Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢሠማኮ የስደተኞችን መብት ለማስከበር ከሌሎች አገሮች አቻ ተቋማት ጋር ትብብር መፈራረም ጀመረ

ኢሠማኮ የስደተኞችን መብት ለማስከበር ከሌሎች አገሮች አቻ ተቋማት ጋር ትብብር መፈራረም ጀመረ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሠራተኞችና ስደተኞችን መብት ለማስጠበቅ ከተለያዩ አገሮች አቻ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነቶችን እየተፈራረመ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ኢሠማኮ ይህንን ያስታወቀው ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ሶማሊያና ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሠራተኞችንና ስደተኞችን መብት ለማስጠበቅ በጋራ ለመሥራት  ከሶማሊያ ሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር በተፈራረሙበት ወቅት ነው፡፡

የሰዎችን ሰብዓዊ መብት መጠበቅ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ በመሆኑ በስደት የሚገኙ ዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ከተለያዩ አገሮች ሠራተኛ ማኅበራት ጋር የሚደረገው እንዲህ ያለው ስምምነት ስደተኞች ባሉበት አገር ከሚገኙ የሠራተኛ ማኅበሮች በቀላሉ ዕገዛ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከሶማሊያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን ጋር የተደረገው ስምምነትም ከሶማሌያ የሚመጡ ስደተኞችና ሠራተኞች መብታቸው እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር የሚከታተልና የሚሠራ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሸን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ገልጸዋል፡፡

ሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በሚኖሩበት ቦታና በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ አገሬው የሚያገኘውን መብትና ጥቅም እንዲያገኙ የሶማሊያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን የሚሠራ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት ስደተኛ ሠራተኞች የሕግ ከለላ እንዲያገኙ ጭምር የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

እንዲህ ያለውን ስምምነት በተከታታይ ከሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ ሠራተኞች ማኅበራት ጋር በመፈራረም የሚተገበር እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ በቀጣይ ወርም በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚገኙበት ከደቡብ ሱዳን ሠራተኞች ማኅበራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነት እንደሚደረግ  ገልጸዋል፡፡

በተለይ በደቡብ ሱዳን በርካታ ኢትዮጵያውያን በንግድ ሥራ፣ በግል ሥራና በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ በመሆኑ የእነዚህን ዜጎች መብት ለማስጠበቅ ከደቡብ ሱዳን ሠራተኞች ማኅበር ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችለው ስምምነት በጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚፈረም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በማኅበር እንዲደራጁ ከተደረገ በኋላ ሊያጋጠማቸው የሚችለውን ችግር የደቡብ ሱዳን ሠራተኞች ማኅበር እንዲፈታላቸው የሚደረግ መሆኑን ከአቶ ካሳሁን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በኤምባሲዎች ብቻ መብታቸውን ማስጠበቅ አስቸጋሪ በመሆኑ በውጭ አገሮች የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ከተቋቋሙ አቻ ማኅበራት ጋር የሚያደርጓቸው ስምምነቶች ብዙዎችን ሊታደግ እንደሚችል አቶ ካሳሁን ጠቅሰዋል፡፡

ከሶማሊያ ሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር የተደረሰው ስምምነት በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የሚቆዩ ቢሆን እንኳ አስፈላጊው እንብካቤ እንዲደረግላቸውና ሌላው የሚያገኘውን መብት እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡

እንዲህ ያሉ ስምምነቶች በመንግሥታት መካከል ብቻ ሲደረግ የቆየ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲህ ያለውን ሥራ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱንም እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

‹‹ሠራተኛ ድንበር የለውም›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ የዓለም ሥራ ድርጅት ድንጋጌም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ የሠራተኛ ማኅበራት የየትኛው አገር የመጣ ሠራተኛን መብት የማስጠበቅ ግዴታ ጭምር ያለባቸውና የሚተገብሩት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ስምምነትና የዓለም አቀፉን የሠራተኞች ድርጅት ድንጋጌን  ከማስፈጸም አኳያ ከዚህ ቀደም ኢሠማኮ የተጫወተው ሚና እንደነበር የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢሰሠማኮ በኢትዮጵያ ችግር የገጠማቸው የውጭ ዜጎችን መብት ሲያስከብር እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ምሳሌ አድርገው የጠቀሱትም አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ኩባንያ ከባንግላዴሽ ሠራተኞችን ካመጣ በኋላ የገጠማቸውን ችግር እንዲፈታ በማድረግ ወደ አገራቸው እንዲሸኙ ማድረጉን ነው፡፡ በወቅቱ የኩባንያው ሠራተኞችን አባሮ ፓስፖርታቸውን ይዞ ስለነበር ወደ አገራቸው መመለስ ባለመቻላቸው ኢሠማኮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ፓስፖርታቸው እንዲለቀቅላቸውና ክፍያቸው ተከፍሎዋቸው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ሠራተኛ ማኅበራት እንዲህ ያለውን ሥራ መሥራት ያለባቸው በመሆኑ በዚሁ አግባብ የሚሠራበት ይሆናልም ብለዋል፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አቻ ተቋማት ጋር ከተጀመረው ስምምነት በተጨማሪ ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይ ስምምነት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ከኩዌት ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት በማድረግ የኩዌት ሠራተኞች ማኅበር መብታቸው ለተነካ ኢትዮጵያውያን ጠበቃ በማቆም ጭምር እንደሟገቱላቸው አስታውሰዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ከሶማሊያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን ጋር በአዲስ አበባ የተደረገውን ስምምነት በሶማሊያ በኩል የፈረሙት የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ፋሩክ ፌስቱ ናቸው፡፡

እሳቸውም በስምምነቱ በተካተተው መሠረት እንዲሁም የዓለም የሥራ ድርጅት መርሆዎችን ተከትለው ስደተኛ ሠራተኞችን እንደራሳቸው አገር ዜጎች መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...