Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት ታክስ መሻሻያ አዋጅና የንብረት አዋጅ በዚህ በጀት ዓመት ይፀድቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ከተረቀቁት የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅም ሆነ ከንብረት ታክስ አዋጁ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ መንግሥት እነዚህን አዋጆች አፅድቆ በዚህ ዓመት ተግባራዊ በማድረግ አጠቃላይ ገቢውን ማሳደግ መሠረታዊ ዓላማው መሆኑን አስታውቋል፡፡ መንግሥት እነዚህን አዋጆች በመጣል ዓመታዊ ገቢውን ለማሳዳግ ሲያቅድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ እስካሁን ከሚከፍላቸው የታክስ ዓይነቶች በተጨማሪ ኪሱን የሚዳብሱ ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎች የሚጠብቁት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ 

እንዲህ ያሉ ኅብረተሰቡን ለተጨማሪ ወጪ ሊዳርጉ የሚችሉ አዋጆች ጫናቸው እንዳይበረታ ግን አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሊቀበላቸው በሚችልባቸው ደረጃ ፀድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ኅብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ሊመክርባቸውና ሊወያይባቸው ይገባል፡፡ መንግሥትም ቢሆን በአዋጆቹ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብና አዋጆቹን በተመለከተ ማኅበረሰቡንና ባለድርሻዎችን በማወያየት ሐሳባቸውን የመስማትና የማካተት ግዴታ አለበት፣ ይህንን ማድረግ ደግሞ ሁለቱንም ወገኖች የሚያግባባና መንግሥትን ደግሞ የሚያስመሠግን ይሆናል። ዋናው ነገር ግን እንዲህ ያሉ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ገንዘብ ሚኒስቴር አዲሱን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ረቂቅ ላይ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ግብዓት ለማሰባሰብ አዘጋጅቷቸው የነበሩ የውይይት መድረኮች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በረቂቁ ላይ አስተያየት እንዲሰጡና ጠቃሚ የሚሏቸውን ግብዓቶች እንዲያቀብሉ ሁሉ ዕድል የመስጠቱን ያህል የተጠበቀውን ያህል ተወያይ ማግኘት እንዳልቻለ እናስታውሳለን፡፡ 

በዚህም ምክንያት የታሰበውን ያህል ግብዓት ተገኝቷል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም የቢዝነስ ዘርፍ ለተከታታይ ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል የተባሉ የግል ዘርፍ ተዋናዮች አልታዩም፡፡ በተለይ የንግድ ኅብረተሰቡን ይወክላሉ የተባሉ የንግድ ምክር ቤቶች ተወካዮችና ሌሎች የሙያ ማኅበራት በዚህ መድረክ ላይ አለመኖር በረቂቁ ላይ አሉ የሚባሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ ግብዓት መስጠት ተችሏል ተብሎ አይታሰብም፡፡  

ነገር ግን አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ ብዙ ጥያቄዎች የሚያነሱበት እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ በረቂቁ የተካተቱ ጥቂት የማይባሉ ድንጋጌዎች በኩባንያዎች ላይም ሆነ በተገልጋይና ተጠቃሚዎች ላይ ሊያሳርፈው የሚችለውን ጫናዎች ተረድቶ፣ ረቂቁ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጠንከር ያለ ሐሳብ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው እንግዲህ ረቂቁ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ አዲስ የሆነውና የእያንዳንዱን ባለንብረት ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሁሉንም ኅብረተሰብ ይነካል የተባለው አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት የሚመለከተው አካል ሁሉ ሐሳብ እንዲሰጥበት ገንዘብ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት አሳውቋል፡፡ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አመላክቷል፡፡ 

ይህ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ አዲስ ከመሆኑም በላይ፣ በእያንዳንዱ ክልልና እያንዳንዱን ባለንብረት የሚመለከት በመሆኑ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኅብረተሰቡ በደንብ ሳይመክርባቸው መፅደቅ እንደሌለበት ይታመናል፡፡  

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ በብርቱ ምክክርና ውይይት ያስፈልገዋል ተብሎ የሚታመነው አዋጁ በዋናነት ከመሬት፣ ከሕንፃና ከመሰል ግንባታዎች ባለቤትነት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የንብረት ታክስ አዋጁ የሚያስከትለው ተጨማሪ ታክስ ክፍያ ኢኮኖሚው ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ አዋጁ ብዙኃኑ የተቀበለው እንዲሆን በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ሐሳብ ሊንሸራሸርበት ይገባል፡፡ 

ከመንግሥት አንፃር ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበት የታክስ ዓይነት መተግበሩ ሊያስገኝለት የሚችለውን ጥቅም በረቂቁ መግቢያ ላይ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አስፈላጊነቱን በተመለከተም የሰጠው ማብራሪያ በሥራ ላይ ያለው የቦታ ኪራይና የቤት ታክስ ሥርዓት በፍጥነት እየጨመረ ያለውን የከተማ ነዋሪ ሕዝብ አገልግሎትና የመገልገያ ቦታዎች ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት የሚያስችልና ለመንግሥትም ትርጉም ያለው ገቢ ለማመንጨት የሚያስችል በመሆኑ ነው ብሏል፡፡

የንብረት ታክስ በከተሞች ነዋሪ በሆነው ሕዝብ መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚያሰፍን፣ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶችንና የመገልገያ ቦታዎችን በተሻለ ጥራትና በዘመናዊ ዘዴ ከፍ ባለ መጠን ለማቅረብም የዚህ አዋጅ መተግበር አስፈላጊ  ነው ብሏል፡፡

የኢንቨስትመንት ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት በሚጣል ታክስ አማካይነት መሰብሰብ የሚያስችል በመሆኑ፣ የመሬት ነክ ንብረት ግመታም ሆነ የንብረት ታክስ አጣጣልና አሰባሰብ የሚካሄድበት ወጥነት ያለውና ግልጽነትን የሚያረጋግጥ የገበያ ሥርዓት በመሆኑም አስፈላጊ የታክስ ዓይነት እንደሆነ በረቂቁ መግቢያ ላይ አመላክቷል፡፡ ሌሎች ጠቀሜታዎቹንም በዝርዝር አቅርቧል፡፡ 

ይህ ምልከታው ትክክል ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም፣ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ ግን ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ በቅርቡ እንኳን የዚህ አዋጅ አካል እንደሆነ ተደርጎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሰበሰብ የነበረው ገቢ በማኅበረሰብ ላይ የፈጠረው ብዥታና የኑሮ ጫና ለአብነት የሚጠቀስ ነው።

በአዲስ አበባ አስተዳደር እንደገለጸው፣ ይህ የታክስ ዓይነት አዲስ ባይሆንም ለቦታና ለቤት ይከፈል የነበረውን ዋጋ በማሻሻል የቀረበ መሆኑን ቢገልጽም፣ የተሻሻለውን ዋጋ ተከትሎ ግን ተጨማሪ ግብር ክፍያ ከፍለናል ያሉ አከራዮች ሳይውሉ ሳያድሩ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ላይ ኪራይ ጨምረዋል፡፡ ስለዚህ አዲሱ የንብረት ታክስ አዋጅ ጫናው እንዳይበረታ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ውይይቱ የሚጠቅመውም እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚረዳ ይሆናል፡፡ 

በፌዴሬሽን ደረጃ የሚተገበረው የንብረት ታክስ አዋጅም ከንብረት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፈል የሚስገድድ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጫና የሚያሳርፍ መሆኑ ስለማይጠረጠር በቂ የውይይት ጊዜ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ረቂቁን በደንብ መርምሮ ሐሳቡን የማቅረብ መብቱን ይጠቅማል፡፡ በተለይ አዋጁ በምን ዓይነት መልኩ ቢተገበር ይሻላል የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ምሁራንም የበኩላቸውን ሐሳብ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ቢችሉ አዋጁን አዳብሮ ለማፅደቅ ያስችላል፡፡ 

