በኢትዮጵያ በየዕለቱ የረሃብ፣ የመፈናቀል፣ የጦርነትና የኑሮ ግሽበት በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በሚሰማበት በዚህ ወቅት፣ በጥቂቱም ቢሆን ከመሰል ቁዘማ መለስ የሚያደርግ ዜና መስማት መታደል እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።
ለዚህም ቀን ከለሌት ድምፃቸውን አጥፍተው በሳምንት አንድ ቀን እያረፉ ልምምዳቸውን ሠርተው፣ በዓለም አደባባይ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ ድንቅ አትሌቶች መኖራቸው ከመታደልም በላይ መሆኑ እርግጥ ነው። በእርግጥ በርካታ የዓለም ሚዲያዎች የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድንቅ ብቃት ለመግለጽ ቃላት እስኪያጥራቸው ድረስ ሲዘግቡ ተመልክቶ ደስታን አለመግለጽ ንፉግነት ነው።

እሑድ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን ከተማ በማራቶን ውድድር የተከሰተው ጉዳይ፣ ዛሬም ድረስ በመነጋገሪያነቱ ቀጥሏል። ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ የበርሊን ማራቶን 2:11:53 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን መጨበጥ መቻሏ፣ የምዕራባውያኑን ሚዲያ እንድትቆጣጠር አስችሏታል።
ትዕግሥት በዓምናው የበርሊን ማራቶን 2:15:37 በመግባት ማሽነፍ የቻለች ሲሆን፣ ዘንድሮ ምናልባት ክብሯን ብታስጠብቅ እንጂ አዲስ ክብረ ወሰን ትጨብጣለች ብሎ የገመታት አልነበረም።
እ.ኤ.አ. በ2022 በሳዑዲ ሪያድ በተከናወነ ማራቶን የመጀመሪያ ተሳትፎ 2:34:01 በማጠናቀቅ የራሷን ምርጥ ሰዓት ያመጣችው ትዕግሥት ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። የዓምናው የበርሊን ማራቶን ስታሸንፍ 18 ደቂቃዎችን በማሻሻል ሦስተኛዋ የዓለም የሴቶች የማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆን ችላ ነበር።
በወቅቱም በጊዜው የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወስን 2:14:04 በመግባት መጨበጥ የቻለችውን ኬንያዊቷ ብሪጅ ኮስጊና፣ እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍን (2:15:25) በመከተል በ2:25:37 ሦስተኛዋ አትሌት መሆን ችላ ነበር።
ሆኖም ትዕግሥት በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ክብረ ወስን ከመጨበጧም በላይ፣ የማራቶን ፈር ቀዳጁ አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ1957 ዓ.ም. የገባበትን 2:12:11 የበለጠ ሰዓት ማጠናቀቅ መቻሏ በአብዛኛው ዘንድ አድናቆትን ፈጥሯል። ይህም እንስት አትሌቶች ከወንድ አትሌቶች ጋር ያላቸውን ሰዓት እያጠበቡ መሄዳቸውን ፍንጭ የሰጠ መሆን ችሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ሦስት ኢትዮጵያውያን በማራቶን ዓለም ክብረ ወሰን የያዙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ከስምንት ምርጥ ሰዓት ግማሹን በማስመዝገብ ጥሩ ውክልና አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም ግን የማራቶንን የዓለም ክብረ ወሰን የሰበረች አንዲት ኢትዮጵያዊት አልነበረችም።
በማራቶን ውድድር ላይ አትሌቶች የሚሄዱበት እያንዳንዱ ኪሎ ሜትር ሒሳባዊ ሥሌት ያለው ሲሆን፣ አትሌቶች በሩጫ ወቅት አንዳች እክል ካልገጠማቸው የሚያጠናቅቁበት ሰዓት ይታወቃል። በዚህም መሠረት አብዛኛውን ጊዜ አትሌቶች የመጀመሪያውን ግማሽ ርቀት (21. ኪሎ ሜትር) በፈጣን ሰዓት ካጋመሱ በኋላ፣ ክብረ ወሰን የመስበር ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ ይገመታል።
በአንፃሩ አብዛኛውን ጊዜ ከግማሽ ኪሎ ሜትር በኋላ በተመሳሳይ ፍጥነት የሚሮጡ በጣም ጥቂት አትሌቶች ብቻ መሆናቸው ይነገራል። ከዚህ አንፃር ትዕግሥት በሩጫዋ 10 ኪሎ ሜትሩን 31:45፣ 15 ኪሎ ሜትሩን 47:26፣ እንዲሁም 20 ኪሎ ሜትሩን 1:02:52 ስታጋምሰው ክብረ ወሰን ልትሰብር እንደምትችል ተገመተ።
ሆኖም ግን ከግማሽ ኪሎ ሜትር በኋላ የሚኖራት ፍጥነት ክብረ ወሰኑን በእጇ የማስገባት ዕድል ለመኖሩ ውስንነት ነበረው። በዚህም መሠረት ትዕግሥት 25 ኪሎ ሜትር 1:18:40፣ 30 ኪሎ ሜትር 1:34:12፣ 35 ኪሎ ሜትር 1:49:41፣ እንዲሁም 40 ኪሎ ሜትር 2:05:13 በመሮጥ በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራትን ፍጥነት በሁለተኛውም በማስቀጠሏ ክብረ ወሰኑን መጨብጥ ችላለች።
እንደ ባለሙያዎች ትንተናና አስተያየት መሠረት፣ ሴቶች በማራቶን ከ2:11 በታች ይገባሉ ብሎ ግምት ማስቀመጥ እብደት ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህም ወጥ አቋሟ አድናቆትን አጉርፎላታል።
‹‹የማራቶን ክብረ ወስን የመስበር ፍላጎት ነበረኝ። ግን ከ2:12 በታች አጠናቅቃለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› በማለት ትዕግሥት አስተያየቷን ሰንዝራለች።
