Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ1498ኛው የመውሊድ ክብረ በዓል

1498ኛው የመውሊድ ክብረ በዓል

ቀን:

ዛሬ ረቡዕ በዓመተ ሒጅራ አቆጣጠር ረቢ-አል-አወል 12ኛው ቀን (የጨረቃ ጥቅምት 12)፣ በፀሐይ መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ነው፡፡ ዕለቱም በሙስሊሞች ዘንድ የነቢዩ መሐመድ ልደት የሚከበርበት፡፡ ሚላድ አን-ነቢ፣ እንዲሁም ማውሊድ በመባል ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነቢዩ መሐመድ የተወለዱበትን ዕለተ መውሊድን በማክበር ላይ ናቸው። ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የእስልምና አዲስ ዓመት ሙሃረም 1 ቀን 1445 ዓመተ ሒጅራ የገባ ሲሆን፣ አሁን ሦስተኛው ወር ረቢ ዑል-አወል ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ወር በስድስተኛው መቶ ዘመን በ570 ዓ.ም. ነቢዩ የተወለዱበት ስለሆነ መውሊድ በመባል ይታወቃል።

ሚላድ በሦስተኛው የእስልምና ወር ረቢዑል አወል 12 ቀን ላይ የሚውል ሲሆን፣ ምንም እንኳን በትክክለኛ ቀኑ ላይ ልዩነት ቢኖርም (የሺዓ ሙስሊሞች የነቢዩ ልደት በ17ኛው ቀን እንደሆነ ያምናሉ) ነቢዩ መሐመድ በአንድ ወቅት ሰኞን ለምን እንደጾሙ ተጠይቀው፡- ‹‹የተወለድኩበት ቀን እና መገለጡ የተጀመረበት ቀን ነው›› ሲሉ መመለሳቸውን ሊቆቹን ጠቅሶ ብሪንግሃምሜይል በድረ ገጹ ከትቧል፡፡

በኢትዮጵያ ዕለተ በዓሉ በፀሐይ መስከረም 16 ቀን 2016፣ በጨረቃ ‹‹ጥቅምት 12›› መዋሉ ባሕረ ሐሳቡ ያሳያል፡፡

ክብረ በዓሉ በትውፊቱ መሠረት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በተለያዩ መድረኮች በጸሎት፣ የነቢዩን ሕይወት በመተረክ፣ የነቢዩ መሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው በመንዙማ፣ በግጥም፣ በቤተሰብ ስብሰባ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍና ልዩ ልመናዎችን በማቅረብ ይከበርበታል፡፡  

መውሊድ ዓምና ከነበረው በ10 ወይም 11 ቀናት ቀደም ብሎ ይውላል፡፡  ምክንያቱም እስላማዊው ካላንደር ጨረቃን የሚከተል በመሆኑ ለ12 የጨረቃ ዑደቶች የሚቆዩት ለ354 ቀናት ነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው ዓለም ጥቅም ላይ ከሚውለው የ365 ቀናት በፀሐይ ላይ ከተመሠረተው አቆጣጠር ጋር ልዩነት አለው፡፡

የመውሊድ ከበራን በተመለከተ ያተቱት የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡-

‹‹በአገራችን የመውሊድ ከበራን በሦስት ቦታዎችና ጊዜዎች የማክበር ልማድ አለ። ቦታን በሚመለከት መውሊድ በመኖሪያ ቤት፣ በመስጊድና በሱፊ ማዕከሎች ይከበራል። የመውሊዱ ጊዜ ደግሞ ባብዛኛው ነቢዩ በተወለዱበት በረቢየል አወል ወር አሥራ ሁለተኛው ቀን፣ ወይም በተወለዱበት ወር ውስጥ በሚገኝ ሰኞ፣ ወይም በማንኛውም ወር በሚገኝ ሰኞ ቀን፣ ወይም በማንኛውም ወርና ቀን ይከበራል።››

ከማኅበራዊ ግንኙነት አንፃር የመውሊድን ፋይዳ ሲገልጹትም፣ በመውሊድ ከበራ ሰደቃ ይካሄድበታል፡፡ በዚህም ሀብታምና ድሃ ይገናኙበታል፣ ያለው ለሌለው የፈጣሪውን ውደታ ፍለጋ ምጽዋዕት ይሰጥበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማኅበራዊ ግንኙነትና ትስስር ይጠናከርበታል ይላሉ።

መውሊድ እንደ አንድ ኢስላማዊ እሴት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ማንነት ማረጋገጫ፣ አንዱ ሙስሊም ከሌላው ሙስሊም ጋር ያለውን ወንድማማችነት፣ የአመለካከት አንድነት የሚያንፀባርቅበትም እንደሆነ የሚገልጹት፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪና ደራሲ አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ናቸው፡፡ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን በብዙ አገሮች መከበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ራሳቸው ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ጸሎት ያደርሱም እንደነበር አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ የመውሊድ በዓል ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች ውስጥ በወሎ ዳና፣ ገታ ንጉሥ፣ በባሌ ሸኽ ሑሴን ባሌ (አናጀና)፣ በሐረር ከተማ፣ በትግራይ ዓዲጉደም፣ ግጀት፣ ራያ (አና) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹የይቅርታው ነቢይ››

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዘንድሮው የመውሊድ በዓል የሚከበርበት መሪ ቃል ‹‹የይቅርታው ነቢይ›› በሚል እንደሆነ በዋዜማው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዓሉ አምላክን በመማፀንና እስላማዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ሊከበር እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን ባስተላለፉት መልዕክት፣ 1498ኛው የነቢዩ መሐመድ መውሊድ መስከረም 16 ሲከበር፣  ሕዝበ ሙስሊሙ ያለውን በማካፈልና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉ በተለያዩ መርሐ ግብሮች በታላቁ አንዋር መስጊድ እንደሚከበር ያወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር በዓል በመሆኑ ነቢያችን እንደሚሉን በመተሳሰብ እና በመተዛዘን እንዲሁም በመረዳዳት ማክበር ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ የሰው ልጆች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን በማመልከት፡፡

 መልካም ሥራን በመፈጸም፣ የኢትዮጵያ ሰላም እንዲሟላ አስተማማኝ ደኅንነት እንዲሰፍን ሕዝበ ሙስሊሙ ዱአ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

መንዙማ

መንዙማ ከሚተገበርባቸው  በዓላት አንዱ መውሊድ ነው፡፡ መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው፡፡ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶችን ሰንዶ ከያዘው የቅርስ ባለሥልጣን መድበል የመንዙማን ሃይማኖታዊ ይዘት እንደሚከተለው ጠቅሶታል፡፡

‹‹የመንዙማ ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አወሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተዓምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው፡፡›› 

በአብዛኛው የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው ነው ሲልም ያክላል፡፡

የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) በታዛ መጽሔት ጥበብ እንደጻፉት፣ መውሊድን ለሚያከብሩ ሰዎች ነቢዩ መሐመድ ለተወለዱበት ወር የተለየ ክብር አላቸው። ይህ ወር ‹‹ረቢእ›› ተብሎ ይጠራል።  ወሩ የዓለሙ መሪ ነቢዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ መቀበል የጀመሩበት፣ ተልዕኳቸውን አድርሰው፣ ለሕዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ነው። እናም በመንዙማ ወሩን የነቢዩ ሙሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው እንደሚከተለው ይገልጹበታል፡-

ረቢእ ተብለህ የምትጠራ፤

የወራት ጓል ንጉሥ አውራ፣

ነቢ ባለ ሙሉ ሰብእና፣

እውድጥህ ፈለቁና፣

ሀሴት አዝለህ አስደሰትከን ተስፋ ወልደህ አደመከን፣

ቃል አደራህ ለኛ ከብዷል ውለታህ ክፋይን ገዷል።

እንደ ዶ/ር መሐመድ አሊ ማብራሪያ፣ በመውሊድ መንዙማ የነቢዩ መሐመድ አካላዊ ገጽታ እየተነሳ ይታወሱበታል። ለምሳሌ ቀጥሎ በቀረበው የመንዙማ ግጥም የነቢዩን ዓይን፣ ፊት፣ ፀጉር ይገልጻል። ዓይናቸው በኑር (በብርሃን) እንደተኳለ፣ ፊታቸው የጨረቃ ብርሃንን እንደሚያስንቅ፣ ፀጉራቸው የሐር ጉንጉን እንደሚመስል፣ ሥዕላዊ በሆነ ጥበብ ሥሎ ይታያል፡፡

‹‹የመድናውን ባየነው ዓይኑን

በኑር አረንጓዴ የተኳለውን

ፊቱ ከጨረቃ የሚያበራውን

ፀጉሩ የሚመስለው የሀር ጉንጉን

ብሎ ያወደሰው ጦሀው ያስኔ።››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...