Saturday, July 20, 2024

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ምሁራንና ልሂቃን አገር አንዴ ካመለጠች እንደማትገኝ አውቃችሁ፣ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና ኃላፊነት የሚጠበቅባችሁን ተወጡ፡፡ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ መወጣት አቅቷችሁ ችግሮች ተባብሰው አገር ካመለጠች፣ በመጪው ትውልድና በታሪክ የሚያስጠይቅ ወንጀል እንደ ሠራችሁ ይቆጠራል፡፡ ብዙዎቹ በጦርነት የፈራረሱ አገሮች ምሁራንና ልሂቃን ትልቁ ፀፀትና ቁጭት፣ ያኔ አገራችንን ለምን ካንዣበበባት አደጋ ለመታደግ አቃተን የሚል ነው፡፡ ለዓመታት የተከማቹ ቂምና ጥላቻዎችን በሰላማዊ መንገድ አለዝቦ አገራዊ የጋራ ራዕይ መያዝ እየተቻለ፣ ጥቃቅን የታሪክ ሰበዞችን በመምዘዝ በአገር ላይ መዓት የሚያመጣ ቅራኔ መፈልፈል አገር እንደሚያፈርስ መማር አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተምረዋል የሚባሉ ልጆቹ ከዘመናት ችግር ሊያላቅቁት ሲገባ፣ ጭራሽ በእነሱ ብሶ ሲያስፈጁትና ሲያሠቃዩት መማራቸው ቢያጠራጥረው አይፈረድበትም፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ሲፈጠር ነው በቁጭት ተነሳስቶ አገርን ከመቀመቅ ለመታደግ መረባረብ የሚያስፈልገው፡፡

በአገር ጉዳይ ቁጭት ውስጥ የሚከቱ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከቁጭቶች መካከል ኢትዮጵያ ያገኘቻቸውን መልካም አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ለመጠቀም አለመቻሏ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚዎች በርካታ ዕድሎች ያመለጧት አሳዛኝ አገር ናት፡፡ የተማሩ ልጆቿ በጣም በሚበዙ ጉዳዮች ላይ ለአገራቸው መልማትና ማደግ የሚፈለግባቸውን አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ፣ እዚህ ግቡ በማይባሉ ምክንያቶችና ሰበቦች ሳቢያ መስማማት ባለመቻላቸው ከድህነትና ከግጭት ውስጥ መውጣት አልቻለችም፡፡ ለቁጥር የሚያታክቱ የመልካምነት ምሳሌ የሆኑ ዘመናትን የተሻገሩ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ አገር በቀል ዕውቀትን በሚያናንቅ አጉል ዘመናዊነት ምክንያት የደረሱ ጉዳቶች ቁጭት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆጨት ባህል እስኪመስል ድረስ በበርካታ ጉዳዮች መብሰልሰል የተለመደ ሆኗል፡፡ ዜጎች ከዕለት ኑሮዋቸው ጀምረው እስከ አገራቸው ዕጣ ፈንታ ድረስ ከመጠን በላይ ይጨነቃሉ፡፡ በአንድ በኩል ፋታ የማይሰጠው የኑሮ ውድነት፣ በሌላ በኩል የሰላምና የደኅንነት ዕጦት የዘመኑ ፈተና ሆነዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ባለመኖሩ ምክንያት ቁጭት የዕለት ተዕለት መደበኛ ተግባር እየሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ያካበቱት ዕውቀትና ልምድ የአገር ችግር የማይፈታ ከሆነ ፋይዳው ምንድነው የሚል ጥያቄ ይቀርብበታል፡፡ ምሁራኑና ልሂቃኑ ከምንም ነገር በፊት አገር ላይ የተደቀኑ ሥጋቶችን መቅረፍ ካልቻሉ የእነሱስ ፋይዳ ምን ይረባል እየተባለም ነው፡፡ ቀደም ሲል በአንገብጋቢነታቸው ከሚታወቁት የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በላይ፣ ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው እንስሳ የህልውና ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ እየሆነ ነው፡፡ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሳቢያ ሕይወታቸው ከዕለት ወደ ዕለት ከድህነት ወለል በታች እያሽቆለቆለ ነው፡፡ በየቀኑ በምግብም ሆነ በምግብ ነክ ቁሳቁሶች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከአቅም በላይ ሆኖባቸዋል፡፡ ከወር ገቢያቸው ላይ እንኳንስ ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ፣ ለመኪና መግዣና ለሌሎች ጉዳዮች ሊቆጥቡ ቀርቶ የቤት ኪራይና የምግባቸውን ወጪ መሸፈን ተስኗቸዋል፡፡ የምግብና የሌሎች አቅርቦቶች የዋጋ ንረት ከመጠን በላይ መክበድ ለብዙዎች ከባድ ፈተና ሆኗል፡፡ ይህንን በጣም መሠረታዊ የሆነ ችግር መፍታት የሚችል ዕውቀትና ልምድ በከንቱ እየባከነ ቁጭቱ ተበራክቷል፡፡

