Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ የያዘችው አቋም ድርድሩ የተመሠረተበትን መርህ ለመናድ ያለመ ነው ተባለ

ግብፅ የያዘችው አቋም ድርድሩ የተመሠረተበትን መርህ ለመናድ ያለመ ነው ተባለ

ቀን:

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውኃ አሞላልና የግድቡ ዓመታዊ አሠራር (ኦፕሬሽን) የሚመራበትን ደንብ ለመወሰን በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል በተጀመረው አዲስ ድርድር ላይ የግብፅ መንግሥት እያራመደ ያለው አቋም፣ ሦስቱ አገሮች የሚደራደሩበትን መሠረታዊ መርህ መናድ ላይ ያነጣጠረ ነው ተባለ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የነበሩትም ሆነ አሁን በድጋሚ የተጀመረው ድርድር መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ሦስቱ አገሮች በሱዳን ካርቱም የፈረሙት የትብብር መርሆች መግለጫ (DoP) ስምምነት መሆኑን አንድ ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ለምታደርገው ድርድር መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ምንጩ፣ ዳግም በተጀመረው ድርድር ግብፅ የትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነትን የሚያፈርስ አዝማሚያ በስፋት ማሳየቷን ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1959 ግብፅና ሱዳን የዓባይን ውኃ ለብቻቸው ለመቆጣጠር አልመው፣ የውኃ ድርሻ የተከፋፈሉበት ስምምነት ላይ የተቀመጡ ነጥቦችን፣ እንደገና በተጀመረው ድርድር በማቅረብ ኢትዮጵያ ለ1959 ስምምነት በእጅ አዙር ተገዥ እንድትሆን ለማድረግ ያለመ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ድርድሩን የሚከታተሉት ምንጮች ገልጸዋል።

ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈራረሙት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመከለተው የትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ ያመጣ መሆኑን ምንጮቹ ያስረዳሉ። ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉት ምንጮቹ እንደገለጹት፣ ሦስቱ አገሮች በፈረሙት በዚህ የትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ላይ የስምምነቱን አስፈላጊነት የሚገልጸው መግቢያ ብቻውን ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ያመጣ ነው። 

የስምምነቱ መግቢያ ሦስቱ አገሮች የዓባይ ውኃ የጋራ ሀብታቸው መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባትና ለሦስቱም አገሮች ሕዝቦች ዕድገት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ተባብረው ለመሥራት የሚከተሏቸውን መርሆዎች ያስቀመጡበት እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ ይገልጻል ብለዋል። 

‹‹ይህ ስምምነት በጋራ መግባባት፣ በጋራ ጥቅም፣ በቅን ልቦና፣ የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ትብብር ለማድረግ ስምምነት የደረሱበትና ወደ እዚህ የሚያደርሱ መርሆዎችንም ያስቀመጡበት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከመግቢያው በተጨማሪ በስምምነቱ ውስጥ ከተቀመጡ የትብብር መርሆዎች መካከል ሁለቱን ብቻ በመውሰድ፣ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ ምንጩ ያስረዳሉ።

‹‹በስምምነቱ ከተጠቀሱ የትብብር መርሆዎች መካከል ሁለቱን፣ ማለትም ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህና ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህን መከተል የሚሉትን ብቻ ብንመለከት ግብፅ ከዓባይ ውኃ አንድ ጠብታ የቀነሰ በህልውናዬ መጣ ከማለት ወጥታ፣ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፋሰሱ አገሮች ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ የዓባይን ውኃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ የተስማማችበት ነው፤›› ብለዋል።

ጉልህ ጉዳት አለማድረስ በሚለው መርህ መሠረት ሦስቱ አገሮች በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስና ይህንንም ለመከላከል ተገቢውን ዕርምጃ ሁሉ ለመውሰድ መስማማታቸውን፣ በፍትሐዊና በምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ መሠረት ደግሞ ሦስቱ አገሮች የጋራ የውኃ ሀብታቸውን በየግዛታቸው ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀምና በዚህ ላይም ለመተባበር ተስማምተው፣ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱን የሦስቱ አገሮች መሪዎቻቸው መፈራረማቸውን አስረድተዋል።

እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመው ይህ የትብብር መርሆች መግለጫ (DoP) ስምምነት ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት በይፋ ተቀብለው የፈረሙበት የመጀመሪያው ታሪካዊ ሰነድ መሆኑን የገለጹት ምንጩ፣ እስካሁን ድረስ ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮች ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉልበት የሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል። በተቃራኒው ደግሞ ግብፆች ይህንን ስምምነት ከፈረሙ በኋላ መፀፀታቸውን፣ የግብፅ ልሂቃንም ስምምነቱን በመቃወም በአገራቸው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችትና ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡  

ይህንንም ተከትሎ ግብፅ አሁን እየተካሄደ ባለው ድርድር፣ ከቀደሙት የድርድር ሒደቶች በተለየ ሁኔታ እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን የሚሸረሽር፣ ወይም ድርድሩ በዚህ ስምምነት ላይ እንዳይመሠረት ለማድረግ አቋም ይዛ መምጣቷን ምንጩ ተናግረዋል።

አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር የትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነትን መሠረት የማያደርግ ከሆነ ደግሞ፣ ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ. በ1959 በተፈራረሙት ስምምነት ላይ የመመሥረት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ በመግለጽ በኢትዮጵያ በኩል ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

እኚሁ ምንጭ እንደገለጹት፣ ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈራረሙት ስምምነት ከስያሜው ጀምሮ ፍትሐዊ አይደለም። ሁለቱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈራረሙት የቅኝ ግዛት ስምምነት ስያሜ፣ ‹‹የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ስምምነት›› (Agreement for the Full Utilization of the Nile Waters) መሆኑን የጠቀሱት ምንጩ፣ አሁን የሚደረገው ድርድር በትብብር መርሆች መግለጫ ስምምነት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ለማድረግ በግብፅ በኩል የተያዘው አቋም እስከ ዛሬ የተደረገውን ድርድር ወደ ዜሮ የሚመልስ፣ በቀጣይ የሚደረግ ድርድር ካለ እ.ኤ.አ. በ1959 ስምምነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ ያሴረ መሆኑን አስረድተዋል። 

በግብፅ በኩል እየተራመደ ያለው አቋም አሁን የሚካሄደው ድርድር በትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን በግብፅ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያወሱት ምንጩ፣ ይህንን ያደረጉበት ምክንያትም ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማትቀበለው መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የድርድሩን ጊዜ ለመፍጀት እንደሆነ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የግብፅ ፕሬዚዳንት አሁን እየተካሄደ ያለውን ድርድር በአራት ወራት ለማጠናቀቅ የተስማሙ በመሆናቸው፣ በግብፅ በኩል ይህንን የጊዜ ገደብ ያለ ስምምነት በማጠናቀቅ የድርድሩ መሠረት የሆነው እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመው የትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ውጤት አላስገኘም ተብሎ ፈራሽ እንዲሆን ሥልታዊ አቋም መያዙንም አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ የምታደርገው ድርድር በትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ላይ አልያም በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግጋት ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑ በግልጽ እንዲመላከት ካላረጋገጠች፣ ድርድሩ በእጅ አዙር እ.ኤ.አ. በ1959 ስምምነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል ሲሉ ሥጋታቸውን ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት አንቀጽ አምስት ከግብፅና ከሱዳን ውጪ ያሉ የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ ተጋሪ አገሮች የዓባይን ውኃ የመካፈል ወይም የመጠቀም ጥያቄ ካነሱ፣ ግብፅና ሱዳን የተነሳውን የይገባኛል ጥያቄ የጋራ ኮሚሽን አቋቁመው እንደሚያጤኑትና ይህንንም በሚያደርጉበት ወቅትም አንድ ወጥ አቋም ለማራመድ ስምምነት ማድረጋቸውን ይደነግጋል ብለዋል። በመሆኑም ድርድሩ እ.ኤ.አ. በ2015 ስምምነት ላይ ካልተመሠረተ ግብፅና ሱዳን ድርድሩን የሚያካሂዱት በ1959ኙ ስምምነት መሠረት ነው ለማለት በር እንደሚከፍትላቸው ገልጸዋል። 

