- አየር መንገዱ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በመንግሥት ለውጥ ወቅት የተለመደ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ በመያዝ ናይጄሪያ ኤር የተሰኘ የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን በማቋቋም ሥራ ለማስጀመር ጫፍ የደረሰው ሒደት በአዲሱ የናይጄሪያ መንግሥት ለጊዜው መታገዱ ተሰማ።
የናይጄሪያ የአቪዬሽንና ኤሮስፔስ ልማት ሚኒስትር ፌስቱስ ኬያሞ እ.ኤ.አ. ኦገስት 31 ቀን 2023 ባሳለፉት ውሳኔ፣ ናይጄሪያ ኤር የተሰኘው አየር መንገድ የምሥረታ ሒደት ለጊዜው መታገዱ ታውቋል።
ናይጄሪያ ኤር የሚል ስያሜ የተሰጠው የናይጄሪያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ. በ2018 በለንደን ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በወቅቱ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት መሐመድ ቡሃሪ አስተዳደር እ.ኤ.አ. ሜይ 29 ቀን 2023 ሊያበቃ ሦስት ቀናት ሲቀሩት ደግሞ አየር መንገዱ መመሥረቱ ይፋ ተደርጎ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በናይጄሪያ ኤር ላይ የ49 በመቶ ድርሻና የማስተዳደር ኃላፊነቱን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ናይጄሪያ ኤር የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ በረራዎችን በመጪው ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. እንደሚጀምር ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር፡፡
አቶ መስፍን የናይጄሪያ አየር መንገድ በሁለት ግዙፍ አውሮፕላኖችና በስድስት አነስተኛ አውሮፕላኖች ሥራውን በመጪው ጥቅምት ወር እንደሚጀምር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
‹‹የናይጄሪያ አየር መንገድ በረራ ጀምሮ የአገር ውስጥ ገበያን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ሲያገናኝ ለማየት ጓጉተናል፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማኔጅመንት ውል ይኖረዋል፡፡ በዚህም የናይጄሪያ አየር መንገድን ያስተዳድራል። ዋናው ዓላማ ደግሞ ናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ እንዲኖራት ማስቻል ነው፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ አዲሱ የናይጄሪያ የአቪዬሽንና ኤሮስፔስ ልማት ሚኒስትር ፌስቱስ ኬያሞ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባሳለፉት ውሳኔ፣ የናይጄሪያ አየር መንገድ ምሥረታን አግደዋል። ሚኒስትሩ ዕገዳውን ካስታወቁ በኋላ የናይጄሪያ አየር መንገድን የምሥረታ ሒደት እንዲቀጥል ከመፈቀዱ በፊት፣ የአገሪቱ መንግሥትና ናይጄሪያውያን ሀቀኛ ግምገማ ሊያደርጉበት ይገባል ብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ወደፊት በሚወጣ መግለጫ መፈቀዱ እስኪገለጽ ድረስ በዘርፉ የሚደረጉ ኮንትራቶችና ፕሮጀክቶች በሙሉ መታገዳቸውንም አስታውቀዋል።
የናይጄሪያውን የአቪዬሽንና ኤሮስፔስ ልማት ሚኒስትር የዕገዳ ውሳኔን በተመለከተ ሪፖርተር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ የአየር መንገዱ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን በሰጠው ምላሽ አዲሱ የናይጄሪያ መንግሥት የናይጄሪያ አየር መንገድን የማቋቋም ሒደት ለጊዜው እንዲቆይ መወሰኑን አረጋግጧል፡፡
‹‹አዲሱን የናይጄሪያ አየር መንገድ ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግሥትና በናይጄሪያ ከሚገኙ ሌሎች ተቋማት ጋር ስንወያይ ቆይተናል፤›› ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን፣ ‹‹በፕሮጀክቱ ላይ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ከፍተኛ መሻሻል አሳይተናል፤›› ብሏል።
ይሁን እንጂ በቅርቡ በናይጄሪያ የተከሰተውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ አዲሶቹ የአገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣናት አዲስ የመጡ ፕሮጀክቶችን ለመገምገምና ለማፅደቅ የተወሰነ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመጥቀስ፣ ፕሮጀክቱን ለጊዜው ማገዳቸውን አስረድቷል።
‹‹በአንድ አገር ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ በአገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ስለዚህ አዲሱ የናይጄሪያ መንግሥት ፕሮጀክቱን እንድንቀጥል እስኪወስን ድረስ እየጠበቅን ነው፤›› ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮርፖሬሽን ገልጿል።
የምሥረታ ሒደቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ሊገባ በነበረው የናይጄሪያ አየር መንገድ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የያዘ ሲሆን የተለያዩ የናይጄሪያ የግል ባለሀብቶች ደግሞ 46 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን፣ የተቀረው አምስት በመቶ ድርሻ ደግሞ በናይጄሪያ መንግሥት ተይዞ መዋቀሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የናይጄሪያ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተከፈለ ድርሻ ላይ ጉዳት ያመጣ እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹የባለአክሲዮኖች ስምምነት ገና ስላልተፈረመ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሁሉም ባለአክሲዮኖች ለናይጄሪያ አየር መንገድ የአክሲዮን ድርሻ ክፍያቸውን አልፈጸሙም፤›› ብሏል።
እንደ ፓን አፍሪካ አየር መንገድ በአኅጉሪቱ ያለውን የአየር ትራንስፖርት ንግድ ለማሳደግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቁርጠኛ መሆኑን፣ ለዚህም ከአፍሪካ መንግሥታትና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር በተለያዩ አገሮች የጀመረውን ብሔራዊ አየር መንገዶችን የማቋቋም ፕሮጀክት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር አረጋግጧል።