ሌላው አስፈሪውና የአገርን ህልውና እየተፈታተነ ያለው የሰላም ዕጦት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ፣ ኢትዮጵያን ወደ መጨረሻው የጥፋት ጠርዝ እየገፋት ነው፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ መሥራት፣ ምርቶችን ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው ማንቀሳቀስና በአጠቃላይ በሁሉም ቦታዎች ሥጋት መስፈኑ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተገታ ማግሥት፣ በአማራ ክልል መጠነ ሰፊ ግጭት እየተካሄደ የዜጎች ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ አንፃራዊ ሰላም የነበራቸው አካባቢዎች ሳይቀሩ የሥጋት ደመና አጥልቶባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ለዓለም ሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገች አገር ከግጭት ጋር አልለያይ ብላ፣ ከዚህ ቀደም በጦርነት ወደ ወደሙና ወደ ጨነገፉ አገሮች ተርታ እየተንደረደረች ነው፡፡ አገር ሰላም ርቋት ዙሪያው አስፈሪ ሆኖ ለዓመታት የተከማቸ ዕውቀትና ልምድ ግን እየባከነ ነው፡፡ ለተቃርኖ መነሻ የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶችን በቅደም ተከተል ለይቶ መፍትሔ መፈለግ፣ የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን ተግባር መሆን ሲገባው በግራና በቀኝ የሚስተዋለው ደንታ ቢስነት ያስፈራል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተማሩ፣ የተመራመሩና የበቁ የሚባሉ ልጆቹ ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ ካላወጡት ምን ይፈይዱለታል? የዛሬ ሃምሳ ዓመት አካባቢ በግብታዊነት ከፈነዳው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ወዲህ በኢትዮጵያ በርካታ ግጭቶች፣ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ እንዲሁም በአገር ሀብት ላይ መጠኑን ለመግለጽ የሚያዳግት ውድመት ደርሷል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን በተለያዩ ጎራዎች በአካልም ሆነ በመንፈስ ተሠልፈው እርስ በርሳቸው ሲፋለሙ፣ ብዙዎች ደግሞ ከአሸናፊው ጎን ለመሠለፍ ያደፍጡ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ አገር በቀል ዕውቀቶችና የግጭት መፍቻ ሥልቶች ተንቀው ከውጭ በተቃረሙ ርዕዮተ ዓለማዊ ዕሳቤዎች አገር መቅኖ ስታጣ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች ያለ ጥፋታቸው የመከራ ዶፍ ሲዘንብባቸውና በተፈጥሮ የታደልናቸው የአገር ሀብትና ፀጋዎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቀርተው ሕዝባችን ለምፅዋት ጠባቂነት ተዳርጓል፡፡ የምግብ ችግርን መፍታት አቅቶ ለሚሊዮኖች የባዕዳንን ዕርዳታ አንጋጦ ከመጠበቅ ውጪ አማራጭ ጠፍቷል፡፡ ይህ ሁሉ ፍዳና መከራ ቁጭት ውስጥ ከቶ ሰላም ማስፈንና መልማት ካልተቻለ የምሁራኑ ዕውቀት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉም ወገኖች አሰልቺ ከሆነው የመካሰስ፣ ደም የመቃባትና የመጠፋፋት አባዜ ውስጥ እንዲወጡ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አንድን የተሳሳተ ነገር እየደጋገሙ ቢሠሩት ትርፉ ልፋት እንጂ ውጤት እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሐሳብ ልዩነትን ለማስተናገድ የሚኬድበት ርቀት በጣም ከመጣመሙ የተነሳ፣ ስህተትን በሌላ ስህተት መደጋገም የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የጥፋት አዙሪት ውስጥ በመውጣት የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ሰላም ቅድሚያ ይሰጠው፡፡ አንዱ ሌላውን አሸንፎ ሥልጣንን ማረጋገጥም ሆነ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በጊዜያዊ ድል የሚገኝ የበላይነትም ሆነ የመንሰራፋት ፍላጎት ማንንም የትም አላደረሰም፡፡ አንዱ ከሌላው የጥፋት ታሪክ መማር ካልቻለ አለ የሚባለው ዕውቀት ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ሁልጊዜ ነገሮች ካለፉ በኋላ ከመቆጨትና ጥርስን ከማፋጨት ይልቅ ከጥፋት መታረም መቅደም ነበረበት፡፡ በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ስለሆነ ይብቃ ማለት ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...