በተጨማሪም እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ከግብፅና ከሱዳን ውጪ በሌላ የተፋሰሱ አገር በዓባይ ውኃ ላይ የሚነሳ የመጠቀምና ወይም የይገባኛል ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ውጤትን ካስከተለ፣ የመጠቀም መብትን ለሚያገኘው ሌላ አገር የሚመደበው የውኃ ድርሻ መጠን ከግብፅና ከሱዳን የውኃ ድርሻ በእኩል መጠን ተሠልቶ ተቀናሽ እንደሚሆን በስምምነቱ አንቀጽ አምስት ሥር መደንገጉን አስረድተዋል። ይህም ማለት ግብፅና ሱዳን በዓባይ ውኃ ላይ የመጠቀም ጥያቄ በሌላ አገር ከተነሳ ለድርድር እንደሚቀመጡና ጥያቄ ላነሳው አገርም የመጠቀም መብት ሊሰጡ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን የመጠቀም ፈቃድ የሚያገኘው የተፋሰሱ አገር የሚያገኘው የውኃ ድርሻ መጠን በግብፅና በሱዳን እንደሚወሰን አስረድተዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ የመጠቀም መብት ያገኘው ሌላ የተፋሰሱ አገር ከተፈቀደለት የውኃ መጠን በላይ እንዳይጠቀም፣ ግብፅና ሰዳን በጋራ በሚቋቁሙት ኮሚሽን አስፈላጊው ክትትል እንደሚያደረግበት እ.ኤ.አ. በ1959 ድንጋጌ መሥፈሩን ምንጩ አስረድተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን የምታደርገው ድርድር እ.ኤ.አ. በ2015 ትብብር መርሆዎች መግለጫ ስምምነት ውጪ እንዳይወጣ የያዘችውን አቋም አጠንክራ መያዝ እንዳለባት፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመዘናጋት ወይም በአንዳች ምክንያት የአቋም መንሸራተት ከተፈጠረ ግብፅና ሱዳን ድርድሩ እ.ኤ.አ. በ1959 ስምምነት የተካሄደ መሆኑን ለማወጅ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረትን ያጎናፅፋቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ የተካሄደውን ድርድር አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር በተመሳሳይ ቀን ያወጡት የተናጠል መግለጫም ምንጩ የገለጹትን የሚያጠናክር ነው። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹አዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የሦስትዮሽ ድርድር ግብፅ እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመውን የትበብር መርሆች መግለጫ (DoP) ስምምነትን የሚያፈርስ አቋም ይዛለች፤›› ብሏል።

ግብፅ የናይልን ውኃ በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚፈልገውን እ.ኤ.አ. የ1959 የቅኝ ግዛት ዘመን አግላይ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና በዚህ የቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት ለራሷ የሰጠችውን ‹‹የውኃ ኮታ›› ሕጋዊ ለማድረግ የያዘችውን አቋም አሁንም አጠናክራ በመቀጠሏ፣ በአዲስ አበባው ድርድር ላይ ተጨባጭ ዕድገት እንዳይገኝ ማደረጉንና ይህም የኢትዮጵያ መንግሥንትን በእጅጉ እንዳሳዘነ መግለጫው አመልክቷል። 

አሁን እየተካሄደ ያለው የሦስትዮሽ ድርድር ዓላማ የኢትዮጵያን መብት በሚያረጋግጥና የታችኛው የተፋሰሱ አገሮችን ሕጋዊ ሥጋቶች ባገናዘበ መንገድ የህዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ የውኃ አሞላልና ዓመታዊ አሠራር መመርያዎችንና ደንቦችን ማጠናቀቅ እንደሆነ የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ኢትዮጵያም በዚሁ አግባብ በድርድሩ እየተሳተፈች እንደምትገኝ አስታውቋል። 

‹‹ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን የኢትዮጵያውያን ትውልዶች ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥታ፣ በዚህ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ እየተሳተፈች መሆኗን ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው፤›› ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ማሳረጊያውን ድምዳሜ በግልጽ አስቀምጧል።

የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የግብፅ ተደራዳሪ ቡድን በግልጽ በተቀመጡ ዓላማዎች የሚመራ ገንቢ ድርድር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል›› በማለት አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር የሚመራበት ግልጽ መሠረት እንደሌለው ለማመላከት ሞክሯል። በመቀጠልም፣ ‹‹የድርድሩ ዋና ዓላማ የግብፅን ብሔራዊ ጥቅም፣ የውኃ ደኅንነቷንና አሁናዊ የውኃ አጠቃቀሟን የሚያስጠብቅ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ የሦስቱን አገሮች ጥቅም የሚያጎለብት የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና ዓመታዊ አሠራር የሚመራበት ስምምነት ላይ መድረስ ነው›› ብሏል።

ይህ አገላለጽም እ.ኤ.አ. በ2015 ስምምነት ላይ የተቀመጡትን ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ፣ እንዲሁም ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህዎችን የሚቃረን ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ ግብፅ ድርድሩ እ.ኤ.አ. በ2015 ስምምነት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ለማድረግ የምታራምደውን አቋም በግልጽ እንደሚያመላክት ከምንጩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...