Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ቀን:

  • በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን ይወስናሉ
  • በ1968 ዓ.ም. የወጣውን የቦታ ኪራይና የቤት ታክስ አዋጅ ይሻራል

ከተሞች ለዓመታዊ የካፒታል ወጪ (የልማት ወጪ) ፍላጎታቸው እንዲጠቀሙበት ታስቦ እንዲሰበስቡ በተወሰነላቸው መሠረት፣ የቤት ባለንብረቶች በየዓመቱ የሚከፍሉትን የንብረት ታክስ መጠን የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡

ባለንብረቶቹ በከተሞች የሚጠቀሙበት ቦታና ቤት ለየብቻቸው በሽያጭ የሚያወጡት ዋጋ ተሠልቶ፣ ወለሉንና ጣሪያውን የሚመለከት የክፍያ መጠን የያዘ ረቂቅ የንብረት ታክስ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ አስተያየት ቀርቧል፡፡

በተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም. በጥር ወር የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋራ ባደረጉት ስብሰባ፣ አሰባሰቡን ከፌዴራል መንግሥት ይልቅ በክልል መንግሥታትና በከተማ አስተዳደሮች እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ነው በገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት የተረቀቀው፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የገንዘብ ሚኒስቴር ሊያደርግ የሚችለውን ጥናት ተመርኩዞ ክለሳ እስከሚያደርግበት ድረስ፣ ረቂቅ አዋጁ የንብረት ታክስ የሚከፈልበትን ምጣኔ ዝቅተኛ ወለልና ከፍተኛ ጣሪያ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

 በዚህም መሠረት አንድ ንብረት ዓመታዊ ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ የሚሠላው፣ ከንብረቱ የገበያ ዋጋ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡

ይህ የሆነበትን ምክንያት ለሪፖርተር ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዋስይሁን አባተ፣ አንድ ንብረት ባለቤቱ ካፈራው በኋላ ሊያድግ በሚችለው ዋጋ ላይ ብቻ ታክስ ለመጣል በመታሰቡ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹የአንድ ንብረት ዋጋ ባለቤቱ ካፈራው በኋላ አደገ ሊባል የሚችለው የዋጋውን 25 በመቶ ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ ዋስይሁን፣ ባለቤቶች በሚያፈሩት ንብረት ላይ በሙሉ ታክስ ሊጣል እንደማይገባም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መንገድና መሰል መሠረተ ልማቶች በቤቱ አካባቢ ሲሠሩ፣ የቤቱ ዋጋ 25 በመቶ ያድጋል፤›› ብለዋል፡፡

 ረቂቅ አዋጁ በተመነው ተመን መሠረት በከተማ ቦታ ላይ የሚጠቀም ባለንብረት ከንብረቱ 25 በመቶ ዋጋ ውስጥ ከ0.2 በመቶ ያላነሰና ከአንድ በመቶ ያልበለጠ የንብረት ታክስ ይከፍልበታል፡፡ ለሚኖርበት ቤት ደግሞ በድጋሚ ከዋጋው 25 በመቶ ውስጥ በትንሹ 0.1 በመቶና በትንሹ አንድ በመቶ የሆነ የንብረት ታክስ ይከፍልበታል፡፡

ለምሳሌ የአሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው መኖሪያ ቤት 25 በመቶው 2.5 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ባለንብረቶችም ከዚህ 2.5 ሚሊዮን ብር ላይ ነው የንብረት ታክስ የሚከፍሉት፡፡

ባለንብረቱ ከ2.5 ሚሊዮን ብር ተሠልቶ በዓመት ለመሬቱ በትንሹ 5,000 ብር፣ በትልቁ ደግሞ 25,000 ብር ሊከፍል ይችላል፡፡ ለቤቱ ደግሞ በዓመት በትንሹ 2,500፣ በትልቁ ደግሞ ድጋሚ 25,000 ብር ሊከፍል ይችላል ማለት ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ ይህን የማስከፈያ ምጣኔ ተምኖ ቢደረግም መኖሪያ ቤቱ ያለበት የከተማ አስተዳደር ደግሞ ትክክለኛውን የታክስ መጠን በአዋጁ ላይ ተመሥርቶ በሚያወጣው የሕግ ማዕቀፍ ይወሰናል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የክፍያ ማዕቀፉን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ክልሎች እንደ ከተሞች ዕድገት የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ከዚህ ማዕቀፍ ሳይወጡ፣ ሕግ በማውጣትና በመወሰን እንደሚተገብሩ አቶ ዋስይሁን አስረድተዋል፡፡

ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠኑን ከወሰኑ በኋላ፣ የዋጋ ንረትን ሳያማክል በዓመት የሚያደርጉት የንብረት ታክስ ጭማሪ እየተከፈለበት፣ ካለበት ዋጋ ከ0.5 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ከዝቅተኛው ጀምረው በአራት ዓመታት ውስጥ ግን ከፍተኛው ጣሪያ ላይ መደረስ እንዳለበትም ረቂቅ አዋጁ ደንግጓል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር አዋጁን በማርቀቅ ሒደት ላይ አስተያየታቸውን ከተቀበላቸው ባለሙያዎች መካከል አንደኛው የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት የታክስ ሕግን ያስተማሩና በግል የሕግ ባለሙያ ታደሰ ሌንጮ  (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡

ቤቶች በዘፈቀደ ግምት ዋጋ እንደሚወጣላቸውና ደላሎች ባሉበት ገበያ ውስጥ ትክክለኛውን የንብረቶች ዋጋ ማወቅ ስለማይቻል፣ የታክስ ክፍያውን ከትንሹ በመነሳት ቀስ በቀስ ማሳደግ እንደሚገባ ባለሙያው አስተያየታቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ባለሙያዎች እንደሰጡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አንደኛው አስቸጋሪ ጉዳይ የቤት ዋጋ አወጣጥ ላይ ባለው አሠራር መሠረት፣ መረጃ ከየት እንደሚመጣ የሚረጋገጥበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡

‹‹የገበያ ተመን ሲጠሩት ደስ ይላል፣ ሲያስተገብሩት ግን በጣም ከባድ ነው፣ ያደናግራል፡፡ የገበያ ተመን በንድፈ ሐሳብ ጥሩ ተደርጎ ይወሰድና በተግባር ግን በጣም ችግር አለው፤›› ሲሉ ታደሰ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

የታክሱ ትልቁ ድክመት ሊሆን የሚችለው የገበያ ተመን አሠራር እንደሆነ  ያስረዱት የሕግ ባለሙያው፣ ከመሬት ጋር በተገናኘ የተጋነነ ዋጋ እንደሚወጣና ደላሎች ለጥቅማቸው ሲሉ ዋጋውን ከሚገባው በላይ እያስወደዱ የዋጋ ተመን ስለሚወጣ ለንብረት ታክስ አከፋፈል ሊወጣ፣ የሚችለውን የዋጋ ተመን አምኖ መቀበል ሊያስቸግር እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

ታደሰ (ዶ/ር) የተሻለ አሠራርና ጥሩ አማራጭ ሆኖ ሊገኝ የሚችለው የኪራይ ዋጋ ተመንን መሠረት በማድረግ ተመኑ ቢወጣ ይሻላል ብለዋል፡፡

በኪራይ ላይ ተመን መሠረት እየተተገበረ ያለው አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ ከተሞች እየሰበሰቡ ያሉት የጣራና ግድግዳ ግብር ነው፡፡

በ1968 ዓ.ም. የወጣውን የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ታክስ አዋጅ መሠረት በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጠኑን ባይቀንስም የኪራይ ዋጋን በማሻሻል እንደ አዲስ ተግባራዊ አድርጎ በርካታ የቤት ባለንብረቶች ከፍተኛ ግብር እየከፈሉ እንደሆነ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡

እንደ ባለሙያው አስተያየት፣ ይህ  ተግባር ‹‹ሕገወጥ›› እንደሆነና መንግሥት ያለሕግ ማሻሻያ ተመኑን ሊለውጥ እንደማይገባው አስረድተዋል፡፡ ‹‹የበፊቱ ሕግ በጊዜው የወጣበት ዓውድ የተለየ ነው፡፡ በጊዜው አስፈላጊ የነበረ፣ ነገር ግን ያረጀና የሞተ ሕግ ነበር፡፡ አዲስ ሕግ እስኪወጣ ሊጠብቁ ይገባ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

አሁን በረቂቅ ያለው የንብረት ታክስ አዋጅ የ1968 ዓ.ም. አዋጅና በ1971 ዓ.ም. የወጣውን ማሻሻያ ይሽራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...