የትዕግሥት ፈታኝ የአትሌቲክስ ጉዞ
ትዕግሥት ሩጫዋን በሆለታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጀመሯን ኢትዮ ረነርስ አስነብቧል። እንደ ገጹ መረጃ ከሆነ ትዕግሥት በ100 ሜትርና በ200 ሜትር ወደ አትሌቲክሱ መቀላቀሏን ያስረዳል። በ2001 ዓ.ም. በተካሄደ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ200 ሜትር፣ በ400 ሜትር፣ እንዲሁም በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ወርቅ ማግኘቷን መረጃው ያስቀምጣል። በወቅቱ በነበራት ውጤት ክለቦች ቢፈልጓትም ‹‹እንቢ›› በማለት ወደ ሆለታ መመለሷ ተጠቅሷል።
በሒደት በ2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በድጋሚ በማሸነፍ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብን መቀላቀል ችላለች። ከዚያም እ.ኤ.አ. 2013 በሞርሺየስ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያና 4በ4 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያን ማግኘት ችላለች። በ2014 ዓ.ም. በአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ሞሮኮ ማራካሽ ላይ በ800 ሜትር ተካፍላ አራተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች። በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ውስጥ ተካታ መካፈል ችላ ነበር።
ሆኖም ከሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በኋላ የተረከዝ አካባቢ የእግር ሕመም አጋጥሟት በትራክ ሩጫ በስፓይክ መሮጥ እንደማትችል እንደተነገራት ተገልጿል። በዚህም ምክንያት ፊቷን ወደ ጎዳና ሩጫ አዙራ፣ በ2018 በ10 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም በ2019 ሦስት ውድድር አድርጋ በዓመቱ መጨረሻ በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን ሕመሙ እየተሰማት 68:24 ሮጣ ውድድሩን በከባድ ጉዳት እንዳጠናቀቀች ኢትዮ ረነርስ አስነብቧል።
ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላም ወዲያው እዚያው ስፔን ለሕክምና መወሰዷ የተገለጸ ሲሆን፣ ጉዳቷ የከፋ በመሆኑ መሮጥ እንድታቆም አርድተዋት ነበር። የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ወደ ጣሊያን ያመራችው ትዕግሥት የተለየ ተስፋ ሊሰጧት አልቻሉም። በመጨረሻም በክራንች ወደ አገሯዋ የተመለሰችው ትዕግሥት፣ በአትሌቲክሱ ተስፋ አልቆረጠችም ነበር። በዚህም መሠረት በቤተሰቦቿና አሠልጣኟ ገመዶ ደደፎ ዕርዳታ ወደ ልምምድ ተመለሰች። ትዕግሥት 2020 እና 2021 ውድድር ሳታደርግ ቆይታለች።
ከአራት ወራት በላይ ከክራንች ያልተነጠለችውና በአትሌቲክሱ ለአፍታም እንኳን ተስፋ ያልቆረጠችው ትዕግሥት ከ2021 አጋማሽ በኋላ ወደ ውድድር ተመልሳ፣ በ2022 በሦስት የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ተካፍላ ሁሉንም ማሸነፍ ችላለች። ከዚያም በኋላ በጀርመን በተከናወነ ግማሽ ማራቶን ቀድሞ የነበራትን ምርጥ ሰዓት 67:28 ወደ 67:24 በማሻሻል ማሸነፍ ችላለች።
ከዚህ ስኬት ጀርባ በዓለም በማራቶን አሠልጣኝነት ቀዳሚ ሥፍራ የሚሰጠው ገመዶ ደደፎ ለጎላ አስተዋፅኦው ትልቅ አድናቆት አግኝቷል።
ትዕግሥት የሮጠችበት የመጀመሪያ የአዲዳስ ጫማ ምርት
ካለፉት ዓመታት ወዲህ አትሌቶች በጎዳና ሩጫ ክብረ ወሰን ሲሰብሩ፣ የዓለም አቀፍ ጫማ አማራጭ ኩባንያዎች ስም አብሮ ይነሳል። የአትሌቶች ውጤትም የጫማው አስተዋጽኦ ተደርጎ ይወሰዳል። አለፍ ሲልም ውጤቱ ወደ ዶፒንግ ይወስዳል። ትዕግሥት በበርሊን ላይ የተጫማችው የመሮጫ ጫማ አዲዜሮ አዲዮስ ፕሮ ኢቮ ዋን (Adizero Adios Pro Evo 1) ሲሰኝ፣ አምራቹ አዲዳስ ይህንን ውድድር ታሳቢ አድርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተው ነው። የጫማው ምርት ከዚህ ቀደም ከፈጠሩት የመወዳደሪያ ጫማ 40 በመቶ ቀለል ያሉና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የፊት እግሩ ከጫማው ርዝመት 60 በመቶ ላይ የተቀመጠ ነው ተብሏል።
‹‹ተዓምራዊው ጫማ›› የሚል ቅፅል ያገኘው የአዲዳስ አዲሱ ምርት 551 ዶላር ዋጋ ሲኖረው፣ ከአንድ ውድድር በላይ ግልጋሎት እንደማይሰጥና እንደሌሎች ጫማዎች ሊበረክት እንደማይችል ተጠቅሷል። በአንፃሩ የጫማ አምራቾች በውድድሮች ክብረ ወሰን ይሰበራል በሚል ሽያጫቸው እንዲጨምር የሚያደርጉት ፉክክር አትሌቲክሱን እንዳይጎዳው የሚል ሥጋት አለ። ሆኖም ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት በማራቶን ሴቶች አዲስ ክብረ ወሰን መጨበጥ መቻሏ ሁሌም በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።