በሙዓመር ጋዳፊ ዘመን የኑሮ ሁኔታዋ በከፍተኛ ደረጃ ትጠቀስ የነበረችውና በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ሊቢያ፣ ከሁለት አሠርታት ወዲህ የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ የምስቅልቅል አገር ሆና ዘልቃለች፡፡ የፕሬዚዳንቷ ጋዳፊ መገደልን ተከትሎ ለ13 ዓመታት ሳትረጋጋ ይብሱንም በምሥራቅና ምዕራብ ተከፍላ ኑሮዋን ትገፋለች፡፡ ሕዝቧም መከራውን፣ ፍዳውን እያየ ነው፡፡
በዋና ከተማ ትሪፖሊ መንበሩ በያዘ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ያላት ሊቢያ፣ በምሥራቁ አቅጣጫ ደግሞ ሌላ የጎበዝ አለቃ የአካባቢው ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ተቀምጦባታል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ለአሐዳዊ መንግሥት ሳትበቃ እየባከነች ባለችበት አጋጣሚ በመስከረም ዋዜማ ዴርና በሚባል ከተማ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የ20 ሺሕ ሰዎች መሞታቸው የተለያዩ የዜና ምንጮች እየገለጹ ነው፡፡
ሱናሚን የመሰለው አውሎ ነፋስ የሊቢያን ምሥራቃዊ የባህር ዳርቻ ከተሞችን አውድሟል፡፡ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ዴርና ከተማ ጎዳናዎቿ በቤትና ሕንፃ ፍርስራሾች ተሞልተዋል፡፡ አንዳንድ መንደሮች ህልውናቸውን አጥተዋል፡፡ የአደጋው መንሥኤ ሱናሚን የመሰለው አውሎ ነፋስ የግድቡ ውኃ ጥሶ በመውጣቱና በማጥለቅለቁ ነው፡፡
ድንገት በሚፈጠር ክስተት ግድቡን ጥሶ ውኃው ሊፈስና አደገኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊከሰት እንደሚችል ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ ባለሙያዎች ያስጠነቅቁ ነበር፡፡ ሰሚ ጆሮ አለማግኘታቸውን አንድ ሊቢያዊ ጋዜጠኛ እንደነገረው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የቅርሶች ሁኔታ
ገዳይ የሆነው የጎርፍ መጥለቅለቅ የሊቢያን ጥንታዊ ቅርሶች ለአደጋ አጋልጧቸዋል፡፡ ዘ አርት ኒውስፔፐር እንደዘገበው በታሪካዊ ሕንፃዎችና ቅርሶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማጣራት ምርመራ የተጀመረ ሲሆን፣ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት ለመከላከል የረዥም ጊዜ መፍትሔዎችን ማፈላለግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል፡፡
በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር የደረሰውን ውድመት ማጤን የጀመሩት አርኪዮሎጂስቶች በጥፋቱ አጋጣሚ አዳዲስ ታሪካዊ ቅርሶችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያ በግሪክ ሠፋሪዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ74 ዓመት በተመሠረተችውና በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በተመዘገበችው ቀሬና ከተማ ቢያንስ አንድ የእብነ በረድ ሐውልት በቁፋሮ ተገኝቷል፡፡
ይህም በደቡባዊ አካባቢ ቅድመ ክርስቶስ በ490 ዓመት በተሠራው የድሜጥሮስ ቤተ መቅደስ ነው የተገኘው፡፡ አካባቢው ለጎርፍ አደጋ የተጋለጠ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ከቀሬና በስተምዕራብ 150 ኪሜ ርቀት ላይ በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው ቶሌማይስ፣ የእብነ በረድ ዓምድና ግድግዳዎች በባህር ዳርቻው ተገኝተዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኘውና የሮማውያንና የግሪክ ዘመን ኪነ ቅርፅ/ምስሎችና የሞዛይክ ወለሎችን ጨምሮ ውድ ዕቃዎችን የያዘው የቶለማይስ ሙዚየም በጎርፉ ተጥለቅልቋል፡፡
በግሪኮች ዳግም የተመሠረተችውና ከቶለማይስ በስተምዕራብ 40 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ጥንታዊቷ ታውቺራ ከተማ፣ ታሪካዊውን የባህር ዳርቻውን ግንብ አጥታለች፡፡
የከተማዋ ማዕከል ክፉኛ የተጎዳ ሲሆን፣ ጃሚ ኣል-ዓቲክ ተብሎ የሚጠራው ጥንታዊው የዴርና መስጊድ አመድ ልሷል፡፡ መስጊዱ መጀመርያ የተገነባው በ17ኛው ምዕት ዓመት ሲሆን፣ በ21ኛው ምዕት ዓመት ዳግም ተገንብቷል፡፡
