Sunday, December 10, 2023

ለዓለም አቀፍ ጫና ምንጭ እየሆነ የመጣው የሽግግር ፍትሕ ጉዳይና ውዝግቦቹ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ክልል ጦርነት ከፈነዳ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ጫና አዙሪት መላቀቅ አልቻለችም፡፡ መጀመሪያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረቢያ ኮሪደር የመክፈት ጉዳይ ነበር የኢትዮጵያን መንግሥት ለዓለም አቀፍ ጫና የዳረገው ጉዳይ፡፡ ‹‹ትግራይ ሲጅ››፣ ‹‹ትግራይ ጄኖሳይድ›› በሚሉ መፈክሮች የተካሄደው ዘመቻና ቅስቀሳ በትግራይ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያን መንግሥት እስከ ማዕቀብ ለደረሰ ለከባድ ዓለም አቀፍ ጫና ዳርጎት ነበር፡፡

በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት አድማሱ ሰፍቶ የሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎችን ማዳረስ ቀጠለ፡፡ በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ኦነግ ሸኔ የሚያካሂደው የንፁኃን ግድያና ከመንግሥት ጋር የፈጠረው ግጭት እየተባባሰ ሄደ፡፡ ይህ ሁሉ አድማሱን እያሰፋ የመጣ ቀውስ ደግሞ አገሪቱን ለበለጠ ዓለም አቀፍ ጫና ተጋላጭ ማድረግ ቀጠለ፡፡

ለዓለም አቀፍ ጫና ምንጭ እየሆነ የመጣው የሽግግር ፍትሕ ጉዳይና ውዝግቦቹ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ፀጋአብ ክበበው ዳካ

ቀጥሎ የመጣው መንግሥት በትጥቅ ከሚፋለሙ ኃይሎች ጋር ተቀምጦ እንዲነጋገር የማስገደድ ዝንባሌ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና ነበር፡፡ በአገሪቱ በአስቸኳይ የተኩስ አቁምና ግጭት የማብረድ ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቁ ዘመቻዎች ጎልተው መደመጥ ቀጠሉ፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች በጦርነቱ መዛላቸውና ዓለም አቀፍ ጫናው ታክሎበት ወደ ድርድር እንዲገቡ ገፊ ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመ የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ከአሥር ወራት በፊት መፈረሙ ይታወሳል፡፡ ከዚያ ወዲህም ቢሆን ግን ዓለም አቀፍ ጫና የተለያዩ ገጽታዎችን ተላብሶ መከሰቱን ቀጥሏል፡፡ ከኦነግ ሸኔና ከሌሎች የትጥቅ ቡድኖች ጋር ተመሳሳይ ድርድርና የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ግፊቱ ቀጥሏል፡፡ በግጭት የተሳተፉ ኃይሎችን ትጥቅ አስፈትቶና አሠልጥኖ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ የሚል ጫናም በሌላ ጎን ቀጥሏል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም መልሶ ግንባታ፣ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት፣ እንዲሁም ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ተጨማሪ ጫና የፈጠሩ ጉዳዮች ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ቀውሶችን በኃይል የመፍታት ጥረት ቆሞ፣ አጠቃላይ ሁሉንም አካታች የሆነ የብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያ አገራዊ ምክክር እንዲካሄድ የሚጠይቅ ግፊትም ጎላ ብሎ መጥቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ልክ እንደ ብሔራዊ ምክክር ሁሉ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ የማካሄድ ጉዳይ ኢትዮጵያ ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳበት አጀንዳ እየሆነ ነው፡፡ እውነት ማፈላለግ፣ የተበደለ የሚካስበት ሁኔታ መፍጠር፣ ያለፈ ቂም፣ ቁስልና ቁርሾ ሽሮ እውነተኛ መግባባትና ሰላም የመፍጠር ጉዳይ አሁን መላው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ሲሆን ማየት የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑን በግልጽ እያንፀባረቀ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መድረኮች ላይም ይኼው የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ የማስፈን ጉዳይ በጉልህ ተነስቷል፡፡

መንግሥት በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን ጥረት መጀመሩን ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሒደቱ ሁሉንም አካታች፣ ተዓማኒ፣ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን እየጠየቀ ነው፡፡ መንግሥት የሽግግር ፍትሕ መተግበሪያ ፖሊሲ ማዘጋጀቱን ሲያስታውቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ሒደቱ የይስሙላ መርሐ ግብር ሳይሆን ሀቀኛ ክዋኔ እንዲሆን እየጠየቀ ነው፡፡ መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት በስምምነት መቋጨቱንና በዚያ ላይ የሽግግር ፍትሕ ሒደት መጀመሩን በአዎንታዊ ስኬት እንዲታይለት ይወተውታል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን የሰላም ስምምነት መፈረሙ የተሟላ ሰላም በኢትዮጵያ አላስገኘምና ሁሉንም አካታች የሆነ የሽግግር ፍትሕና ዕርቀ ሰላም መፍጠር አስፈላጊ ነው በሚል በመንግሥት ላይ ግፊት ማድረግን የመረጠ ይመስላል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመውና የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ሲያጠና የቆየው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የተባለው ኮሚሽን፣ ከሰሞኑ ባቀረበው ሪፖርት የሽግግር ፍትሕን ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ኮሚሽኑ የአንድ ዓመት የሥራ ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም እንደ አስፈላጊነቱ  የሥራ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ኮሚሽኑ ያም ቢሆን ግን የትግራይ ክልል ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. እስካሁን በኢትዮጵያ ተባብሰው የቀጠሉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ በሪፖርቱ በስፋት አቅርቧል፡፡

ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ሰብሳቢና ባልደረቦቻቸው በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው ነበር፡፡

የኮሚሽኑ አመራሮች በዚህ ሪፖርታቸው የተካተቱ ፍሬ ነገሮችን ስዊዘርላንድ ጄኔቭ በሚገኘው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ፊት ለተጨማሪ  ውይይት አቅርበዋል፡፡ ሐሙስ ዕለት በ54ኛው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ 18ኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው የኢትዮጵያ ሪፖርት በርካታ የዓለም አገሮች ተወካዮች ውይይት ያደረጉበት ነበር፡፡ ከአገሮች ተወካዮች በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ወኪሎች ሐሳብ የሰጡበት ይህ ስብሰባ በዋናነት የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ተነስቶበት ነበር፡፡

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሐመድ ቻንድ ኦስማን ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፣ ‹‹የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አሰቃቂ ከሚባሉ ግጭቶች አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመ አጋጣሚ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ የሆነውን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የመጠበቅ ሚናውን መወጣት እንዳቃተው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ የተባባሰው የግጭት አዙሪትና ቀውስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ እንደ አገር የቆመችበትና ማኅበራዊ መስተጋብር ቀስ በቀስ እየሸረሸረው ይገኛል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

የሽግግር ፍትሕ ማስፈን በኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የሽግግር ፍትሕ አንገብጋቢና ቀዳሚው ጉዳይ መሆን እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ረቂቅ አዘጋጅቶ ማቅረቡን አስረድተው፣ ‹‹ረቂቁ በየደረጃው ምክክር ተደረገበት ቢባልም ሒደቱን በጥንቃቄ በመመርመር ያገኘነው ውጤት ግን የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ዓለም አቀፍ መመዘኛን እንኳ የማያሟላ ነው፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ከደረጃ በታችና የምንጠብቀው ዓይነት አይደለም፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ የተጎጂ/ሰለባዎች ፍላጎትን መሠረት ያላደረገ፣ አካታችነትም ሆነ ግልጽነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን በብዙ ወገኖች ዘንድ እምነት ሊጣልበት የማይችል መሆኑንም የባለሙያዎች ኮሚሽኑ አስምሮበታል፡፡ መንግሥት ይህን የሽግግር ፍትሕ ያለውን ሒደት ለመጀመር የመቸኮልና ለማስተግበር የመጣደፍ ሁኔታ ይታይበታል ሲሉ ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚባሉ የመንግሥት ኃይሎችን ጥፋት መርምሮና አጣርቶ ለፍትሕና ለርትዕ ያቀርባል የሚለው ግምት እየተሟጠጠ መምጣቱንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ፣ ‹‹የሽግግር ፍትሕን በሚመለከት ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ጥረት አድርገናል፡፡ ሒደቱ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በማማከርም ሆነ በሌላም ሒደቱን ለመደገፍ ፈቃደኝነታችንንን አሳይተናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ምላሽ አለማግኘታችን አሳዝኖናል፤›› በማለት ነበር የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ለተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ የተናገሩት፡፡

ለተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ሪፖርት ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ፀጋአብ ክበበው ዳካ ግን፣ ሪፖርቱ በአሉታዊ ድምዳሜዎች የተሞላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ያሳየችውን መሻሻልና ለውጥ ያልተመለከተ፣ የተዛባና ሚዛኑን ያልጠበቀ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት የጥይት ድምፅ የማስወገድ ማዕቀፍን ገቢራዊ በማድረግ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻልም ሆነ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው ያሉ ጥረቶች በኮሚሽኑ ሪፖርት አንዳችም ግምት አለማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው ነው አቶ ፀጋአብ የተናገሩት፡፡

‹‹የኮሚሽኑ ሪፖርት አጠናን ጥያቄ በሚያስነሳ ሁኔታ ከሩቅ ቦታ ሆኖ የተጠናቀረ ነው፡፡ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የመጡ በርካታ የፖለቲካ መሻሻሎችንም በተንሸዋረረ መንገድ የሚመለከት ነው፡፡ ሪፖርቱ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (OHCHR) መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም ካቀረቡት የጋራ ሪፖርት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው፤›› በማለትም ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽኑ፣ ‹‹ደረጃውን ያልጠበቀ፣ ሙያዊ ግድፈት የሚታይበት፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሽረባ ያለው ሪፖርት ነው ያቀረበው፤›› ሲሉም የኢትዮጵያው ተወካይ ጠንካራ የአፀፋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ እንዲያደርግ ሙሉ ትብብርና ድጋፍ ያሳየው ቢሆንም፣ ነገር ግን ኮሚሽኑ በጀርባ በመሄድ ሀቀኛ ሪፖርት ከማቅረብ ይልቅ ኢትዮጵያን በመወንጀልና ስሟን በማጠልሸት ላይ ያተኮረ ሪፖርት እንዳቀረበ አቶ ፀጋአብ አስረድተዋል፡፡

አቶ ፀጋአብ ከዚህ በተጨማሪም የኮሚሽኑ ሪፖርት አንዳችም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያልያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን መረጃና በጎረቤት አገሮች ተገን ጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ወሬ መሠረት አድርጎ የተጠናቀረ ሪፖርት ነው ያቀረበው፤›› ሲሉም ወቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ብሎም ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን በሚል ለተወሰነ ጊዜያት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በነሐሴ ወር በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች ማወጇን የገለጹት አቶ ፀጋአብ፣ ኮሚሽኑ ግን ይህን ባልተገባ መንገድ ወስዶ ኢትዮጵያ ወደ ባሰ የሰብዓዊ መብት ቀውስ እንደገባች ለማስጮህ እየተጠቀመበት ነው ብለዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መከታተያ ቦርድ በፓርላማው መመሥረቱንና ችግር ተፈጥሮ ከተገኘ ተከታትሎ ዕርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ መመቻቸቱን አውስተዋል፡፡

ይህን ብለው ወደ ሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ገለጻ የገቡት የኢትዮጵያው ተወካይ፣ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ተከራክረዋል፡፡ በሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ላይ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ወኪሎች ጋር ውይይት ተጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህ የምክክር ሒደት ደግሞ በኢሰመኮና በተመድ ክትትል የተደረገበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

‹‹የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ መሠረቱ የሰፋ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የግጭቱ ተጎጂዎችን ያካተተ ብቻ ሳይሆን ሴቶችንና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልዩ ሁኔታ ያቀፈ ሒደት እንዲሆን ጥረት አድርገናል፡፡ ሒደቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅሬታዎችን በተሟላ ሁኔታ የሚፈታ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ኢሰመኮና የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በግጭት ቀጣናዎች የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችን አሰማርተዋል፡፡ የሚያቀርቧቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግሮች ካሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታውን መርምሮ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽንም በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ መሻሻል ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ የሚቀርቡ ማናቸውም ጥፋቶች ተቀብሎ ተጠያቂነት የማረጋገጥ፣ እውነትን የማፈላለግና ዕርቅ የመፍጠር ግብን አንግቦ የሚሠራ ነው፤›› በማለት ነበር የኢትዮጵያው ተወካይ አቶ ፀጋአብ የተከራከሩት፡፡

