Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ምርቃት በመስቀል ክብረ በዓል

ትኩስ ፅሁፎች

የመስቀል ክብረ በዓልን ከሚገልጹት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ ምርቃት ነው፡፡ ለዓይነት የስድስት ብሔረሰቦች አመራረቅ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነውን እነሆ፡፡

በሀዲያ

ደመራ የሚቀጣጠለው መስከረም 16 ሲሆን፣ መጀመሪያ በዕድሜ ትልቅ የሆኑ በየመንደሩ ያሉ አዛውንቶች ‹‹እንኳን በሰላም አደረሰን እንኳን በሰላም ብርሃን አየን ከጨለማም ወጣን›› እያሉ በመመረቅ ችቦ ይለኩሳሉ፡፡ ከዚያም ወጣቶች እየተጫወቱ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ሲነጋጋ ከብቶች ደመራውን ይዞራሉ፡፡

በወላይታ

ጨዋታው ሲያበቃ ለመስቀል የታረደውን በሬ እየተመገቡ ይመራረቃሉ፡፡ ‹‹እስከ መጨረሻው እንኖራለን የዳሞታ ተራራ እንደኖረ፣ የኮይሻ ተራራ እንደኖረ እኛም እንኖራለን፡፡ አህያ ቀንድ እስኪያወጣ እንኖራለን፡፡ ኮንድቾ (በጣም አጭር እንጨት) ምሰሶ እስከሚሆን እንኖራለን፤›› እያሉ መጪውን ዘመን በተስፋ በመቀበል ይለያያሉ፡፡

በሸከቾ

በበዓሉ ቀን ጧፍ በማብራት በየጓዳው በየእህል ማስቀመጫው ይዞ በመግባት ‹‹መጥፎ ነገር ከቤት ውጣ፣ ሀብት ግባ›› እያሉ ከመረቁ በኋላ ጎረቤት ተጠራርቶና ተሰባስቦ ችቦ ይበራል፡፡ በነጋታው የእርድ ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን ቤተሰብና ጎረቤት በመስቀል ይጠራራል ይገባበዛል፡፡

በየም

በዋዜማው ሌሊት ሊነጋ አቅራቢያ ‹‹የረሀብ ምንቸት ውጣ ጥጋብ ግባ›› በማለት ችቦ ከተለኮሰ በኋላ ወደ ደመራው ቦታ ሁሉም ያመራል፡፡ ደመራው በአዛውንቶች ተመርቆ ይለኮሳል፡፡

በካፍቾ

የደመራ በዓሉም የሚከበረው በባህላዊ እምነት መሪው ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ሰው ችቦ በየቤቱ ለኩሶ በራሱ ቤት ዙሪያ በመዞር ድህነት ውጣ፣ ሀብት ግባ ብሎ መልካም ምኞቱን ከገለጸ በኋላ የተቀጣጠለውን ችቦ የባህላዊ እምነት መሪው ግቢ በተዘጋጀው ደመራ ላይ ወስዶ ይለኩሳል፡፡ በማግስቱ ሠንጋ ይታረድና የደመራው እሳት በነደደበት ቦታ ላይ እሳቱን ለማቀዝቀዝ ሲባል ደም ይፈስበታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ደሙን በእጁ በመንካትና ከአመድ ጋር በመለወስ ግንባሩ ላይ ይቀባል፡፡

      በጎፋ

      ‹‹ማስቃላ ዮ! ዮ!›› እያሉ የተለያዩ የበረከት ሐሳቦችን ይለዋወጣሉ– መስቀል እንኳን መጣህልን እንደማለት ነው፡፡ አስከትለውም እየደጋገሙ፣ እየተቀባበሉ፡-

‹‹ማስቃላ ዮ! ዮ! ዳናው ዳና

አልባ ዙማዳን ዳና

ክንቲ ሻላዳን ዳና

መሪናው ዳና

ሀረይ ካጨ ከሳናዳን

ገላኦ ገል ውራናስ ዳና›› ይላሉ፡፡

ትርጉሙም እነሆ፡- አልባ ዙማ በአካባቢው የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሲሆን፣ እንደሱ እንኖራለን እንደ ማለት ነው፡፡ ክንቲ ሻላ ማለት በአካባቢው የሚገኘው ትልቁ አለት ሲሆን እንደሱ እንኖራለን፣ ለዘለዓለም እንኖራለን ማለት ነው፡፡ አህያ ቀንድ እስከሚያበቅል ድረስ እንኖራለን፡፡ ሁሉም ልጃገረዶች እስኪያገቡ ድረስ እንኖራለን፡፡ እንዲህ እያሉ እርስ በርስ ይሸካከማሉ ይተቃቀፋሉም፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች