Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዕዳውን መክፈል ያቃተው ሶደሬ ሪዞርት በሐራጅ እንዲሸጥ ፍርድ ቤት ወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓመታት በፊት ሶደሬ ሪዞርትና መዝናኛን ከመንግሥት የገዙት ባለሀብቶች  ገንዘቡን መክፈል ባለመቻላቸው፣ መንግሥት ሪዞርቱን በሐራጅ ሸጦ ገንዘቡን እንዲያገኝ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት የንብረት ተረካቢና አስረካቢ ይታይሽ መኮንን ተፈርሞ የወጣው ውሳኔ እንደሚያሳየው፣ ከዚህ ቀደም ገዥዎቹ ሶደሬ በሐራጅ እንዳይሸጥ ያስወሰኑት የዕግድ ውሳኔ ተቀልብሶ ሐራጁ እንዲወጣ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ሶደሬ ሪዞርት ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በሐራጅ እንዲሸጥ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሐራጁ የሚካሄደው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት የሐራጅ ክፍል እንደሚሆን ውሳኔው ያሳያል፡፡

የሪዞርቱ የጨረታ መነሻ ዋጋ 60 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ተጫራቾች አንድ አራተኛውን የንብረቱን ግምት ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አሸናፊው ሙሉን ዋጋ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ በማድረግ ንብረቱን በፍርድ ቤቱ በኩል ይረከባል ተብሏል፡፡

ከጨረታው መከፈት ቀደም ብሎ ባሉት ሦስት የሥራ ቀናት አስተዳደሩ ተጫራቾችን በትራንስፖርት ወስዶ ሶደሬ ሪዞርትን ማስጎብኘት እንዳለበትም የፍርድ ቤት ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ዴክ ኦሮሚያ ቢዝነስ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሶደሬ ሪዞርትን መጀመሪያ ከአሥር ዓመታት በፊት በከፊል የገዛ ሲሆን፣ በኋላም ለመጠቅለል ተስማምቶ ነበር፡፡ ድርጅቱን ባለሀብቱ አቶ ድንቁ ደያስ አብላጫ ባለድርሻ የሆኑበት ሲሆን፣ የኦሮሚኛ ዘፋኙ ቀመር የሱፍም ድርሻ እንዳለው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዴክ ሪዞርቱን የገዛው በፊት የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጀቶች ኤጀንሲ ከሚባለው ተቆጣጣሪ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ስያሜው የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ይዞታና አስተዳደር በመባል ተሰይሟል፡፡ ዴክ ከመግዛቱና ከመረከቡ በፊት ሶደሬ ሪዞርት ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በመንግሥት እጅ ነበር፡፡

ባለሀብቶቹ ሪዞርቱን ሲገዙ የጠቅላላ ዋጋውን 35 በመቶ ወዲያው ከፍለው ቀሪውን በአምስት ዓመታት ከፍለው ለመጨረስ ነበር የተስማሙት፡፡ ባለሀብቶቹ የገዙት የሶደሬ ሪዞርትን 60 ሺሕ አክሲዮኖች እያንዳንዳቸው በአንድ ሺሕ ብር ሲሆን፣ ጠቅላላው ዋጋውም በወቅቱ 60 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በዴክ ኦሮሚያ በኩል የገቡትን ውል ባለማክበርና በተባለው አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍለው መጨረስ ስላልቻሉ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ንብረቱን በሐራጅ ሸጦ የመንግሥትን ገቢ እንዲያስመልስ ፍርድ ቤት መወሰኑን ሪፖርተር ያገኘው የፍርድ ቤት ሰነድ ያሳያል፡፡

ከዚህ ቀደም በሐምሌ ወር አስተዳደሩ አውጥቶት የነበረውን የሐራጅ ጨረታ ባለሀብቶቹ በፍርድ ቤት አሳግደውት የነበረ ሲሆን፣ የጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጨረታ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዕግድ ውሳኔውን ያነሳበትን ምክንያት አልጠቀሰም፡፡

‹‹የሐራጅ ዓላማ ሪዞርቱን ሸጦ ለመንግሥት ይገባ የነበረውን ገንዘብ ማስመለስ ነው፡፡ 60 ሚሊዮን ብር መነሻ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ገቢ ከሽያጩ ይገኛል ብለን እንጠብቃለን፡፡ 60 ሚሊዮን ከዓመታት በፊት የተተመነ ዋጋ ስለሆነ አሁናዊ የሪዞርቱ ዋጋ ከዚያ በላይ ነው፡፡ ክፍያ በመዘግየቱ የደረሰው ጉዳት፣ ወለድና የተለያዩ ኪሳራዎች ታሳቢ ተደርገው ከሽያጩ ላይ ከሚገኘው ገቢ ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡ ሪዞርቱን ለገዙት ባለሀብቶች የተላለፈው ከዓመታት በፊት የነበረ ሲሆን፣ እስከ ዛሬ ገቢ ሲያገኙበት ነበር፤›› ሲሉ አንድ የአስተዳደሩ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  ሪፖርተር የባለሀብቶቹን ሐሳብ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች