Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ...

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ እንቅስቃሴ ላይ በመከረው ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን በዲፕሎማቲክ አማራጮችና በትብብር ማዕቀፎች ላይ ትኩረት እንድታደርግ ጥሪ ቀረበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከመከላከያ ዋር ኮሌጅ ጋር በመተባበር መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ‹‹የቀይ ባህር የደኅንነት ሁኔታ ቀጣናዊ ምክክርና ትብብር መልከዓ ፖለቲካዊ መጠላለፍ በበዛበት ዓለም ወቅት›› በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጉባዔ፣ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የተመረጡ የውጭ ዲፕሎማቶች፣ ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋናዮች የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ሌሎች ተጋባዦች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ በኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነትና በቀጣናው ያለው የኃያላን አገሮች  ፉክክር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ በመድረኩ ሁሉም የቀይ ባህር ቀጣና አገሮች ዲፕሎማቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከባለሀብቶችና ከሚዲያ ኃላፊዎች ጋር በተለያዩ መድረኮች አደረጉት በተባለው ንግግር፣ አትዮጵያ በተለያዩ አማራጮች የወደብ ባለቤት ትሆናለች ብለው መናገራቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች በስፋት ሲሠራጩ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ ባተኮረው መድረክ በዋናነት ከተንፀባረቁ ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት ጉዳይ ሲሆን፣ በዚህ አጀንዳ ላይ ወደብ የመጠቀም መብት ወይስ የወደብ ባሌበት የመሆን፣ ወደብን በኃይል የመውሰድ ወይስ በዲፕሎማቲክ መንገድ የማሸነፍ የሚሉ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡

በውይይቱ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን አገር ወደብ አልባ ማድረግና በቀይ ባህር ቀጣና ላይ በሚከናወኑ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ማግለልን በዝምታ ማለፍ ለመጪው ትውልድ ፈተና ጥሎ መሄድ ነው ያሉት፣ የቀድሞው የዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ማኅበር የቦርድ አባል አቶ እንድሪስ መሐመድ ናቸው፡፡

‹‹ከዚህ በፊት የነበረው የእኔ ትውልድ አገሪቱን ወደብ አልባ ያደረጋትን ስህተት ማናቸውም አማራጮች በመጠቀም መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ሥራ መሥራት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ወደብ የማግኘት ጉዳይ አማራጭ የሌለው በመሆኑ በሰጥቶ በመቀበል፣ ከዚያም ካለፈ የኃይል አማራጮችን የመጨረሻ መንገድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ እንድሪስ አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሳፍንት ተፈራ፣ ከቀይ ባህር ፖለቲካ ኢትዮጵያን አግልሎ መቆየት የማይቻል በመሆኑ ማናቸውም ቀይ ባህርን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሚና ልትጫወት ግድ ይላታል ብለዋል፡፡

ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በፀጥታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በደኅንነት ወይም በሌላ ጉዳይ እያደገ ከሚመጣው ፍላጎት ጋር ከቀይ ባህር ውጭ መንቀሳቀስ የማይቻላት በመሆኑ፣ በዚህ ቀጣና በማንኛውም ኢትዮጵያን ተሳታፊ ሊያደርግ የሚችል ጉዳይ ላይ ተሳታፊ መሆኗን ማረጋገጥ እንደሚገባት አብራርተዋል፡፡

በቀይ ባህር ቀጣና የደኅንነትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ባተኮረው መድረክ ምክትል ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ቀይ ባህርን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደ አንድ ጥናት ተቋም መከናወን ያለባቸው አስፈላጊ የመፍትሔ አማራጮች በገለልተኝነት  ተዘጋጅተው በየጊዜው ለውይይት ይቀርባሉ ብለዋል፡፡

በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉትና በቀጣናው ጉዳይ ላይ ዕውቀት ያካበቱት ግሩም ዓባይ (አምባሳደር) እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ያስፈልጋታል የሚለው ጉዳይ በአመዛኙ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዕሳቤ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ወደብ ባለቤት ትሆናለች የሚለውና ወደብ የመጠቀም መብት ይኖራታል የሚለው ጉዳይ ተለያይቶ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ይህ ማለት አንድ አገር የሌላን አገር ድንበር አልፎ መሀል ላይ የወሰን ንብረት ባለቤት ነኝ ብሎ መናገር የማይቻል በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የወደብ ባለቤትነት የሚባለው ንግግር ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን ያስረዱት ግሩም (አምባሳደር)፣ ባለቤትነት የሚለው ጉዳይ የማያስኬድ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ  የወደብ ተቃሚነትን ላይ ለመነጋገር ሲታሰብ የወደብ ባለቤትነትንና የመጠቀም መብትን ዕሳቤ ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ፣ የማንንም ድንበር በኃይል እወስዳለሁ ብሎ መነሳት የማይቻልና ዓለም አቀፍ ሕግንም የሚጥስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለወደብ እንሁን በሚል የተለያዩ ሐሳቦች ሲነሱ ይደመጣል፣ ነገር ግን ይህ በፍላጎት ብቻ የሚሳካ ነገር ባለመሆኑ ምክንያታዊ በመሆንና አካባቢን በማጥናት በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉ አማራጮችን በሰላማዊ መንገድ መፈለግ ያሻል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የተረጋገጠ የባህር ወደብ ማግኘት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ትልልቅ አገሮች ጭምር ለኢትዮጵያ የወደቡን አስፈላጊነት በብዙዎች ዘንድ እምነት የተጣለበት ነው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ አቀማመጧን በመውሰድ የቀይ ባህር ኃይል ነች ለሚለው ጥያቄ የባህር ዳርቻ ስለሌላት አይመለከታትም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከቀይ ባህር በ48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝና እያደገች ያለች ትልቅ አገር በመሆኗ፣ በአፍሪካ በዲፕሎማሲውም ሆነ በፖለቲካው ተፅዕኖ እየፈጠረች ያለች፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ስለሆነች የባህር ጠረፍ የላትም በሚል ከቀይ ባህር እንዳትጠቀም ማድረግ የማይሆን ጉዳይ ነው፤ ሲሉ አክለዋል፡፡

ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ግሩም (አምባሳደር)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ በመጣ ቁጥር የተረጋገጠና ዋስትና ያለው የባህር በር ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት አለባት የሚለው ጉዳይ በምን መልኩ ይመለስ የሚለው ጉዳይ ግን ምክክርና ውይይት ያስፈልገዋል ያሉት ሌላኛው ተሳታፊ የምክክር፣ ጥናትና ትብብር ማዕከል የተሰኘ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አብደታ ድሪብሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የወደብን ጉዳይ የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚያመላክቱትን አማራጭ ማየት ያስፈልጋል ብለው፣ ነገር ግን በዲፕሎማሲው ማሳመን ሳይቻል በኃይል ለመሄድ ሲሞከር ከሚጠቁት አገሮች ጀርባ ሌሎች ደጋፊ አገሮችና ዓለም አቀፍ ሕግ በመኖሩ፣ በሌላ አገር መሬት ላይ ጦርነት ከፍቶ የትም አይደረሰም በማለት ተናግረዋል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ ወይም ከቀጣናው አገሮች በአንዱ ለኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል አዲስ መሪ ሲተካ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በስፋት የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ የቀጣናው የደኅንነት ሥጋትን የተመለከተ ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ ግሩም (አምባሳደር) እንዳብራሩት፣ በቀጣናው በርካታ ሽኩቻዎችና ፉክክሮች ስላሉ በርካታ ዓይኖች እያማተሩ ናቸው፡፡ የቀይ ባህር ቀጣና አገሮች ከምንጊዜውም በላይ ትብብር ካልመሠረቱ በሜዳቸው የተመልካች እንጂ የተጫዋችነት ሚና አይኖራቸውም ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በሚገኙ አገሮች የፖለቲካ ሽግግር መኖሩን፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የደኅንነትና የዲፕሎማሲ ፍላጎት ማደጉንና እነዚህ አገሮች ባላቸው ሀብት ወደቦችን እየገዙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ቀጣና የታላላቅ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆኑት ቻይና፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ቱርክና መሰል አገሮች የሚያደርጉት ፉክክርም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም ያማከለ ወዳጅነትና ትብብር መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡  

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ዲፕሎማትና የቀጣናው ጉዳይ ተንታኝ ዘሪሁን አበበ፣ በቀይ ባህር ቀጣና ኢትዮጵያን በማግለል የሚመሠረት ማንኛውም ዓይነት ትብብር ውጤታማም እንደማይሆንና ፍሬም እንደማያፈራ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ቀጣና የሚደረጉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ወይም የደኅንነት ፉክክሮችን ኢትዮጵያ ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ብለዋል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም አማካሪ ሌተና ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህር ቀጣና እያሳዩት ያለው ፍላጎት የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎችን ለማጋበስ ነው ብለዋል፡፡  

በመሆኑም በዚህ አሳሳቢ በሆነው ቀጣና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ጠንካራ ትብብር በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አገሮቹም ለዚህ አመቺ የሆነ አዲስ የፖሊሲ አማራጭ መተግበር እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ ፓስፊክና እስያ ጉዳዮች ዳይሬክተር ገበየሁ ጋንጋ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 ወዲህ በቀይ ባህር አካባቢ በርካታ የዓለም አገሮች የርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በከፍተኛ ሁኔታ ሲማትሩ ይታያሉ ብለዋል፡፡ በዚህ ፉክክር ምክንያት ቀጣናው የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ቀጣናው የሚመሠረቱ አዳዲስ አገሮች መብዛትና አገሮቹም በሚፈለግባቸው መጠን እንደ አገር ጠንክሮ መቆም አለመቻል፣ ለዓለም አቀፍ የሽብርተኛ ተቋማት ምቹ ምኅዳር እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁሉን አቀፍና አካታች የጋራ ዕቅድና ትልም በማውጣት፣ ችግሩን በዘላቂነት የመፍቻ መንገድ ማበጀት ተገቢ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ የቀጣናው አገሮች የትብብር ፎረም መመሥረት ከቻሉ ከውጭ ኃይሎች የሚመጣን ያልተገባ የፖለቲካ ፉክክር የመቀነስ አቅም እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በትብብር መሥራት ባለመቻላቸው ከመካከለኛው ምሥራቅም ሆነ ከምዕራባውያን አገሮች ወደ ቀጣናው መጥተው መፎካከራቸው ምክንያቱ፣ የቀጣናው አገሮች መተኛት ነው የሚሉት ደግሞ አብደታ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የቀጣናውን አገሮች መተኛት በምሳሌነት ሲያብራሩ፣ ‹‹ለአብነት በሱዳን በተፈጠረው ቀውስ አገሮች ቁጭ ብለው የተነጋገሩበት ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ራቅ ካሉ አገሮች መጥተው በጉዳዩ ላይ ተዋናይ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡ በጦርነቱ ውስጥ ያሉት የጦር ጄኔራሎች ብቻ ሳይሆኑ ስለጦርነቱ ባህሪና ስለውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነት ግልጽ የሆነ ምክክር ያስፈልጋል ያሉት አብደታ (ዶ/ር)፣ በቀጣናው አገሮች መካከል ያለው ትልቁ ችግር እንደሚባለው በግልጽ አለመተዋወቃቸውና መነጋገር አለመቻለቸው ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...