አዋጁ እያንዳንዱን የመኖሪያ ባለቤት የሚመለከት ከመሆኑ አንፃርም፣ ባለንብረቶች ጉዳዩን በማስጠናት ጭምር መፍትሔ የሚሆን ማቅረብ ካልቻሉ ከፀደቀ በኋላ መሟገት መፍትሔ እንደማይመጣ በመገንዘብ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ያመቻቸውን መድረክ በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት ግብር ታክስን ሲተገብር እንዳስተዋልነው ብዙ የንግድ ድርጅቶች የተጠየቅነው ዋጋ ከፍተኛ ነው ብለው ሲያማርሩ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከዚህም ሌላ ከአተገባበር አንፃር አሉ የሚሉትን ክፍተቶች ከዘገየ በኋላም ቢሆን ሲያቀርቡ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ አሁንም በንብረት ታክስ አዋጅ እንዲህ ያለው ክፍተት እንዳይፈጠር የንግድ ኅብረተሰቡ ዕድሉን እንዲጠቀም ማስታወስ ነገ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመድፈን ያስችላል፡፡ 

ከዚህ አንፃር በተለይ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ የንግድ ምክር ቤቶች የንብረት አዋጁን ረቂቅ ለአባላት በማሠራጨት አስተያየት መሰብሰብ፣ ይህንኑ በሚገባ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ ይዘው መቅረብ ግዴታቸው ነው፡፡ ረቂቁ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ሐሳቦችን ይዞ በመቅረብ ሁሉንም ያግባባ ሐሳብ ይዞ በመቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡም ይገባል፡፡ 

በተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጁ ላይ የታየው ደካማ ተሳትፎ በዚህም አዋጅ መታየት የለበትም፡፡ ይህንን አዋጅ ለማዳበርና ሊፈጥር ይችላል የሚባለውን ጫና ለመቀነስ አንዱና ብቸኛው አማራጭ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ ይዞ በመቅረብና መሞገት የየትኛውም ዜጋ መብት በመሆኑ ሁሉም ይህንን መብቱን ሊያሳይ ይገባል፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የንብረት ታክስ አዋጁን ለመተግበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ቀላል ላይሆንለት ይችላል፡፡ ይህንን ሥጋት መቀነስ ግን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነት የሚጣቸው አካላት በሚገባ መደራጀት ብቻ ሳይሆን ከመሬትና ከተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ተቋማት ውስጥ ያሉ በሙስና የተጨማለቁ ሠራተኞች ዓይነት ይዞ ግቡን ሊመታ ስለማይችል፡፡ የመሬትና የቦታ ጉዳይ ወትሮም ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ የአዋጁ መተግበር ሊፈጥር የሚችለውን ቀዳዳ አሻግሮ በማየትና ለዚህ ዓይነቱ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ዕርምጃዎች የአዋጁ አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አጠቃላይ አሠራሩ ዘመናዊና በአግባቡ በተደራጀ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በተደራጀ መረጃ ላይ እንዲሠራ ለማድረግ አዋጁን ወደ መሬት ከማውረድ በፊት የራሱን የቤት ሥራ ቀድሞ መሥራት አለበት፡፡

ካለ በቂ ዝግጅት ወደ ሥራ የሚገባ ከሆነ ደግሞ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም አዋጁ ከመፅደቁ በፊት በቂ የውይይት መድረክ ከማስፈለጉም በላይ፣ መንግሥት በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመሬት፣ የቦታ፣ የግንባታዎችና ተያያዥ ንብረቶችን መረጃ በሚገባ ማደራጀት ቀዳሚው ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንን ሳያደርግ አዋጁን ተሯሩጦ ማፀደቅ ብቻውን ወደተፈለገው ግብ እንደማያደርስ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት