Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢትዮጵያ ለአራት ወራት ዕርዳታ ያልቀረበላቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ሕይወት አደጋ ላይ...

በኢትዮጵያ ለአራት ወራት ዕርዳታ ያልቀረበላቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

  • የደቡበ ሱዳን ስደተኞች እየሞቱ መሆናቸው ተገልጿል

ኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አስጠልላቸው የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች የዕርዳታ እህል በመቋረጡ፣ ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑንና ለአገርም የደኅንነት ሥጋት መደቀኑ ተነገረ፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ ተፈጸመ ባሉት የዕርዳታ እህል ዝርፊያ ምክንያት፣ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ዕርዳታ ማቆማቸው ይታወሳል፡፡

የምግብ አቅርቦቱ እንደገና እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥት እየተነጋገርኩበት ነው ቢልም፣ ዕርዳታው እየቀረበ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ የተጠለሉ የውጭ አገሮች ስደተኞች በምግብ ዕጦት እየሞቱና ሕመም ላይ መውደቃቸውን፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተመሳሳይ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለተረጂዎች እየቀረበ ባለመሆኑ ወደ 400,000 የሚጠጉ በጋምቤላ ክልል ውስጥ በካምፕ የሚገኙ ስደተኞች ሕይወት አደጋ ውስጥ መውደቁን ገልጾ አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ወር ጀምሮ ዕርዳታ ያላገኙ ስደተኞች በምግብ እጥረት የተነሳ በሚመጣ ረሃብ ለሞትና ለከፋ ሕመም እየተጋለጡ መሆናቸውን፣ አካሄድኩት ባለው ክትትል አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም አገኘሁት ባለው መረጃ በምግብ እጥረት ምክንያት በጋምቤላ ብቻ 30 ሰዎች መሞታቸውን፣ አምስት ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት ለከፋ ሕመም መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡

በተከሰተው የምግብ እጥረት የተነሳ ከስደተኞች መጠለያ ካምፕ ወጥተው ወደ ማኅበረሰቡ በሚገቡበት ወቅት ለሰላም ችግር መንስዔ መሆናቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት የተገለጸ ሲሆን፣ ከመጠለያ ወጥተው በምግብ ስርቆት በመሰማራታቸውና ከቆሻሻ ላይ ምግብ ለማንሳት ሲጥሩ ሕይወታቸው ያለፉ መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋምቤላ ክልል ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤል አዳነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጋምቤላ የሚኖሩ ስደተኞች በአብዛኛው ከጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ናቸው፡፡ በምግብ እጥረት የሞቱትም በአብዛኛው እነዚሁ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች ናቸው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በጋምቤላ ከሚገኙ በሦስት መጠለያ ካምፖች ክትትል ያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ አቤል፣ በርካታ ስደተኞች አደጋ ላይ በመሆናቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በአካል ንጉሤ፣ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ስታስተናግድ የዓለም አቀፉን ሕግ መሠረት በማድረግ ከለላና ጥበቃ የምታደርግ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስደተኞች የሚቀርበው ዕርዳታ በመቆሙ ቀውስ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱትና የሚታመሙት ወይም የሚቸገሩት ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ችግር ሲፈጠር በመሠረታዊነት የመጀመርያ ተጎጂ ሕፃናትና ሴቶች በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በመጠለያ ካምፕ የሚገኝን ሀብት አፈላልጎ ለመመገብ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት፣ ስደተኞቹ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ ይገቡና ሰላማዊ የኑሮ ሁኔታን የሚያናጋ እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ምግብ ነክ ድጋፎች እየቀረቡ አለመሆናቸውን፣ በቀጣይ አፋጣኝ ዕርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ በሁሉም የአገሪቱ መጠለያ ካምፖች ችግሩ መከሰቱን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን ለመታደግ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ንግግር እያደረጉ መሆኑን፣ በአጭር ጊዜ ዕርዳታው እንደገና ይጀመራል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ በአካል ተናግረዋል፡፡

በስደተኛ ቁጥር በጋምቤላ ወደ 400,000 በቦሎ መልካዲዳ በሶማሌ ክልል 200,000፣ በቤኒሻንጉል አሶሳ ወደ 90,000፣ በአፋር 68,000፣ በሶማሌ ጅግጅጋ ወደ 50,000፣ አማራ ክልል ባባት 25,000፣ መተማ ወደ 40,000፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ወደ 80,000 ስደኞች እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ከ900,000 በላይ የሚሆኑት በመጠለያ ካምፕ ውስጥ መሆናቸውን ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...