በሰሜናዊ ምሥራቅ ሊቢያ በሚገኘው የቤንጋዚ ዩኒቨርሲቲ፣ የአርኪዮሎጂ (ሥነ ጥንት) ረዳት ፕሮፌሰርና የሊቢያ የጥንት ዘመን አማካሪ የሆኑት አህመድ ኢምራጅ፣ ‹‹መዓት ነው፣ አደጋ ብቻ ነው፣ …ሁሉም ነገር በአሥር ደቂቃ ውስጥ ጠፋ፣ በጣም ያማል፤›› ማለታቸው ዘ አርት ኒውስ ፔፐር ዘግቧል፡፡
አሁን መንገዶቹ እየተከፈቱ ስለሆነ ኤምራጅና ባልደረቦቻቸው የድርጊት መርሐ ግብራቸውን ለማዘጋጀት በሚቀጥለው ሳምንት ዳሰሳ ለመጀመር አቅደዋል፡፡
ምንም እንኳን በቀሬና ያጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ በዴርና የታየውን ውድመት ባያመጣም፣ በቀጣይ ግን የውኃው ሁኔታ ቤተ መቅደሶችን፣ አምፊ ቴአትርንና መቃብሮችን፣ ኪነ ቅርፆችን ሊጎዳ እንደሚችል ባለሙያዎች አሳስቧቸዋል፡፡
በዘመናዊቷ የሼሃት ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የቀሬና ጥንታዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት፣ ውኃን ከሕንፃዎች ለማራቅ የተዘጋጁ መስመሮችን ያቀፈ ነው፡፡ የአውሎ ነፋሱ መጠን ግን ሥርዓቱን አናግቶታል፡፡
‹‹እነዚያ መስመሮች (ቻናሎች) ሙሉ በሙሉ በውኃ የተሞሉ [የተዋጡ] ናቸው፤›› የሚሉት ኤምራጅ፣ በአካባቢው ያሉ ባለሥልጣናት ጉዳቱን ለመጠገንና አካባቢውን ለማድረቅ በትጋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለወትሮው ዩኔስኮ ቦታው ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን አይቶ እ.ኤ.አ. በ2016 የመጥፋት አደጋ ላይ ባሉ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ አስቀምጦታል፡፡
በሌስተር ዩኒቨርሲቲ የሮማውያን አርኪዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑትና ከ40 ዓመት በላይ ከሊቢያ ቅርሶች ጋር በመሥራት ያሳለፉት ዴቪድ ማቲንሊ፣ ለዘአርት ኒውስ ፔፐር እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹በዚህ ጉዳይ ካስቸገረኝ ነገር አንዱ የአውሎ ነፋሱ መጠን ነው፡፡ ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነበር፡፡ በሊቢያ በሕይወቴ በሚቀጥሉት አሠርታት ውስጥ የበለጠ ተደጋጋሚ ሊሆን ይችላል፡፡››
እ.ኤ.አ. በ2011 የሊቢያ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከሥልጣን ሲወገዱ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት፣ የአገሪቱን ምሥራቅና ምዕራብ በፖለቲካ ተከፋፍሎ እያንዳንዳቸው በተለያዩ ሚሊሻዎች እየተደገፉ፣ በሁለት መንግሥታት እንዲመሩ አድርጓል። ከ2011 በፊት አምስት የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎች ያላት ሊቢያ፣ በዓለም አቀፍ ተጓዦች ዘንድ ተወዳጅነት እያሳየች ነበር።
‹‹እነዚያ ቦታዎች አሁንም እዚያ ስላሉ እንደገና አስፈላጊ የመሆን አቅምም አላቸው፤›› ይላሉ ማቲንሊ።
የዕርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በጎርፉ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ውድመት ለመቅረፍ ሲታገሉ ቆይተዋል። ዓለም አቀፉ የቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ ባለፈው ሳምንት በሊቢያ ለሚደረገው ዕርዳታ 11 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የአደጋ ጊዜ ጥሪ ማቅረቡን አስታውቋል።
‹‹ሰብአዊ ቀውሱ አስከፊ ነው። ለዚህ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የጋራ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያስፈልገዋል፤›› ሲሉ በሊቢያ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) ቃል አቀባይ በሽር ኦማር ለአርት ኒውስፔፐር ተናግረዋል።
የተጎዱ አካባቢዎችን ለመርዳት የአደጋ መጠለያ፣ የምግብ ዕርዳታ፣ የመገናኛ መሣሪያዎች፣ የመፈለጊያና የማዳኛ መሣሪያዎች፣ የሕክምና ዕርዳታ፣ ባለአራት ጎማ መኪናዎች፣ የፀሐይ ፓነሎችና ሌሎች የሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ኦማር ተናግረዋል።
‹‹ከአይሲአርሲ እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት አቅም በላይ ስለሆነ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲደረግልን እንጠይቃለን፤›› በማለት ጭምር፡፡