የኢትዮጵያው ተወካይ ይህንን ቢሉም አገሪቱ የሽግግር ፍትሕ ከማስፈን ጉዳይ ጋር በተገናኘ በብዙ አገሮች ተወቃሽ ከመሆን አልተረፈችም፡፡ በተመዱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተገኙና በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ያንፀባረቁ በርካታ አገሮች፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ኢትዮጵያ በሒደቱ የተሻለ አተገባበር አንድታሳይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የበርካታ አገሮችና ድርጅቶች ተወካዮች ኢትዮጵያ ከባለሙያዎች ኮሚሽን ጋር አልተባበርም ማለቷን በአሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሽግግር ፍትሕን በኢትዮጵያ በተሻለ መንገድ ለመተግበር ያስችላል የሚለውን ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቀጠለው የሰብዓዊ መብት ቀውስ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው የተናገሩት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የአውስትራሊያ፣ የካናዳ፣ የፈረንሣይ፣ የስዊዘርላንድ፣ የአየርላንድ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የሌሎችም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ተወካዮች ኮሚሽኑ በአገሪቱ ላይ ሊወሰድ አስፈላጊ ነው የሚለውን ዕርምጃ እንደ አንድ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብላቸው ሲጠይቁም ተደምጠዋል፡፡

ልክ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንደሚንፀባረቀው ሁሉ በኮትዲቯር ተወካይ የተወከለው የአፍሪካ ኅብረት ቡድን፣ ሩሲየ፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ቬኒዙዌላ፣ ኢራን፣ እንዲሁም ኡጋንዳና ኒጀር በተናጠል በበኩላቸው ኢትዮጵያን ደጋፊ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሽግግር ፍትሕ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ የጀመረችው የሽግግር ፍትሕ ሒደት እንዲሳካ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል አገሮቹ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መነሻነት በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር መሞከር ተገቢነት እንደሌለው ሞግተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጥር 2015 ዓ.ም. ባቀረበችው የሽግግር ፍትሕ መተግበሪያ ዕቅድ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥም ቢሆን ገና መግባባት የተፈጠረ አይመስልም፡፡ በረቂቅ ሰነዱ ላይ የሽግግር ፍትሕ ‹‹ዘላቂ ሰላም ዕርቅ፣ እንዲሁም ፍትሕና ርትዕ በብዙ አገሮች ለመፍጠር የሚረዳ›› መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የሽግግር ፍትሕ መሞከሯንም መለስ ብሎ ሰነዱ ይዳስሳል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓት መገርሰስ ማግሥት የተቋቋመው የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መርማሪ ኮሚሽን አዋቅሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በአግባቡ ሥራውን መሥራት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ወደ 61 የቀድሞ ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ያላግባብ ተገድለዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሊተገበር ይችላል የሚለው ተስፋም በዚያው ከስሟል ይላል፡፡

በደርግ መንግሥት ውድቀት ማግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ተጠሪ የሆነ፣ የደርግ ባለሥልጣናትን ጥፋት መርምሮ ተጠያቂ የሚያደርግ የልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እንደነበር ረቂቅ ሰነዱ ያስታውሳል፡፡ ይህኛውም ቢሆን በሒደቱ ውስጥ ተጎጂዎችንና ውስን ጥፋተኞችን ብቻ ያካተተ ሲሆን፣ የሽግግር ፍትሕ መሠረታዊ ይዘቶችን ያልያዘ በመሆኑ በአጭሩ ተኮላሽቷል ይላል፡፡

ኢትዮጵያ ካለፈ ታሪኳ ጋር መታረቅ ብቻ ሳይሆን መፃኢ ጉዞዋን በፍትሕ፣ በእኩልነት፣ በሰብዓዊ መብቶችና በአካታችነት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የሽግግር ፍትሕ ያስፈልጋታል በማለት ይኸው ሰነድ ይዘረዝራል፡፡ በዚህ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት መካሄድ መጀመሩንም መንግሥት አበክሮ ይገልጻል፡፡

ይሁን እንጂ የሽግግር ፍትሕ ጥያቄ ከማንም በላይ እያቀረበ የሚገኘው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በሒደቱ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ በማሰማት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በቅርቡ እንኳ በሰነዱ ላይ ለሚመለከታቸው አካላት የውይይት ግብዣ የፍትሕ ሚኒስቴር ቢልክም፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ግን ግብዣውን ተቀብሎ የተካፈለ አለመኖሩ ተነግሯል፡፡ የትግራይ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ከዚያ ይልቅ አስቀድሞ ከመንግሥት ጋር የተናጠል ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ሒደቱን በሚመለከት ብዙዎችን አላግባባ ከሚሉ ነጥቦች መካከል ከየት እስከየት ድረስ የተፈጸሙ ጥፋቶች በሒደቱ ይሸፈኑ የሚለው ጉዳይ እንደሚገኝበት ይነገራል፡፡ አንዳንዶች ከንጉሡ ዘመን ማክተም ጀምሮ የደረሱ ቀውሶች እንዲታዩ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ ሌሎች በበኩላቸው ከደርግ ወዲህ ያሉ ችግሮች ብቻ እንዲዳኙ ይጠይቃሉ፡፡ በሌላ በኩል በኢሕአዴግ ዘመን የተፈጠሩ ችግሮች ይታዩ የሚሉ ሲኖሩ፣ ሌሎች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ጊዜ ወዲህ ያለው ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች የሽግግር ፍትሕ አድማሱ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ በተፈጠሩ ቀውሶች ላይ እንዲያተኩር እየጠየቁም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ሒደቱን በዋናነት እያደናቀፈው ነው ተብሏል፡፡

በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት አጣሪ ኮሚሽን ተብሎ በተቋቋመው ተቋም የሕግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለም አብርሃም፣ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ጥድፊያ የበዛበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አቶ ዓለም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ሒደቱ የትግራይን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያገናዝብ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፖች ውስጥ አስቸጋሪ ሕይወትን በመግፋት ላይ እያሉ፣ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ የእናንተን ቁስል ለማከም ነው የመጣው ቢባሉ አጥጋቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ከኢሰመኮ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያሉ ተቋማትም ሆኑ እየተተገበሩ ያሉ ሒደቶች እውነቱን አጣርተው ፍትሕ ሊያሰጡን ይችላል የሚል መተማመን በትግራይ በኩል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሒደቱ ካልተከለሰና መተማመን የሚፈጥር ካልሆነ በስተቀር፣ በትግራይ የተፈጸሙ ጥፋቶች አሁን መተግበር በጀመረው የሽግግር ፍትሕ ተገቢ ፍትሕ ያገኛሉ የሚል ተስፋ አለመኖሩን ነው አክለው የገለጹት፡፡

‹‹የፌደራል መንግሥት ይህንን አካሂዳለሁ ብሎ ቀነ ገደብ አስቀምጧል፡፡ እኔ እስከማውቀው ጊዜ ድረስ ግን ይህ የትግራይን ወገን ፍላጎት የተከተለ አይደለም፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ በዚህ መንገድ ይተግበር መባሉ ተቀባይነት እንደሌለው በትግራይ በኩል ምላሽ መሰጠቱን አውቃለሁ፡፡ በይፋ የአብሮነት ሥራዎች በሽግግር ፍትሕ በኩል እየተሠሩ አለመሆኑን ነው የማውቀው፤›› በማለት ነው በትግራይ ወገን ያለውን አቋም ያብራሩት፡፡

አቶ ዓለም እንደሚሉት፣ ይህን ሒደት ለማስተካከል የትግራይ ክልል ተወካዮች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ተቀምጠው የተናጠል ንግግር ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱ ወገኖች በቅድሚያ ተቀምጠው ቢነጋገሩ ችግሩ ሊፈታ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ነው ኃላፊው ያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ የሚተገበረወ የሽግግር ፍትሕ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ጋር ይጋጫል የሚል ሥጋት ሲነሳ ቆይቷል፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በአንድ ወቅት የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ በተቋማቸው ሥር ቢከናወን አዋጭ እንደሆነ ሐሳብ ሲሰጡም ተደምጠዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕን ማን ይምራው? ከየት እስከየት ጊዜ ድረስ ያሉ ጥፋቶች ይታዩ? የሚሉ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ ክልሎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች የቀጠሉ ቀውሶች እንዴት ሊዳኙበት ይችላሉ የሚሉ ጉዳዮችም አሳሳቢ እንደሚሆኑበት እየተገመተ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -