባ ማድረግ የቀጠለው በከባድ መሣሪያዎች ጭምር የታገዘው ጦርነት አገሪቱን ለከባድ አደጋ እንዳጋለጠ ተናግረዋል፡፡
በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ አገሮች ተወካዮች በምክር ቤቱ አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና መረጃ እንዳይወጣም በማፈን ጭምር በአማራ ክልል ለንፁኃን በቂ ጥበቃ ያላደረገ ዘመቻ መክፈቱን ተቃውመዋል፡፡ መንግሥት በሕግ ማስከበር ዘመቻ ሕገወጦችን በመከላከልና ትጥቅ በማስፈታት ስም በገለልተኛ ወገን ክትትል ሊካሄድበት በማይችል ሁኔታ በአማራ ክልል የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች፣ አገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ እንዳይከታት የብዙ አገሮች ተወካዮች ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡
በተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ተገኝተው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ያንፀባረቁ ተወካዮች ግን ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡ መንግሥት በአማራ ክልል እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ሕግ የተከተለ ስለመሆኑ ተከራክረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚከታተል ቦርድ በፓርላማው መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ኦፕሬሽን በገለልተኛ አጣሪ ቦርድ ክትትል የሚደረግበትና ሕግን የተከተለ ሥርዓት የማስፈን ዘመቻ መሆኑን ለማሳመን ጥረት አድርገዋል፡፡
በአማራ ክልል ጉዳይ በመንግሥትም ሆነ በተፋላሚ ኃይሎች ወገን የሚሰማው መረጃ ፍፁም የሚቃረን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ አገር አቀፍ ቀውስ ወደ መሆን መሸጋገሩ የሚቀር አይመስልም የሚለው ሥጋት ግን የብዙዎች ነው፡፡